በአማራ ብሔራዊ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ ከተሞች ከሦስተኛ ወገን ነፃ ባልሆነ መሬት ላይ በሚደረግ ሕገወጥ የሪል እስቴት ልማት፣ ባልተፈቀደ መሬትና ባልተገነባ ሕንጻ፣ ሕዝቡን የሚያጭበረብሩ አካላት መኖራቸውን የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በሰላም ይመኑ፣ በክልሉ በሚገኙ ከተሞች የኢንቨስትመንት ሥራዎች ይሠራሉ። ከዚህ ውስጥ ሪል እስቴት ልማት አንዱ ነው፤ አሁንም አልተከለከለም። ሆኖም ባልተፈቀደ መሬትና ባልተገነባ ሕንጻ ሪል እስቴት ይሸጣል በሚል ሕዝቡ እየተጭበረበረ ነው ብለዋል።
ስለዚህም የክልሉ መንግሥት ዜጎችን ከተሳሳተና ሕገወጥ አሠራር መከላከል ስላለበት እንዳይታለሉ መረጃ መስጠቱ እንዲሁም በአርሶ አደሩ መሬት ላይ ሪል እስቴት እናለማለን የሚለው አሠራር ሕጋዊ ባለመሆኑ መታረም እንዳለበት ነው የገለጹት።
ይህ ዓይነት እንቅስቃሴ በባህር ዳር ከተማ እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም አስተዳደር ስር ባለው ባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ በስፋት የሚስተዋል መሆኑን ቢሮው የገለጸ ሲሆን፣ በደብረ ብርሃን ከተማም መሰል እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ነው የሚነገረው።
የሪል እስቴት ኢንቨስትመንት አስፈላጊነቱ ታምኖበት፣ ቢያንስ አንድ ሺሕ ቤቶችና ከዚያ በላይ ለሚገነቡ አካላት ማልሚያ የሚሆን ከሦስተኛ ወገን ነጻ የሆነ ቦታ የክልሉ መንግሥት አዘጋጅቶ ይሰጣልም ተብሏል።
ይህ ሲደረግም መጀመሪያ የሚቀርበው ፕሮጀክት አሳማኝነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የሚለሙ ቤቶች ብዛት እንዲሁም ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያማከሉ ስለመሆኑ ተረጋግጦ፣ በተጨማሪም ይህን ለመገንባት የሚያስችል በቂ ካፒታል መኖሩ ግምት ውስጥ ገብቶ፣ ይህ ኹሉ ሲሟላ ለአልሚው ፈቃድ እንደሚሰጠው ተመላክቷል።
ቢሮው አሁን ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን አልፈቀድኩም ሕገወጥ ናቸው ያለበት ምክንያትም፣ መንግሥት በሦስተኛ ወገን ያለን መሬት ነፃ አድርጎ ሳያስረክብ ግለሰቦች በቀጥታ ከመንግሥት ጋር ሳይሆን ከአርሶ አደሮች ጋር ግንኙነት ፈጥረው የአርሶ አደሩን መሬት ገዝተው፣ አርሶ አደሮች በራሳችን መሬት ላይ ማልማት እንችላለን የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ ተደርጎ፣ ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ነው ያልተገነባ ሕንጻ እየተሸጠ ያለው ተብሏል።
ሆኖም የክልሉ መንግሥት ለአርሶ አደሩ ካሳ ከፍሎ ከሦስተኛ ወገን ነፃ ባደረገው መሬት ላይ የሪል እስቴት ልማት ሲሠራበት የቆየና ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑ ነው የተገለጸው።
ቦታው የኢንዱስትሪ ማዕከል፣ የገበያ ማዕከል፣ የመኖሪያ ወይም ለሌላ ዓላማ ሊውል እንደሚችል ሳይታወቅ የሚደረግ የሪል እስቴት ሥራም በከተሞች ንድፍ አወጣጥ (Plan) ላይ እንቅፋት እንደሚፈጥርና ዜጎችን ለአላስፈላጊ ወጭ እንደሚዳርግ ተመላክቷል።
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ማንኛውም ልማት የሚሠራው የአርሶ አደሩን መሬት በመጠቀም መሆኑን ጠቅሰው፣ ሕገወጥ የሪል እስቴት እንቅስቃሴዎች ሊፈጠሩ የቻሉት የአርሶ አደሩ መሬት ለልማት በሚፈለግበት ወቅት አቅም ካለው ቅድሚያ የማልማት መብት አለው በሚል አዋጅ ላይ የተቀመጠን አሰራር በመያዝ ነው። ሆኖም ግን የአፈጻጸም መመሪያ ሳይዘጋጅ ይህን ተግባራዊ እናደርጋለን ማለት ስህተት ነው ብለዋል፡፡
ይህን አሠራር ተፈጻሚ ለማድረግም፣ ወደፊት አዋጁ ላይ የተቀመጠውን መነሻ በማድረግ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ እንደሚዘጋጅ እና በሚወጣው መመሪያም አርሶ አደሩ የሚሳተፍበት መንገድ ዝግ ላይሆን ይችላል ሲሉ ጠቁመዋል።
ቢሮውም ሕገወጥ የሪል እስቴት ግዥና ሽያጭ መኖሩን አውቆ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ከጀመረ ወዲህ በስውር ይደረጋል ተብሎ ከሚታሰበው ውጪ እንቅስቃሴው ረገብ ማለቱ ተነግሯል።
በክልሉ በመደበኛ አሠራር የሪል እስቴት ልማት የተጀመረው በ1999 ሲሆን፣ በአጠቃላይ 611 ሺሕ 166 ካሬ ሜትር ቦታ ወስደው በተለያዩ ከተሞች የሚንቀሳቀሱ 12 አልሚዎች መኖራቸው ተገልጿል።
በዚህም በባህር ዳር አራት የሪል እስቴት ፕሮጀክቶች ሲኖሩ፣ በተጨማሪም በጎንደር አራት፣ በደሴ ሦስት እንዲሁም በሸዋሮቢት አንድ መኖራቸው ነው የተመላከተው። በሪል እስቴት እንዲገነቡ ፈቃድ ከተሰጣቸው 1 ሺሕ 263 መኖሪያ ቤቶች ውስጥም 723 የሚሆኑት ግንባታቸው ያለቀ ሲሆን፣ 364 የሚሆኑት ደግሞ በሂደት ላይ እንዳሉና 153 ያልተገነቡ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በተፈቀደ መሬት ላይ ለመኖሪያ፣ ለንግድ ወይም ለኪራይ የሚገነባ ሕንጻ ሆኖ፣ ቅጥር ግቢ ያለውና በግቢው ውስጥም ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ፣ ጅምናዚየም እና የመሳሰሉትን ያካተተ ሆኖ ሲገኝ፣ ሪል እስቴት ነው ተብሏል። በአሁኑ ወቅትም በርካታ የሪል እስቴት ልማት ጥያቄዎች ከተለያዩ የክልሉ ከተሞች እየቀረቡ ነው ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014


