የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በየጊዜው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ በተለይ በቅርቡም ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከእጥፍ በላይ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል።
አዲስ ማለዳ ከተጠቃሚዎች ባገኘችው መረጃ መሠረት፣ ለአብነትም ኮምፎርት የተሰኘው የንጽህና መጠበቂያ ከአንድ ዓመት በፊት በ35 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ ከሦስት ወር በፊት 45 ብር ሲሸጥ ነበር ብለዋል። እንዲሁም ከወር በፊት ደግሞ ዋጋው 55 ብር ሊደርስ የቻለ ሲሆን፣ አሁን ላይ ከ65 ብር ጀምሮ እስከ 100 ብር እየተሸጠ መሆኑንም ነው የገለጹት።
አዲስ ማለዳ በተለያዩ ቦታዎች ባደረገችው የገበያ ቅኝትም ከ35 ብር ጀምሮ እንደየመሸጫ ቦታው እና የንፅህና መጠበቂያው ዓይነት እስከ 100 ብር ድረስ እንደሚሸጥ ተመልክታለች። በዚህም ከሦስት ወር በፊት 25 ብር ገደማ ይሸጥ የነበረው በአሁኑ ወቅት ከ50 ብር በላይ እንደሚሸጥ ነው መረዳት የተቻለው።
ዋጋው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ጭማሬ እያሳየ ሲሆን፣ በርካታ ሴቶችም የንፅህና መጠበቂያ ምን ያህል መሠረታዊና አስፈላጊ እንደሆነ ያነሳሉ። ተጠቃሚዎች ‹‹በወር አበባ ወቅት የንጽህና መጠበቂያው በየስድስት ሰዓት ካልተቀየረ ለማኅፀን ካንሰር ሊዳርግ ይችላል aቀን እንኳን አይሆንም። በዚህ ሁኔታ እንዴት እንደምናደርግ አናውቅም።›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ኤልሻዳይ ገበየሁ፣ ሴቶች በወር አበባ ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች (ሞዴስ፣ ፓድ) ለማስገባት መንግሥት ድጎማ (Subsidize) እንደሚያደርግ መግለጹን አስታውሳለሁ ሲሉ ጠቅሰዋል። ‹‹በወቅቱ ይህ ለእኛ ትልቅ እፎይታ የሚያመጣና አንድ እርምጃ ለመራመድ የሚያስችል ነው ብለን ነበር።›› ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ሆኖም አሁን ገበያ ላይ ያለው ነገር ግን፣ መንግሥት ካለው ጋር የማይገናኝ በመሆኑ ወይ ወደ ተግባር አልገባም አልያም ደግሞ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች ድጎማውን ተጠቅመውና ከዚያም በላይ አስፍተው አላግባብ ትርፍ እያገኙበት ነው ሲሉ አመላክተዋል።
ስለዚህም፣ የወጣው መመሪያ አፈጻጸም ምን ያህል እንደሆነና ክፍተቱ የቱ ጋር እንደሆነ አላውቅም ያሉት ኃላፊዋ፣ ከላይ የሚነገረውና መሬት ላይ ያለው ተቃራኒ ሆኖ ከተገኘ ትልቅ የአፈጻጸም ክፍተት መኖሩን ያሳያል ሲሉ ተደምጠዋል።
ብዙ ጊዜ ማሻሻያዎች ሲኖሩ ጉዳዩ የአንድ ሰሞን አጀንዳ ይሆንና ይረሳል፣ ሲጀመርም ለሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ማግኘት የመብት ጉዳይም ነው ብለዋል።
ሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን መጠቀም ካልቻሉ ጫናው በጣም ሰፊ ነው የሚሉት ኃላፊዋ፣ ከትምህርት ቤትና ከሥራ ይቀራሉ፣ ከቤት ወጥተውም ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ እንዳይሳተፉ ይከለክላቸዋል። በሴቶች ላይ ካለው ጫና አንጻር ይህ ሲጨመርም ማነቆው ይበዛል ነው ያሉት።
አክለውም፣ በቀጣይ በዚህ ጉዳይ ላይ እንቅስቃሴ እንጀምራለን ሲሉ ገልጸው፣ በሴቶች ላይ የሚሠሩና የሴቶች መብት ያገባናል የሚሉ አካላትም በመንግሥት የተነገረው ለምን ተፈጻሚ እንዳልሆነና ማን ተጠያቂ እንደሚሆንም መጠየቅና መሠራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል የሕፃናት ንፅህና መጠበቂያም (ዳይፐር) ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ እየተነገረ ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ በእሽግ 200 ብር ይሸጥ የነበረው በአሁኑ ወቅትም፣ አንድ ፍሬ ከ80 ብር በላይ እና የታሸገው ደግሞ ከ400 ብር በላይ እየተሸጠ ነው መባሉን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
አዲስ ማለዳ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት፣ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መስከረም ባህሩ በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።
ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014



