ሠሞኑን አነጋጋሪ ከሆኑና ብዙዎችን ግራ ካጋቡ ክስተቶች መካከል በሳምንቱ መጀመሪያ የሩስያ ኤምባሲ በር ላይ የነበረ ሠልፍ አንዱ ነው። ለቀናት ያለማቋረጥ ሠነድ የያዙ ኢትዮጵያዊያን ከወትሮው በተለየ በብዛት ተሰልፈው የተመለከቱ ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎች ጉዳዩን ለማጣራት ሞክረው ነበር።
ሩስያ ከዩክሬን ጋር እያደረገች ያለችውን ጦርነት ለማገዝ የቅጥር ማስታወቂያ መነገሩን ከሠው ሰው ሰምተው ብዙዎቹ ዶሴያቸውን ሸክፈው መገኘታቸውን ገልፀው ነበር። ይህ የውጭ ዜጋን ለጦርነት መመልመል ቬይና ላይ በተፈረመው ዓለም ዐቀፍ ስምምነት የተከለከለ ወንጀል ነው ብለው ብዙዎች የተቹት ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግሞ ለክፉ ጊዜ ወዳጃችን ውለታዋን የምንመልስበት አጋጣሚ ስለሆነ አይመለከታችሁም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ለመመዝገብ የተሰለፉትም ሆኑ ጠየቅናቸው ያሉት ግለሰቦች የተናገሩት ኤምባሲው እንደሚመዘግብ ቢሆንም፣ ኃላፊዎቹ ሲጠየቁ ግን እንዲህ ዓይነት ሕገወጥ ተግባርን አናከናውንም ሲሉ አስረድተዋል። ማንም ኢትዮጵያዊ ወደ ሩስያ ለመሄድ ቪዛ ቢፈልግ እንደሚያደርገው ሕጋዊ ሠነዱን ይዞ ሲመጣ መዝግበን እናስተናግዳለን ሲሉ ተደምጠዋል። ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ድጋፍ ቀደም ብለን እናውቃለን ያሉት የኤምባሲው ኃላፊ፣ ለአገራችን ለመዋጋት ቢፈልጉም እንዴት እንደምናደርግ ግራ ገብቶናል ብለዋል ተብሎም ተወርቷል።
አብዛኞቹ የውትድርና ልምድ ያላቸው አመልካቾች መሰብሰባቸውን ያዩ የተወሰኑ ኢትዮጵያዊያን እንደአገር ዝቅጠትን የሚያመላክት ነው ሲሉ ገልፀውታል። አንዳንዶች ደግሞ ደቡብ ኮሪያን ደግፈን ሰሜን ኮሪያን በመውጋታችን አሁን ድረስ የምንኮፈስ ሕዝቦች፣ በጥቁሮች ላይ አንዳችም የሆነ በደል በታሪኳ ፈፅማ የማታውቅን አገር ብንደግፍ ምኑ ነው ኃጢያቱ ሲሉ ተደምጠዋል።
የዩክሬን መንግሥት ጥቁሮች ላይ የሠራውን ዓለም ያየውን ግፍ ለመበቀል አልያም፣ የአፍሪካ አገራት ሳይጠይቁ ለመመልመል ተጣድፈው እንዳፈሩት ዓይነት ቅሌት ውስጥ ያልገባችውን ሩስያን ለማዋረድ ምዕራባውያን የሸረቡት ሴራ ነው በማለት ነገሩን ያብራሩም ነበሩ።
ያም ተባለ ይህ፣ በኤምባሲው ደጃፍ ላይ በተከታታይ ቀናት ለአባት አገር ሩስያ ለመዋጋት ብለው ሳይጠሩም ቢሆን የተሰለፉት ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው የኑሮ ሁኔታ ምን ያህል እንደተማረሩ የሚያሳይ ነው ሲሉ በርካቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዉበታል። ኢትዮጵያዊያን በውስጥ ጦርነት እየታመሱ ባለበት ሁኔታ፣ አሁንም ሠላም ማስከበር እንደሰማይ የራቀበት መንግሥት ዜጎቹ የሌላ አገርን ሠላም ለማምጣት ብለው ጦርነት ውስጥ መግባት ሲፈልጉ እያየ ምን እንደሚል ብዙዎች በጉጉት እየጠበቁ ነው።
ወደውጭ አገር መሄድ እስካልተከለከለ ድረስ ማንም ሄዶ በፈቀደው ሥራ የመቀጠር እድል እስካለው ድረስ መሄድ አይከለከልም። የአገሩን ዜግነት ሳይለቅ የሌላ አገር ወታደር ሆኖ መቀጠር ስለመቻሉ ግን ብዙዎች ሲወዛገቡበት ቆይተዋል። የአሜሪካ ጦር ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተቀጥረው ሲሠሩ ምንም ሳይሉ፣ ለሩስያ ሲሆን ምነው ሆዳቸውን ቆረጣቸው ሲሉ፣ ትችትም ሆነ ድጋፍ ፍትሐዊ ይሁን ሲሉ የጠየቁም ነበሩ። በሌላ በኩል፣ የኃያላኑን ሽኩቻ እዚህ እንዳያመጡብን ሲሉ ያስጠነቀቁም አሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014



