በፖለቲካው ዓለም ይቅርና በእለት ተእለት ማኅበራዊ ሕይወት የሚገናኝ ሰው ዘላቂ የሚባል ወዳጅ አይኖረውም። እግርና እግር እንኳ ይጋጫሉ እየተባልን ባደግንባት በኢትዮጵያ፣ ወዳጅ ዘላቂ እንደማይሆን በተረትና ብሂል ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ታሪኮች ተምረናል።
የቅርቡን ጠላት በሩቁ እየተባለ ራስን ለማዝለቅ በሚደረግ ሰብዓዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሂደት ጠላትን ከወዳጅ የበለጠ ማቅረብም እንደ አንድ የድል ስልት ይወስዳል። ይህንን የሚረዳ መንግሥትም ሆነ ግለሰብ ሕዝብን ይቅርና አንድ ሠውን በዘላቂነት ወዳጄ ነው ብሎ መተማመን እንደማይችል ይረዳል።
ኢትዮጵያዊያን ሠላም አጥተውና ኑሮ ተወዶባቸው እንዲህ እየተሰቃዩ ባለበት ወቅት መንግሥት ቢያንስ ቅርቡ ካሉ በዝባዦች ሊጠብቃቸው ሲገባ በትዕግስት እንዲጠብቁ እየወተወተ ይገኛል። ወደ ሥልጣን የመጣ ሰሞን የነበረው ድጋፍ አሁን እንደሌለ መረዳት የሚገባው መንግሥት፣ ሕዝብ ወዳጅ ሆኖ የሚቆየው ፍላጎቱ እስከተሟላለት ድረስ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል። ለድጋፍ ብቻ ሲፈለግ የነበረው ኅብረተሰብ፣ ቁርጥ ቀን ሲመጣ ሊያስጥል ቀርቶ መውደቂያን ሊያመቻች እንደሚችል መንግሥት ይረዳ ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
እንደማር በተገኘው ቀዳዳ ሲላስ የኖረው ሕዝብ፣ የጠገበው ሄዶ የተራበ ሲቀየርበት እንደቀደመው በትዕግስት ከመላስ ይልቅ እንደሬት የሚመርበት አዝማሚያ እንደሚያመዝን ከየትኛውም አገር ታሪክ ጭምር መረዳት ይቻላል።
በሠላም ወጥቶ መመለስ ያልቻለ ሁሌ መንግሥትን ሲማፀንና ሲጠብቅ እንደማይኖር ልንረዳ ግድ ይለናል። ማምለጫ ያጣ አማራጭ የመሰለውን በራሱ ተነሳሽነት ከማድረግ ስለማይቆጠብ፣ ማኅበረሰቡ በራሱ አስተሳሰብ ብቻ መመራት የጀመረ ጊዜ ለመመለስም ሆነ ለማስተካከል ማዳገቱ እንደማይቀር እሙን ነው።
በዘራፊ ሌባ የተማረረ የካሜሩን ሕዝብ ሌባ ሲያገኝ መውሰድ ከጀመረው እርምጃ መንግሥታቸው ማላቀቅ እንዳልቻለ ከታሪካቸው ልንማር ያስፈልጋል። ይዞ ሲያስረክብ ፖሊስ እየለቀቀበት የተማረረው ሕዝብ፣ ግለሰብ ዘራፊን እጅ ከፍንጅ ሲይዝ ሌባ እያለ በደቦ የመኪና ጎማ አጥልቆበት በየሰፈሩ በአደባባይ ማቃጠል ጀምሮ ነበር። በዚህ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ምክንያት ሲሰርቅ የተነቃበት ሌባ ሮጦ አስጥሉኝ እያለ ፖሊስ ጣቢያ እስከመግባት ደርሶ ነበር። በዚህ መንገድ መንግሥት መቀነስ ያልቻለውን ሌብነት የኅብረተሰቡ ተግባር እንዳስቆመው ይነገራል። ይህ ተግባር ግን ዘግናኝ እንደመሆኑ ማኅበረሰቡ እንዲተወው ቢጣርም፣ ‹ውጤታማ ነው› በሚል አልፎ አልፎ ሰርቀው የተገኙ ላይ ተግባራዊ እየተደረገ የፍትሕን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ከትቶ ነበር።
በኢትዮጵያ አሁን ሌብነት እንደተበራከተ ማንም ያውቀዋል። ኪስ አውላቂ ያንገበገበው ሕዝብ ይባስ ብሎ ትልልቅ ንብረቱን በጠራራ ፀሐይ ይነጠቅና ይዘረፍ ተያይዞታል። መኪናን የሚያክል ግዙፍ ነገር ሠርቀው የሚሰወሩ ከመበራከታቸው የተነሳ መንግሥትም ማፈላለጉን ችላ ያለው ይመስላል። የተማረረው ሕዝብ ግን ምሬቱ ጣሪያ ነክቶ በቃኝ ያለ ጊዜ መመለሻ እንደማይኖረው አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ከሠሞኑ አንድ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጣ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ ተሰርቆ፣ ባለቤቶች የሚመለተው አካል ጋር ተንከራተው እንዲገኝላቸው ለፍተው ነበር። የተሽከርካሪያቸው ዱካ ከመጥፋቱ በላይ በፍትሕ አካላቱ ላይ የነበራቸውን ተስፋ ያስሟጠጠው የተነገራቸው ተስፋ አስቆራጭ ምክር ነው። የተለመደ ድርጊት እንደሆነና ማግኘት ከፈለጉ ማድረግ የሚጠበቅባቸውን ተግባር የነገራቸው አካል ማንነት አስገርሟቸዋል።
‹ኬላ ላይ ከሚጠብቁ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በግል ተደራድራችሁ የተስማማችሁበትን ከከፈላችሁ ከከተማ እንዳይወጣ ያደርጉላችኋል። እዚሁ ታርዶ ማለትም ተበታትኖ እንዳይሸጥባችሁ ደግሞ ቶሎ ብላችሁ እዚህ ቦታ ሂዱ› ብለው፣ የሚያውቁትን ቦታ ጠቁመው በገንዘብ ተደራድረው እንዲመለስላቸው፣ ራሱ ማስመለስ ከነበረበት አካል ምስጢር በሚመስል መንገድ እንደምክር ተለግሷቸዋል።
ይህ ዓይነት የመንግሥት አካላት ተግባር ኅብረተሰቡ ሲዘረፍበት ፀጥታ ኃይል ጋር ሄዶ ከማሳወቅ እንዲቆጠብና በፍትህ ስርዓቱ እንዳይተማመን እንደሚያደርገው ይታወቃል። ዝም ማለት እንዳለማወቅ ወይም እንደመፍራት ከተወሰደ፣ ሕገወጥ ተግባሩ እየባሰበት እንደሚሄድ በብዙ ምሳሌዎች ማስረዳት ይቻላል። የሳንቲም መልስ እንዲመለስለት ይከራከር የነበረ ሕዝብ፣ አንድና ኹለት ብር ጠይቆ መቀበሉን ሲያቆም ምን እንደሚከተል ለመገመትና ለማወቅ የሥነልቦና ባለሙያ መሆንን አይጠይቅም።
በአንድ ሠፈር ሲነጥቅም ሆነ ሲዘርፍ የተያዘ ሌባ ምን ያህል በያዘው ኅብረተሰብ እጅ ለጉዳት እንደሚዳረግ ያየው ያውቀዋል። ታስሮ በግብራችን እየቀለብነው ወዲያው ከሚፈታ ይልቅ የሚያስተምረው መደብደቡ ነው በሚል፣ ለከት በሌለው ዱላና እርግጫ ሕይወቱ ያለፈ ሰው እንደሚኖር አያጠራጥርም። ያለልክ መደብደብ ብቻ ሳይሆን፣ ሌላውም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲያደርግ መልዕክቱን ማስተላለፍም ጭካኔን እንድንለማመድ አድርጎናል።
ይህን አይነት ተግባር በፊት በፊት ፖሊሶችና የፀጥታ ኃይሎች ራሳቸው እንደሚፈፅሙት ቢታወቅም፣ አሁንም ብሶበት እንደቀጠለ የሚያመላክቱ ማስረጃዎች አሉ። ተጠርጣሪያቸውን ይዞ ማቃጠልም እኛም አገር ከጀመረ ከራርሟል። መጀመሪያዎቹ ፈፃሚዎች ላይ ተገቢ እርምጃ ባለመወሰዱ አሁንም ድረስ በስፋት ሲፈፀም ይስተዋላል።
በየሠፈሩና በየአካባቢው በስርዓት አልበኞች ከሚፈፀም የወንጀል ተግባር የበለጠ አሳሳቢ መሆን የሚገባው፣ በመንግሥት አካላት አሊያም እንደመንግሥት ሆነው ሕዝቡን በመዝረፍ እንዲማረርና እንዲያምጽ የሚያደርጉት ጉዳይ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች። ሕዝብ ደኅንነቱንና ንብረቱን እንዲጠብቅለት የለፋበትን የሚገብርለት መንግሥት፣ ኃላፊነቱን ካልተወጣ፣ ሕዝቡ ራሱን መከላከል እንደሚጀምር ሊታወቅ ይገባል። ሕግና ሥርዓት ስለማይገዛውም እንዲህ አድርግ ለማለትም አስቸጋሪ ይሆናል።
ከሰሞኑ ሻሸመኔ አቅራቢያ አምስት ሆነው የሚጓዙ መንገደኞች ላይ ተከሰተ የተባለው ለኹላችንም አስተማሪ ሊሆን ይገባል። ግለሰቦቹ ከከተማው እንደወጡ በ300 ሜትር ርቀት ውስጥ ኹለተኛ ኬላ ላይ እንዲቆሙ ከተደረጉ በኋላ የክልልና የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎችን ዩኒፎርም በለበሱ ሰዎች ይፈተሻሉ። አንድም ነገር ሳይቀር በመበርበር ከስልክ ጀምሮ ያላቸውን ውድ ንብረት በሙሉ ካስቀሩ በኋላ መሬት አስተኝተው ከደበደቡዋቸው በኋላ ሀብታቸውን አስቀርተው እንዳስኬዷቸው ከመካከላቸው የነበረ ሰው እማኝነቱን ሰጥቷል። ግለሰቡ ያሳዘነው ሀብቱን መዘረፉ ሳይሆን አገሩን ማጣቱ እንደሆነ ያሰፈረው መልእክት ለመንግሥትም ሆነ ለማንም ኢትዮጵያዊ አሳፋሪ መሆኑ ግልጽ ነው።
በሌላ በኩል፣ እያደር በሚጨምረው የኑሮ ውድነት ሳቢያ ያልተገባ ተግባር ፈፅመዋል የሚባሉ ላይ እርምጃ እንደተወሰደ የተነገረው ለይስሙላ እንደሆነ የወጣ ዘገባም ተሰምቷል። ይህ አይነት ተግባር የመንግሥትን ታማኝነት ይበልጡኑ አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ከመዋሸት ይልቅ ጭራሹኑ ዝም ማለት እንደሚሻል አዲስ ማለዳ ታምናለች።
የሕዝብ ምሬት ሲበዛ ‹እሳት እንደበዛበት ሽሮ› ገንፍሎ መውጣቱ አይቀሬ ነው። በትምህርት ፖሊሲው ምክንያት፣ በፀጥታ መደፍረስ ሳቢያ እንዲሁም ሰሞኑን በደብረማርቆስ የተካሄደውን የኑሮ ውድነትን የተመለከተ የተቃውሞ ሠልፍ አይነት በየቦታው መበራከቱ አይቀርም። ሰላማዊ የሆኑ ተመሳሳይ ሠልፎች እንደ ሱዳን እየበዙ ትኩረት የሚያጡ ከሆነም፣ ሰላማዊነታቸው ቀርቶ አጥፊዎች ስለሚሆኑ ለማንም እንደማይጠቅሙ ተረድቶ አስቀድሞ መሥራት ያለበት መንግሥት መሆኑን ማመልከት ያስፈልጋል።
‹‹ወዳጅህ ማር ቢሆን ጨርሰህ አትላሰው›› የተባለው የሚላሰው እንዳይመር ነውና፣ መንግሥት ለራሱ ሲል ሕዝብን የምታማርር ትንሽ የተባለችን ተግባር ሳይቀር አቅም በፈቀደ መጠን ለማስተካከል መጣር ይጠበቅበታል። “እናቴ ምነው በመሐረቡ ጊዜ በቀጣሽኝ ኑሮ” ብሎ እንደተቆጨው ሰው፣ ዘግይቶ ከመከራ ከመማር አገርንም ለጥፋት ከመዳረግ፣ አስቀድመን ኹላችንም ብናስብበት መልካም ነው ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014



