በዘጠኝ ወራት 66 ሺሕ ቶን የአሳ ምርት ተገኝቷል

0
1122

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 66 ሺሕ ቶን የአሳ ምርት ማግኘት መቻሉን ግብርና ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

በግብርና ሚኒስቴር የአሳ ሀብት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሁሴን አበጋዝ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከሐይቆች 34 ሺሕ ቶን፣ ከግድቦች 20 ሺሕ ቶን እንዲሁም ከወንዞች 11 ሺሕ ቶን ገደማ በጥቅሉ 66 ሺሕ ቶን የአሳ ምርት ማግኘት ተችሏል።

በበጀት ዓመቱ 3 ሺሕ 500 ቶን ዓሳ ለሱዳን ለማቅረብ ታቅዶም፣ 2 ሺሕ 900 ቶን በጨው የተዘጋጀና 500 በደረቅ የተዘጋጀ ተልኳል ብለዋል። ይህም በሕገ ወጥ መንገድ በኬንያ በኩል ወደ ውጭ የሚላከውን ከፍተኛ መጠን ያለው የአሳ ምርት ሳይጨምር መሆኑን ነው የጠቆሙት።

በተጨማሪም 622 ሺሕ ቶን የአሳ ጫጩት ለአርሶ አደሩና ለሐይቆች የተሰራጨ ሲሆን፣ ከ1 ሺሕ 500 በላይ የአሳ ማርቢያ ኩሬዎችም መቆፈራቸውን ገልጸዋል።

የአሳ ምርት በስምጥ ሸለቆ ሐይቆችና በዋና ዋና ሐይቆች ከጊዜ ወደ ጊዜ የመቀነስ እንጂ የመጨመር ሁኔታ አያሳይም ነው ያሉት። ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቀሰው፣ በሐይቁ ዙሪያ ያሉ ማኅበረሰቦች የሚያሰግሩበት መንገድና የሚጠቀሙት መሣሪያ ኋላቀርና ሕገወጥ በመሆኑ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በሌላ መልኩ ግን በሌሎች ሐይቆችና ግድቦች በስፋት እየተመረተ ይገኛል ብለዋል። ለአብነትም በግልገል ጊቤ አንድ እና በግልገል ጊቤ ሦስት ግድቦች እንዲሁም በወንዞች በተሻለ መጠን ምርት እየተገኘ መሆኑን አንስተዋል።

ሆኖም ግን የአሳ ምርት አጠቃላይ ሁኔታ ሲታይ፣ ምርቱ እንደ አገር ትንሽ ነው ሲሉ ገልጸዋል። ያለውን አቅም በሙሉ መጠቀም ብንችል የሚገኘው ምርት ከ95 ሺሕ ቶን የበለጠ አይደለም፣ ይህ ደግሞ ከ100 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን ሕዝብ ሲካፈል እንደ አገር ያለው የአሳ ምርት አቅርቦት እጅግ ዝቅተኛና የኅብረተሰቡን ፍላጎት የማያሟላ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።

የአገሪቱ መሬት የውሃ አቅርቦት አለው። የአየር ሁኔታውም ተስማሚ ነው፣ ገበያም አለ። ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት 1 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆነው ለአሳ ምርት እጅግ ተስማሚ ሲሆን፣ ከዚህም 80 በመቶ የሚሆነው ደግሞ መካከለኛ ተስማሚነት (moderate) ያለው መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ያለውን ዝቅተኛ የአገር ምርት መጠን ለማሳደግ ይህን ዕድል በመጠቀም በራስ አቅም ማምረት ነው መፍትሄው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህም ጥረት ጊዜና ቴክኖሎጂ ይጠይቃል ሲሉ አክለዋል። በዘርፉ የግል ባለሀብቶችም ተሳታፊ ቢሆኑ የምርት መጠኑን ለማሳደግ ይበጃል የሚል ሐሳባቸውንም አጋርተዋል።

ብዙ ጊዜ አገር ውስጥ የሌሉ የአሳ ዝርያዎች ከውጭ እንደሚገቡ አንስተው፣ በአገር ውስጥ ያሉ የአሳ ምርቶችም በተበጣጠሰ መልኩም ቢሆን እንደሚገቡ ገልጸዋል። በዘጠን ወራት የአሳ ምርት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብዙም ልዩነት እንደሌለውም አክለዋል። በዚህም የዘድሮው ምርት ከባለፈው ዓመት ከ6 ሺሕ ቶን በላይ ብልጫ አላሳየም ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here