ዕረቡ ሚያዚያ 12 (አዲስ ማለዳ) የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ለኩላሊት ህመምተኞት ኹለገብ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችለውን ህንፃ ለመገንባት 1 ሺህ 410 ካሬሜትር ቦታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መቀበሉን አስታወቀ።
ድርጅቱ የኩላሊት ህሙማንን በገንዘብ በመደገፍ ከሚሰራው ሥራ በተጨማሪ፤ የራሱን የሆነ ኹለገብ የኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) አገልግሎት መስጫ ማዕከል እና በቂ የሆነ የገቢ ማሰባሰቢያ ተቋም ለመገንባት ነው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶው ቡልጋሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቦታውን የተቀበለው።
የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት በአሁኑ ወቅት ዋና ጽ/ቤቱ በዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ አሁን የተቀበለው ሥፍራ ላይ ህንፃው ሲገነባም፤ ጽ/ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ወደ አዲሱ ህንፃ እንደሚዘዋወር የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
“ይህን ቦታ ያለምንም ክፍያ ከመንግሥት ማግኘታችን መንግሥት ለኩላሊት ህመም የሰጠውን ትኩረት ያሳያል” ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ህብረተሰቡም ለኩላሊት እጥበት ማዕከሉ ግንባታ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ከመንግስት በተገኘው በዚህ ቦታ ላይ፤ ከ17 እስከ 20 ወለል የሚደርስ ህንፃ ከ4 እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ ለመገንባት መታቀዱን ሰለሞን የገለፁ ሲሆን፤ እስከዛው ግን በቀላሉ ሊፈርሱ የሚችሉ ተገጣጣሚ ቤቶችን በመገንባት ለህመምተኞች አፋጣኝ የዲያሊሲስ ህክምና ለመስጠት መታቀዱንም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም፤ ህንፃውን ለማስገንባት የተለያዩ መንግስታዊና የግል ተቋማት ለድርጅቱ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልፀው፤ እንደ ምሳሌም በአገራችን የሚገኙ ባንኮች የህንፃውን አንድ አንድ ወለል እንዲሰሩ ጥያቄ ቀርቦ፤ በአሁኑ ሰዓት ከአንዳንዶቹ ባንኮች ቀና ምላሽ እየተገኘ መሆኑንም ጨምርው ገልፀዋል።
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




