የመገናኛ ብዙኃን ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ

0
904

ሐሙስ ሚያዝያ 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአገራችን የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እና ጋዜጠኞች ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች እና ጋዜጠኞች ጋር በጋራ መስራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ የመጀመሪያውን የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በውይይት መድረኩ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን ቀጣይ አገራዊ አቅጣጫዎች የሚያመላክት ብሎም፤ የመገናኛ ብዙሃን ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት መሰረት የሚጣልበት መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እያከናወናቸው የሚገኙ ሥራዎችን በመድረኩ ያብራሩ ሲሆን፤ የኮሚሽኑ ሥራዎችም በአራት አንኳር ምዕራፎች ተከፍለው መቀመጣቸውን አስረድተዋል።

እነርሱም የቅድመ ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የሂደት እንዲሁም የትግበራና ምዕራፍን የማገዝና የመከታተል ምዕራፎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም ኮሚሽኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ፕሮፌሰር መስፍን፣ በዚህም የእርስ በእርስ ትውውቅ፣ የአባላት የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅትን የመለየት፣ ኮሚሽነሮች የኮሚሽኑን አዋጆችንና የምክክርን ፅንሰ ሀሳብ፣ ዐውድ ተኮርና ተግባራዊ ትርጉም እንዲረዱ እና እንዲተገብሩ የማስተዋወቅ እና የማስረዳት ሥራ፣ የሎጅስቲክ ሥራዎች፣ ለአገራዊ ምክክሩ የክልል ጽ/ቤቶች የማደራጀት ሥራዎች እንዲሁም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የአጋነት እና የውይይት ሥራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ማድረግ መጀመሩን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ አሁንም ከመገናኛ ብዙኃን አመራሮች ጋር የሚደረገው ምክክር የዚሁ አንድ አካል መሆኑን ገልፀዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነሮች፣ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተገኙ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እና ጋዜጠኞች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።

ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በመድረኩ ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነሮች መልስ ሰጥተውበታል።
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here