ዕረቡ ሚያዚያ 12 (አዲስ ማለዳ) በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አምባሳደር ፍስሃ ሻውል የኢትዮጵያን ሁኔታ በሚመለከት ከአምስት የአፍሪካ አገራት ለተውጣጡ የጦር መኮንንች ገለፃ አደረጉ።
የጦር መኮንኖቹ በታንዛኒያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ስልጠና እየተከታተሉ ያሉ ሲሆን፥ ከናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ፣ ዝምባብዌና ሩዋንዳ የተውጣጡ ናቸው።
ለቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና አሁናዊ ሁኔታ ላይ ገለፃ ያደረጉት አምባሳደር ፍስሃ ሻውል ፥ ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናት የተሻገረ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ታሪክ እንዳላት አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በኹለትዮሽና በባለ ብዙ ወገን መድረኮች ያላትን ተሳትፎም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በአሁን ጊዜ እየደረሰባት ያለባትን ኢ-ፍትሃዊ ጫናዎች በሚመለከት ለጦር መኮንኖቹ አባላት ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደሩ ፥ የኹላችንም እጣ ፈንታ ተመሳሳይ በመሆኑ ይሄን ድርጊት ለመቃወም አፍሪካዊያን በህብረት መቆም አለብን ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማንኛውንም የተፋሰሱ አገራት የማይጎዳ የልማት አጀንዳ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፤ ውሃውን በሚመለከት ዘመን ያለፈበትን ኢ-ፍትሃዊ የቀኝ ገዢዎች ስምምነት በመተው የተፋሰሱ አገራት በትብብር መስራትና መጠቀም እንደሚገበ አስገንዝበዋል።
የጦር መኮንኖቹ አገሮቻቸው ከኢትዮጵያ ጋር መስራት በሚችሉት የትብብር ጉዳዮች ላይ ከአምባሳደር ፍስሃ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n









