በቆቦ ከተማ አንድ ሊትር ቤንዚን 100 ብር እየተሸጠ ነው

0
696

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ በቆቦ ከተማ ቤንዚን እስከ አሁን ሲሸጥበት ከነበረው መደበኛ ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ 100 ብር እየተሸጠ መሆኑ ተገለጸ።
አንድ ሊትር ቤንዚን ከኹለት ወር በፊት 40 ብር ይገዙ እንደነበረና አሁን ግን 100 ብር እንደሆነ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የቆቦ ከተማ ቤንዚን ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።

ከተወሰኑ ሳምንታት ወዲህ የቤንዚን ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል የሚለው በቆቦ ከተማ ባጃጅ በማሽከርከር ሥራ የተሰማራው ሽመልስ ሞገስ የተባለ ወጣት ነው። ከወር በፊት ዋጋው ከ40 ወደ 70 ብር ከፍ ብሎ የነበረ ሲሆን፤ ሰሞኑን ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የ30 ብር ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል።

እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለጻ፤ በኹለት ወር ቆይታ ውስጥ የቤንዚን ዋጋ ከ40 ወደ 100 ብር ከፍ ማለቱን ተከትሎ ላልተፈለገ ወጪ ከመዳረጋቸውም በተጨማሪ በሥራቸው ላይ መስተጓጎልን አስከትሏል።

ቤንዚን የሚገዙት ከቸርቻሪዎች መሆኑን የገለጹት ሌላኛው ሰለሞን አዲሱ የተባሉት የባጃጅ ሹፌር፤ ዋጋው የጨመረበት ምክንያት ከቸርቻሪዎች እንጂ ከማደያ አለመገኘቱ መሆኑን አንስተዋል።
‹‹ቸርቻሪዎችም በቀን ኹለት ጀሪካን ብቻ ነው የምናገኘው ይላሉ›› ያሉት ሰለሞን፤ ቤት ንብረታቸው በጦርነት መውደሙን በመግለጽ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር መቸገራቸውን ይናገራሉ።

በተያያዘም፣ ከሣምንት በፊት አንድ ሊትር ቤንዚን አንዳንድ ቦታ ላይ 60 ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ 70 ብር ሲገዙ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ግን አልፎ አልፎ 90 ብር አብዛኛው ቦታ ላይ ግን 100 ብር እንደሚገዙ ነው ያብራሩት።

ኤፍሬም አማረ የተባሉ የባጃጅ ሹፌር በበኩላቸው፤ በአንድ ቀን ስድስት ሊትር ቤንዚን እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፤ ለዚህም 600 ብር እንደሚያስፈልጋቸውና ከገቢው ወጪው እንደሚያመዝን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ በነበረችው የራያ ቆቦ ከተማ እስከ አሁን የወደመው የውሃና የመብራት መሠረተ ልማት አለመጠገኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህን በተመለከተም ነዋሪዎቹ ቅሬታ እያቀረቡ መሆኑን አዲስ ማለዳ በከተማው በተገኘችበት ወቅት ማረጋገጥ ችላለች።

ከነዋሪዎቹ በተደጋጋሚ የሚሰማው ቅሬታ፤ ‹‹በጨለማ ውስጥ ነው ያለነው። የውሃ ችግርም እስከ አሁን መፍትሄ አልተሰጠውም። አንድ ጀሪካን ውሃ 20 ብር ነው የምንገዛው›› የሚል ነው።
የነዳጅ መግዣ ዋጋ በየጊዜው ከመጨመሩም በላይ እየተፈራረቀ በሚከሰተው ‹‹ሰው ሠራሽ›› እጥረት ምክንያት ሌሎች ተጠቃሚዎችና በተለይም አሽከርካሪዎች ነዳጅ ለማስሞላት ለረጅም ጊዜ (ከኹለት ቀን በላይ) ወረፋ እየጠበቁ ስለመሆናቸው ቅሬታ እያነሱ መቆየታቸው አይዘነጋም።

መንግሥት ለችግሩ መከሰት ዋነኛው ምክንያት ነጋዴዎች ነዳጅ በውድ ዋጋ ወደሚሸጥባቸው የድንበር አካባቢዎች በሕገ ወጥ መንገድ ስለሚሸጡ መሆኑን ጠቅሶ ዋጋውን ከውጭ አገሮች ጋር እኩል ለማድርግ ውሳኔ አስተላልፏል።

በቆቦ ከተማ ሰሞኑን በተለይም የቤንዚን ዋጋ እስከዛሬ ሲሸጥበት ከነበረበት ዋጋ ከእጥፍ በላይ እንደጨመረም አዲስ ማለዳ በቦታው ተዘዋውራ አረጋግጣለች።
አዲስ ማለዳ ስለጉዳዩ የሚሰጡትን ምላሽ ለማግኘት ለቆቦ ከተማ ከንቲባ ሰይድ አባተ ስልክ የደወለች ሲሆን፤ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here