የኃይል እጥረት እንዳያጋጥም ወደ ሱዳንና ጅቡቲ ኤክስፖርት ሲደረግ የነበረው ኃይል በግማሽ እንዲቀንስ ተደርጓል
ሐሙስ ሚያዚያ 13 (አዲስ ማለዳ) በትንሳኤና በኢድ-አልፈጥር- ረመዳን በዓላት የኃይል እጥረት እንዳያጋጥም አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል እንዳስታወቀው፤ በረመዳን ጾም የአፍጥር ዝግጅት፣ በትንሳኤ በዓልና በኢድ-አልፈጥር – ረመዳን በዓል የኃይል እጥረት እንዳያጋጥም የኃይል ማመንጫዎች፣ ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
ያለፉትን ሦስት ዓመታት የበዓላት የኃይል ፍላጎት እና አቅርቦት መነሻ በማድረግ፤ ካለፈው ዓመት በ2 ነጥብ 7 በመቶ ብልጫ ያለው ኃይል ለማቅረብ የማመንጫ ጣቢያዎች ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም ማዕከሉ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም የኃይል እጥረት እንዳያጋጥም ለማድረግ ወደሱዳንና ጅቡቲ ኤክስፖርት ሲደረግ የነበረው ኃይል በግማሽ እንዲቀንስ መደረጉን አስታውቋል፡፡
የኃይል ተጠቃሚው ፍላጎትን ተከትሎ በሥርጭት መስመሮች ላይ ሊያጋጥም የሚችለውን የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር ለመፍታት፤ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ውይይት ተደርጎ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ማዕከሉ ገልጿል፡፡
የግሪድ ሲስተሙን በማረጋጋት ከፍተኛ ሚና በሚጫወቱት በጊቤ 3 እና በበለስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ በልዩ ትኩረት ዝግጅት መደረጉም ታውቋል፡፡
በኃይል ማመንጫዎች፣ በማስተላለፊያ መስመሮችና በማከፋፈያ ጣቢያዎች ከተደረገው ዝግጅት በተጨማሪ ማንኛውም ዓይነት የቴክኒክ ችግር ቢያጋጥም ችግሩን ሊፈታ የሚችል የአስቸኳይ ጥገና የቴክኒክ ቡድን መዋቀሩንም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
ህብረተሰቡም የኃይል አቅርቦቱን ሊያስተጓጉሉ የሚችል የመሰረተልማት ሥርቆት በሚመለከትበት ጊዜ በአቅራቢያው ለሚገኝ የህግ አካል እንዲጠቁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥሪውን አቅርቧል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




