የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ከ2014 የትምህርት ዘመን ማብቂያ ጀምሮ መታገዱ ተገለጸ

0
723

ከ20 ዓመታት በላይ ሕጋዊ እውቅና ሳይኖረው ለመንግሥት የሚጠበቅበትን ግብር ሳይከፍል ሲያስተምርና ከፍተኛ ገቢ ሲሰበስብ መኖሩ የሚነገርለት የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት፣ ከሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ጀምሮ ማስተማር እንዲያቋርጥ መታዘዙን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለትምህርት ቤቱ በጻፈው ደብዳቤም፣ ጥር 24/2014 ቀን ከትምህርት ቤቱ ጋር ባደረገው ውይይት ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የበርካታ አገር ዜግነት ያላቸው ተማሪዎችን የትምህርት ክፍያ እያስከፈለ በማስተማር ላይ እንዳለና፣ ይህም ከማኅበረሰብ ትምህርት ቤት መርህ ያፈነገጠ የትምህርት ቤቱን ሕጋዊ ማንነት አሻሚ እንዳደረገው በወቅቱ ስምምነት ላይ መደረሱን አውስቷል።

ስለሆነም፣ ትምህርት ቤቱ የተሰጠውን ትዕዛዝ ችላ በማለት ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማያደርግ መግለጹን ተከትሎ፣ በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደሌለበት ትምህርት ሚኒስቴር በመወሰኑ፣ የ2014 የትምህርት ዘመን እንዳበቃ የካምብሪጅ ስርዓተ ትምህርት የሚጠቀመው የእንግሊዘኛ ትምህርት ክፍል፣ ትምህርት የመስጠት ምንም ሕጋዊ ፈቃድ ስለሌለው ለሚቀጥለው ዓመት ተማሪዎችን ማስተማር እንደማይችል ከወዲሁ አውቆ ተማሪዎችን እንዲያሰናብት ሲል ትምህርት ሚኒስቴር መጋቢት 21/2014 ቀን በጻፈው ደብዳቤ አሳውቋል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የትምህርት ቤቱ መምህር፣ ትምህርት ሚኒስቴር ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢ መሆኑን አንስተው፣ እስከዛሬ ኖሮ አሁን ላይ መተላለፉ ግን ትምህርት ሚኒስቴርን የሚያስወቅስ ነው ብለዋል። ትምህርት ቤቱ ከ20 ዓመታት በላይ ያለ እውቅና እንዲሁም ግብር ሳይከፍል “ሲዘርፍ” በመኖሩም እስከ አሁን ለፈጸመው ከፍተኛ ወንጀል ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የትምህርት ቤቱ የሰው ኃይል ኃላፊ የነበሩት ወሰን ውበት፣ የትምህርት ቤቱ እንግሊዘኛ ክፍል (English section) ከመጭው ሰኔ ወር በኋላ በትምህርት ሚኒስቴር መታገዱን ገልጸው፣ በዜግነት ግሪካዊ የሆኑት የትምህርት ቤቱ ኃላፊ ከነልጃቸው በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚሠሩት የማጭበርበር ድርጊቶች መኖራቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዚህም ይህን የሚያሳዩ እና ወደ ሕግ የሚቀርቡ ሰነዶች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ትምህርት ቤቱ ከእንግሊዘኛ ክፍሉ በተጨማሪ በግሪክ ክፍሉ (Greek section) በሚማሩ ተማሪዎች ላይም በደል እንደሚፈጽም ነው ያሳወቁት። እነዚህ ተማሪዎች የድሃ ልጆች በመሆናቸውም የሚንከባከባቸው ሞግዚት እንደሌላቸው፣ ምግብ ጠዋት አንድ ሰዓት እና ሰባት ሰዓት እንደሚሰጣቸውና እንደሚራቡ፣ ብሎም ወንዶችና ሴቶች በአንድ ላይ እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ ይህ መሆኑ በአዳሪ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የሥነልቦና ጫና እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይ ሰኞ ቀን አዳሪ ተማሪዎች ጋር የጫት ፍርፋሪ፣ ሲጋራና ጥቅም ላይ የዋለ ኮንዶም እናገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በተከታታይ ስለትምህርት ቤቱ የሚነሱ ቅሬታዎችን እና ከትምህርት ሚኒስቴር በኩል የሚገኙ ምላሾችን በማካተት ስትዘግብ መቆየቷ ይታወሳል። አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በተከታታይ በሠራቻቸው ዘገባዎች ትምህርት ቤቱ ሕጋዊ እውቅና ሳያገኝ ከ20 ዓመት በላይ ቢያስተምርም ለመንግሥት መክፈል የሚገባውን ግብር አልከፈለም ስትል ዘግባለች።

በቀጣይም፣ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተማሪዎች እና መምህራንን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ እንዲሁም ትምህርት ቤቱ እስከ አሁን ለሠራው ተገቢ ያልሆነ ሥራ ተጠያቂ ለማድረግ በሚመለከታቸው አካላት የሚሠሩ ሥራዎች ካሉ መረጃዎችን አጠናቅራ የምታቀርብ ይሆናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here