የዓመት ፈቃድ ለሥራ

0
957

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ሥራ የጀመርኩት አንጋፋ በሆነ አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ነው። የሥራ ቡድኑን እንደተቀላቀልኩ ያገኘኋቸው በእድሜ ገፋ ያሉና እንደልጃቸው የሚመለከቱኝን እናቶችን ነበር። ብርቱና ታታሪ ሠራተኞች ናቸው። ጠዋት ቀድመው ይገባሉ፤ ማታ የሰዓት ፊርማ ፈርመው፣ መንገዱ ቀለል እስኪል ታግሰው ወደቤታቸው ይገሰግሳሉ። ያኔ እንደ አሁኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የትራንስፖርት አገልግሎት አልነበረም።

ታድያ በዓል ሲሆን አልያም ሲዳረስ ከሥራ ፈቃድ ጠይቀው ለተወሰኑ ቀናት ይቀራሉ። አያት ለመሆን ከሚንደረደሩ የልጅ እናት ከሆኑት በቀር፣ ሌሎቹ በአብዛኛው የበዓል ሰሞን ነው ፈቃዳቸውን ወስደው ከሥራ ፋታ የሚወስዱት። አልያም ልጃቸውን ለማረስ ነው። ሲከፋ ደግሞ ሐዘን ሲያጋጥም።

የሚገርመኝና አንዳንዴም ‹‹እረፍት ባትወጡ አይሻልም ነበር?› ብዬ እንድጠይቃቸው የሚያስገድደኝ ታድያ፣ እረፍት ወጥተው ግን አለማረፋቸው ነው። የዓመት ፈቃድ ጠይቀው ከሥራ ቦታ ሲቀሩ፣ ሙሉ ጊዜያቸውን ለቤት ውስጥ የበዓል ሰሞን ሥራ ያውሉታል።

የበዓሉ ዋዜማ፣ እለት አንዳንዴም ማግስት ‹እንኳን አደረሳችሁ! መልካም በዓል!› ለማለት ስልክ ስደውል፣ በሥራ ተጠምደው እየተንጎዳጎዱ እንደሆነ ይነግሩኛል። እንደውም አንዳንዴ እረፍታቸውን ሳያውቁት አልቆ፣ የባሰ ደክሟቸውና ተጨማሪ ፈቃድ መጠየቅ ቢቻል እየተመኙ ወደ ሥራ ይመለሳሉ።

እረፍት ምን ማለት እንደሆነ ግራ የሚገባኝ ይሄኔ ነው! ለሴት ሠራተኞች የዓመት ፈቃድ ወይም እረፍት ማለት የቤት ውስጥ ሥራን ሙሉ ለሙሉ በትኩረት መሥራት እንደማለት ነው ብዬ እንዳስብም ሆኛለሁ። በእረፍት አካልንና አእምሮን ማሳረፍ ይጠበቃል፣ እኔ የማውቃቸው እነዛ ሴቶች ግን በእረፍት ቀናቸው ከወትሮው በተጨማሪ ብዙ ሥራን ለመሥራት ይገደዳሉ።

በእርግጥ እንደ አገርም እንደ ማኅበረሰብም ካለንበት የምጣኔ ሀብት ደረጃ አንጻር እንደውም እረፍት ፈጽሞ የሚያስፈልግ ነገር አይደለም። ግን ደግሞ ሰው ውጤታማ ሥራን ሊሠራ የሚችለው በተወሰነ መንገድ አእምሮውንም ሆነ አካሉን ከዝለት ማስታገስና ማደስ ሲችል እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ሲነገር ሰምቻለሁ። የጥሞና ሰዓት፣ የአርምሞ ጊዜ፣ መንፈስንም ማደሻ ሁኔታ ያስፈልጋል።

እነዛ ሴቶች ግን ያንን አልጠየቁም። እንደውም ሲያማርሩና የቤቱን ሥራ ሲረግሙ ሰምቼ አላውቅም። አልፎም አንዳንዴ ፈቃድ ወስደው ቤት ውስጥ ያለውን ሥራ እስኪሠሩ የሚናፍቁ ይመስላሉ።

‹ቤቴ ምን እንደመሰለ! ገብቼ ሳሎኑን እስካጸዳው፣ ኩሽናውን እስካድሰው› ብዙ ብዙ ይላሉ። እኔም እንደነሱ እንድሆን ተመኝቼ አውቃለሁ። እንደ እነሱ ፈቃድ ወስጄና እረፍት ወጥቼ በሥራ ማሳለፍን አይደለም። ይልቁንም በዛ ልክ በአደባባይም በጓዳም ውጤታማ ለመሆን አለመሰልቸትን።

ዛሬም በዓል ሲደርስ እነዛ ፈቃድ ወስደው የቤታቸውን ሥራ የሚሠሩትን ሴቶች አስባለሁ። እናንት ውድ እናቶች! እንኳን አደረሳችሁ!
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here