ከ390 በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሠራተኞች ድርጅቱ ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ ‹ፍትኃዊ ባለመሆኑ› ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ቅሬታ አቅራቢ ሠራተኞቹ ለአዲስ ማለዳ ያሳወቁት፤ ድርጅቱ የብሩን መጠን ሳይገልጽ ለተከታታይ ወራት ደመወዝ ይጨመርላችኋል ሲል ቢቆይም፤ የደመወዝ ጭማሪው ሲደረግ ግን ለአመራሮቹ እንጂ ከ390 በላይ ለሚሆኑት የድርጅቱ ሠራተኞች ተገቢው ጭማሪ እንዳልተደረገላቸው ነው።
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የድርጅቱ ሠራተኛ ለአመራሮቹ ለቤት ኪራይ ተብሎ 18 ሺሕ ብር፤ ለትራንስፖርት ተብሎ 10 ሺሕ ብር የደመወዝ ጭማሪ እንደተደረገላቸውና የሌሎች ሠራተኞች ግን ዝቅተኛ 450 ከፍተኛ ደግሞ 500 ብር ጭማሪ ነው የተደረገው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በተለያዩ ጊዜያት በነበሩት ስብሰባዎች ሠራተኞቹ የኑሮ ውድነትን በማንሳት የደመወዝ ጭማሪ ሲጠይቁ ድርጅቱ የጭማሬውን መጠን ባይገልጽም ጭማሪ እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ ቃል ሲገባ ቆይቷል ነው የተባለው።
በመሆኑም፣ “ከሥራ አስኪያጁ፤ ከዋና አዘጋጁና ከምክትል ዋና አዘጋጁ ውጭ ያሉት ሠራተኞች በሙሉ ቅሬታ ውስጥ ናቸው” ብለዋል።
ጥያቄ ለማቅረብ ቢሞክሩም እንዳልተቻለ ያመላከቱት ቅሬታ አቅራቢው፣ ‹‹እንዲያውም ጥያቄ እንዳይቀርብ ለተወሰነ ጊዜ ዋና ሥራ አስኪያጁ የት እንደሄዱ ሳይታወቅ ጠፍተው ነው የሰነበቱት።›› ብለዋል።
ሌላኛው ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የድርጅቱ ሠራተኛ በበኩላቸው፣ ድጋፍና የተሻለ የደመወዝ ጭማሪ ሊደረግላቸው ከሚገባቸው ከ390 በላይ ሠራተኞች ይልቅ ድጎማና የተሻለ የደመወዝ ጭማሪ የሚደረግላቸው አመራሮቹ ናቸው ብለዋል።
የራስን ጥቅም ብቻ በማስቀደም መጣደፍ ይስተዋላል ያሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ የመዋቅር ችግር እንዳለና የመልካም አስተዳደር ቁጥጥር እንደሌለ ነው ያብራሩት።
‹‹ደመወዝ ጨምረናል በሚል ሥም አመራሩ የራሱን ጥቅማ ጥቅም የማካበት ሥራ ነው የሠራው።›› ያሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ ጭማሬ እየተደረገላቸው ያሉት በአንድም በሌላም ጉዳይ በመንግሥት በኩል ድጋፍ እየተደረገላቸው ያሉ አመራሮች እንጂ በስር ያሉ ሠራተኞች እንዳልሆኑ ነው ያብራሩት።
አክለውም አመራሮቹ በመንግሥት የተዘጋጀ ቤት እንዲሁም ነዳጅና መኪና አላቸው ሲሉ ጠቁመው፤ በሕጉ መሠረት የቤት አበል ያለው አካል የትራንስፖርት አበል ሊወስድ አይገባም ነበር ብለዋል።
ቅሬታ አቅራቢው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ይህን መሰል አሰራር እየተፈጸመ ያለው በተደጋጋሚ ነው።
የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ አመራሮቹ የመንግሥት ቤት እያላቸው ከዚህ ቀደም 18 ሺሕ ብር የቤት ኪራይ፤ ስምንት ሺሕ የትራንስፖርት ድጎማ ይደረግላቸው እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፤ ‹‹አሁንም ለሌላው ሠራተኛ ከ450 እስከ 500 ብር ጨምረው፤ ለራሳቸው ግን በፊት ከነበራቸው 18 ሺሕ ብር የቤት ኪራይ ድጎማ በተጨማሪ ሌላ 18 ሺሕ ብር እንዲሁም፤ ለትራንስፖርት ከነበራቸው የስምንት ሺሕ ብር ድጎማ በተጨማሪ ሌላ 10 ሺሕ ብር ለራሳቸው ጨምረዋል።›› ነው ያሉት።
ሠራተኞቹ ተጨመረ የተባለው ብር የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማሸነፍ እንደማያስችል እየታወቀ ይህ መደረጉ ቅር እንዳሰኛቸው ነው የገለጹት።
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ጌትነት ታደሰ የተነሳው ቅሬታ ሊሆን እንደማይችል ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ ቅሬታ ሆኖ ከተገኘም ጉዳዩ የሚፈታው በአዲስ ማለዳ በኩል ሳይሆን በድርጅቱ በኩል መሆኑን ተናግረዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014



