የትምህርት ጥራት ከታች ወደ ላይ ወይስ ከላይ ወደ ታች?

0
1976

ከሚመጣው 2015 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ባሳለፍነው መጋቢት 26/2014 አሳውቋል።

በተያያዘም ‹‹በቀጣይ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡ የመውጫ ፈተናዎች ተገቢውን ዕውቀት፤ ክህሎትና ስብዕና ያሟላ ምሩቅ ለማፍራት እንደሚያስችልና መውጫ ፈተናው በምሩቃን ፕሮፋይል መሠረት ብቁና ተወዳዳሪ ምሩቃንን በማውጣት ጥራት ያለውና በአግባቡ የሠለጠነ የሰው ኃይል ለገበያው ለማቅረብ እንደሚያስችሉ›› ነው የተጠቆመው።

ይህን ተከትሎም በርካታ አካላት ብቁና ተወዳዳሪ ምሩቃንን ለማፍራት የትምህርት ጥራትና የመውጫ ፈተና መስጠት ከታች ወደ ላይ ወይስ ከላይ ወደ ታች የሚል ጥያቄ አዘል ትችት እያነሱ ይገኛሉ።

የሆነው ሆኖ ትምህርት ሚኒስቴር የመውጫ ፈተናውን በመስጠት ተወዳዳሪ ምሩቃንን ለማፍራት ማቀዱ ይበል የሚያሰኝ አተያይ ነው። ነገር ግን በብዙኀኑ በኩል ደግሞ በርካታ ቅሬታዎችን አሳድሯል። ‹ብቁና ተወዳዳሪ ምሩቃንን› ለማፍራት ያስችላል በተባለው አካሄድ፣ ለሥራ የሚወዳደሩ ምሩቃንን የመቀነስ ውስጠ ወይራ እንዳለውም ቅሬታቸውን የሚወነጭፉ አካላት አልጠፉም።
በእርግጥም ይህ ውሳኔ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለመቀነስም የታለመበት ይመስላል የሚሉት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሙሃባው በጎ ናቸው።

ብዙኀን የማኅበረሰብ ክፍል ልጆቹን የሚያስተምረው ከዓመት አንድ ጊዜ ገቢ ለማግኘት ሳይሆን ልጆቹ ትምህርታቸውን አጠናቀውና ሠራተኛ ሆነው የወር ደመወዝተኛ እንዲሆኑ በማሰብ ነው። ነገር ግን ተመራቂ ተማሪዎች ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሲመጣ ይስተዋላል።

ታዲያ ማኅበረሰቡም ሆነ እናትና አባት ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ቀንበር ለመውጣት እጆቻቸውን ዘርግተው ከልጆቻቸው የሚጠብቁት የሥራ ቅጥር መገኘት እንደ ሰማይ ከራቀ ሰንበትበት ብሏል።
ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንመለከት እንኳ፣ የ2014 በጀት ዓመት እቅድን በተመለከተ መንግሥት ውይይት ባደረገበት ወቅት፣ ለምሩቃን የሥራ ዕድል ያለው ቦታ የጠበበ እንደሆነ መነሳቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ከዚህ ቀደም መንግሥት የ2014 የበጀት ዓመት ዕቅዱን አስመልክቶ ባደረገው በዛው ውይይት፣ ከአንዳንድ አስፈላጊ ቦታዎች ውጭ በበጀት ዓመቱ አዲስ ቅጥር አልፈጽምም ማለቱ የሚታወስ ነው።
በአገራችን ኢትዮጵያ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዜጎችን ለሥራ በማሰማራት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙ ተቋማት ናቸው።

የመንግሥት ተቋማት በየዓመቱ በርካታ ምሩቃንን በመቅጠር ብዙውን ዜጋ አቅፈው በመያዛቸው ቢታወቁም፣ የሥራ አጡን ብዛት በተፈለገው ልክ ግን መቀነስ አልተቻለም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ መንግሥት ‹እንደተለመደው ቅጥርን አላስተናግድም› ከማለቱ ጋር ተያይዞ የሥራ አጡ ዕጣፈንታ ምን ይሆን? የሚል ጥያቄ እየተነሳ እንደነበርም አዲስ ማለዳ ስትዘግብ ቆይታለች።

አሁንም ስጋቱ የቀጠለ ይመስላል። የ2015 የዩንቨርሲቲ መውጫ ፈተና መሰጠቱ የጥቂቱን ፍላጎት ቢያሟላ እንጂ የብዙኀኑን ምሩቃን ሥራ የማግኘት ዕድል የሚያከስም እንደሚሆን ከወዲሁ ስጋት አሳድሯል።

ይህን በተመለከተም ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናው ሊሰጥ መሆኑ ጠቃሚ ጎን ቢኖረውም፣ ተማሪዎቹ የመውጫ ፈተናውን ማለፍ የማይችሉበት አጋጣሚ ቢፈጠር ሥራ የማግኘት ዕድላቸው የላላ እንደሚሆን ቅሬታ እያነሱ ይገኛሉ።

ከታች ስላለው የትምህርት ሂደት በጥቂቱ
ወደ ዩኒቨርሲቲ ከማቅናታችን በፊት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያለውን የትምህርት ሂደት ስንቃኝ ተማሪዎችን ወደ ቀጣዩ ክፍል ማሳለፍ እንጂ ብቁ የማድረጉ አሠራር ትኩረት ተነፍጎት ይስተዋላል።

መንግሥት ከታች ላሉት የትምህርት ተቋማት አስተዳዳሪዎች ያወረደላቸው አንድ መመሪያ አለ። ይኸውም ተማሪዎችን አብቅቶ ማሳለፍ እንጂ መጣል እንደማይቻል ነው። ይህ አሠራር ዋነኛ ዓላማው በትምህርታቸው ደከም የሚሉ ተማሪዎችን ከመጣል ይልቅ የክለሳ ትምህርት በመስጠት ውጤታቸውን እንዲያሻሽሉ አድርጎ ወደ ቀጣዩ ክፍል ማሸጋገር ነው።

ውሳኔው ከቃል በዘለለ ተግባራዊ ቢደረግ ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ከለጋነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ማፍራት የሚያስችል ማራኪ አሠራር መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።

ይህን ተከትሎ ግን ከታች የሚገኙ የትምህርት ተቋማት አስተዳዳሪዎች ስንት ተማሪ አሳልፌ ከተጠያቂነት ዳንኩኝ እንጂ፣ ስንት ተማሪ አበቃሁ የሚል አሠራራቸው የደከመ መሆኑ ይነገራል። ይህ ክስተት የሚስተዋለው በተለይም በገጠሩ ክፍል በሚገኙ የትምህርት ተቋማት እንደሆነም ይሰማል።

በመሆኑም ተማሪዎቹ ለማካካሻ ትምህርት ሲጠሩ የመምጣት እድላቸው እምብዛም ነው። ለዚህም ምክንያቱ በቤተሰቦቻቸው በኩል ለትምህርት ያለው አመለካከትና በቤታቸው ውስጥ ያለው የሥራ ጫና ነው።

በሌላ በኩል በበርካታ ተማሪዎች አንደበት ‹‹ተመርቆ ማን ሥራ ያዘ!? ትምህርት ቤት የምሄደው እኮ ጊዜ ለማሳለፍ ነው›› የሚል ዓላማን የሚገድልና የሕይወትን ጣዕም የሚያጠፋ ወሬ በተደጋጋሚ ይነገራል።

ታዲያ ብዙ ተማሪዎችን ወደ ቀጣዩ ክፍል አለማሳለፍ ያስተቸናል በሚል ስጋት አንዳንድ ከታች ባሉ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተማሪዎች ዝም ብለው ወደ ቀጣዩ ክፍል የሚያልፉበት አጋጣሚ እንዳለ የተማሪ ወላጆች በተለያዩ ስብሰባዎች ሲያነሱ ይስተዋላሉ።

በሌላ በኩል በጦርነቱ ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ ተማሪዎች ከሌሎች ጋር እንዴት እኩል ሊወዳደሩ ይችላሉ የሚል ቅሬታም እየተነሳ ነው።
በተለይም ከትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች በጦርነቱ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው እንደተመለሱና ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ቢመደቡም የትምህርት ገበታቸው ሲሸራረፍ እንደቆየ ይታወቃል።

በመሆኑም ተማሪዎቹ የመውጫ ፈተናውን ከሌሎች ተማሪዎች ጋር እኩል መፈተናቸው ፍትሃዊ እንደማይሆን ቅሬታ እያነሱ ነው።

ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን አቋርጠው ስለመምጣታቸው ትምህርት ሚኒስቴር በወቅቱ ከዓዲግራት 2 ሺሕ 355፤ ከአክሱም 2 ሺሕ 992፣ ከመቀሌ 3 ሺሕ 668፣ ከራያ 1 ሺሕ 149 በድምሩ 10 ሺሕ 164 ተማሪዎች እስከ ነሐሴ 06/2013 በሠመራ ዩኒቨርሲቲ በኩል ወደ አዲስ አበባ እንደገቡ ገልጾ ነበር።

ተመላሽ ተማሪዎቹ የትምህርት ገበታቸው እየተሸራረፈባቸው መሆኑን በተደጋጋሚ ቢያነሱም፣ ከብዙ ቆይታ በኋላ ሰላም ወዳለባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበዋል። ይህ ቢሆንም ግን የተመረቁበት ጊዜያዊ ሠነድ የሚሰጣቸው ባለማግኘታቸው የተቸገሩ መኖራቸው በአዲስ ማለዳም ተዘግቦ ነበር።

‹‹ለተመራቂዎች ምንም ዓይነት ፈተና ቢሰጥ፣ አንባቢ ትውልድ መፍራት የለበትም። ፈተና ራስን መፈተሻ ነው።›› የሚሉት የልዩ ፍላጎትና የአካቶ ትምህርት ባለሙያው ዓለማየሁ ተክለማርያም (ዶ/ር) ናቸው።

የመውጫ ፈተናውን ተማሪዎቹ ራሳቸውን እንዲፈትሹ ይረዳቸዋል የሚሉት ዓለማየሁ፤ ጥሩ የትምህርት ጥራትን ካስመዘገቡ አገራት መካከል አሜሪካንን አንስተዋል። በአሜሪካ ተማሪዎቻቸው ዲግሪ የሚቀበሉት በየዓመቱ ፈተና እየተፈተኑ ከወደቁም በድጋሚ እየወሰዱ ነው ብለዋል።

እንደ ዓለማየሁ ገለጻ ከሆነ፤ በቀጣይ ዓመት ይሰጣል የተባለው የዩቨርሲቲ የመውጫ ፈተና የተማሪዎቹን ክህሎት በማዳበር፤ በትምህርት ተቋማት፤ በመምህራንና በወላጆች ላይ ኩራትንና መተማመንን የሚያጎናጽፍ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ከታችኛው ክፍል ጀምሮ በኩረጃ የዋዠቀ ነው ያሉት ዓለማየሁ፤ የመውጫ ፈተና መሠጠቱ አሁን ላይ ያለው ትውልድ ራሱን እንዲፈትሽ ለመጭው ትውልድ ደግሞ በጥንቃቄ ለመማር ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ፣ የመውጫ ፈተናውን የሚሰጡና የሚያወጡ መምህራን ብቁና ታማኝ መሆንም ይጠቅባቸዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ለግሰዋል።

እንደ ማሌዢያ፤ ጃፓንና ቻይና የመሳሰሉ አገራት ያሉ ተማሪዎች ራሳቸውን የሚገመግሙት በየዩኒቨርሲቲው የመውጫ ፈተና እየወሰዱ ምን ያህል እንዳለፉና እንደወደቁ ራሳቸውን በመፈተሸ መሆኑን ዓለማየሁ ጠቅሰዋል። ይህም ድርጊት ተማሪዎች ጉድለታቸውን አውቀው እንዲጠነክሩ ይረዳቸዋል ባይ ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥም ይህ ዓይነት ልምድ ቢኖር የትምህርት ጥራቱ የተሻለ እንደሚሆን አያጠራጠጥርም ሲሉ አነጻጽረዋል።

ምንም እንኳ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚሰጠው የመውጫ ፈተና ለተማሪዎች ክህሎት መዳበር ጥሩ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ቢታሰብም፤ በተለይም በጦርነት ቀጠና ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች ከሌሎች ጋር እኩል መወዳደራቸው ፍትሃዊ እንደማይሆን አስተያየቶች ተሰንዝረዋል።

ይህን በተመለከተም ዓለማየሁ በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ለነበሩ ተማሪዎች ፈተናውን ቀለል ማድረግ ተገቢ መሆኑን አሳስበው፤ ምናልባት ለተማሪዎቹ የጥናት ጊዜ መስጠትም አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ትምህርትና ፖለቲካ
በኢትዮጵያ ለሚስተዋለው ያሽቆለቆለ የትምህርት ጥራት ዋነኛው ምክንያት ፖለቲካን ከትምህርት ጋር ማያያዝ ነው የሚሉት ዓለማየሁ፤ ይህ አሠራር እንዲቀር ከታችኛው የትምህርት ተቋም ጀምሮ ሊሠራበት እንደሚገባም መክረዋል።

ከታችኛው የትምህርት ተቋም ጀምሮ ያሉት አመራሮች በፖለቲካ የተተበተቡ በመሆናቸው፣ ተማሪዎችን አብቅቶ ማሳለፍ እንጂ መጣል አይቻልም በሚል መመሪያ ሳያበቁ በማሳለፍ ትውልድን እየገደሉ መሆኑንም አንስተዋል።

‹‹ርዕሰ መምህሩን ሌላው የበላይ አካል፤ ርዕሰ መምህሩ መምህራኑን የሚቆጣጠሩበት መንገድ ስንት ተማሪ አብቅተህ አሳለፍክ የሚል አይደለም። ይልቁንም ስንት ተማሪ አሳለፍክ የሚል ነው። በመሆኑም የትምህርት ስርዓቱ በፖለቲካው አፈር ድሜ በልቷል›› ነው ያሉት።

ዓለማየሁ በተያያዘም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መጻፍና ማንበብ የማይችል ተማሪ ማግኘታቸውን አስታውሰው፤ ለዚህ ችግር መከሰት ዋነኛው ችግር ከታች ያለው አሠራር ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here