በኢትዮጵያ በግል ተቋማት ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የኩላሊት ንቅለ ተከላ አገልግሎት ሊጀምር መሆኑን ‹‹ሊያና ሄልዝ ኬር›› ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ኃላፊዎች ለአዲስ ማለዳ አሳወቁ።
ተቋሙ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና አገልግሎቱን በቀጣይ መስከረም ወር 2015 በይፋ የሚጀመር መሆኑን የሊያና ሄልዝ ኬር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ግርማ አባቢ ተናግረዋል።
የንቅለ ተከላ መስጫ ተቋሙን ለማቋቋም ያነሳሳቸው ዋነኛ ምክንያት የኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) አገልግሎት ለሕሙማኑ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ባለመቻሉ በንቀላ ተከላው ችግሩን ለመቅረፍ ታሳቢ በማድርግ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል።
በተያያዘም ሙሉ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ እስከ አሁን በሆስፒታሉ ስር ከሚገኙ 100 ሠራተኞች በተጨማሪ ከ70 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ነው የተባለው። አገልግሎቱን ለማቋቋምም 80 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተበጀተም ጠቅሰዋል።
የተቋሙ የገበያና የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ አለበል ተፈራ በበኩላቸው፣ በግል ድርጅት ደረጃ ፈር ቀዳጁ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ነገር፣ ከተማ ውስጥ የኩላሊት ሕሙማንን ለብቻቸው አድርጎ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ክፍል ማካተቱ ነው ብለዋል።
አክለውም የንቅለ ተከላ አገልግሎቱ የሚሰጠው በአዲስ አበባ አያት አካባቢ ደራርቱ አደባባይ አጠገብ በሚገኘውና ለኮቪድ ሕሙማን ማዕከል በመሆን አገልግሎት ሲሰጥበት በነበረው ያኔት ሆስፒታል ነው ብለዋል።
ተቋሙ አሁን ባለበት ደረጃ 220 አልጋዎች እንዳሉትና ወደ ሃረር፤ ጅማ፤ ያቤሎ እና ሌሎች ከተማዎችም አገልግሎቱ እንዲስፋፋ ለማድረግ በዕቅድ ላይ መሆናቸውን አለበል ጠቁመዋል።
የኮቪድ ማዕከል ሆኖ አገልግሎት ሲሰጥ በቆየው ሆስፒታል ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ለመስጠት ‹‹ከሕንድ አገር ሞጁላር ሩም ኦ.አር›› እየተመረተ እንደሚገኝ ተመላክቷል። በተያያዘም፣ ምርቱ ተጠናቆ ወዲያውኑ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባና በሕንድ ሙያተኞች የንቅለ ተከላው አገልግሎት እንደሚጀመር አለበል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ይህን ለማድረግ ሕጉ አለመፍቀዱን ያነሱት አለበል ጉዳዩን በተመለከተ፣ የሕግ ማሻሻያዎች ለማድረግ ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በጋራ እየሠራን ነው ብለዋል።
በባንክ በኩል የሚከናወነው የዶላር ፍቃድ በሂደት ላይ ከመሆኑ ውጭ ሁሉም ነገር መዘጋጀቱም ተጠቅሷል። ‹‹ሁሉም ነገር ተዘጋጅቷል›› ያሉት አለበል፤ ለአብነትም ሲቲ ስካን፤ አልትራ ሳውንድ፤ ዘመናዊ ላቦራቶሪ፤ ፊዞዮቴራፒ፤ ስምንት ሜካኒካል ቬንትሌተሮች እና ሌሎችም መሣሪያዎች ተሟልተዋል ብለዋል።
በሌላ በኩል፣ ሊያና ሄልዝ ኬር ለኩላሊት ሕሙማምን የንቅለ ተከላ አገልግሎት ከመስጠቱ በተጨማሪ፣ ስድስት የዲያሌሲስ (ኩላሊት እጥበት) አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ማሽኖችም እንደተዘጋጁ አለበል ጠቁመዋል።
የአንድ ዲያሌሲስ ዋጋ ሦስት ሺሕ ብር እንደሆነና፤ በሳምንት ሦስት ጊዜ የዲያሊሲስ ክትትል የሚያደርጉ የኩላሊት ሕሙማን በወር 36 ሺሕ ብር ስለሚያስፈልጋቸው ሕክምናቸውን ለመከታተል የሚቸገሩ ሕሙማን እንዳሉ አውስተዋል አሉ። ሊያና ሄልዝ ኬርም የአንድ ሺሕ ብር ቅናሽ በማድርግ አገልግሎቱን እንደሚሰጥ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገልጸዋል።
ሊያና ሄልዝ ኬር ከተመሠረተ 10 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በሐዋሳ ከተማ ክሊኒክ በመክፈት ለ25 ሺሕ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014



