ሐሙስ ሚያዚያ 13 (አዲስ ማለዳ) ባለፉት 9 ወራት በድህረ ፈቃድ ክትትል ከተደረገባቸው 912 ድርጅቶች ውስጥ 96 ድርጅቶች በህግ አግባብ እየሰሩ ባለመሆኑ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሚኒስትሩ የገበያና ፋብሪካ ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር ተከተል ጌቶ እንደተናገሩት፤ በ71ዱ የንግድ ድርጅቶች ላይ የንግድ ፈቃድ እገዳና እሽጋ እንዲሁም በ25ቱ ድርጅቶች ላይ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የመስጠት እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
በተጨማሪም በ344 ድርጅቶች ላይ በፋብሪካዎች እና በገበያ ቦታዎች በተደረገ የኢንስፔክሽን ሥራ ከ30 የምርት አይነቶች ላይ 195 ወካይ ናሙናዎች መወሰዳቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ከተወሰዱት ናሙናዎች ውስጥም 86 ድርጅቶች የተቀመጠውን የጥራት ደረጃ ሟሟላታቸው ተረገግጧል። የ48 ድርጅቶች ምርት ጥራት ደግሞ ከደረጃ በታች በመሆኑ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡
ከ48ቱ ድርጅቶች ውስጥ 31ዱ አምራች ፋብሪካዎች ከማምረት ሂደታቸው እንዲታደጉ ተደርጎ የማስተካከያ ሥራዎች ከሰሩ በኋላ በድጋሚ ምርቶቻቸው በላቦራቶሪ ፍተሻ ተረጋግጦ ወደ ሥራ እንዲመለሱ መደረጉን፣ ለ5 ፋብሪካዎች የጹሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም በ12 አስመጭዎች ላይ የንግድ ፈቃድ እገዳ እርምጃ መወሰዱን ተከተል አክለው ገልጸዋል።
ኹሉም አስመጪዎችና እና አምራቾች በህብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ምርቶችን ከማምረት እና ከማሰራጨት በመቆጠብ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



