በአፋር ክልል የባንክ አገልግሎት ለማኅበረሰቡ ፈተና ሆኗል
በአማራ ክልል በሦስት ዞኖች 6 ሺሕ 305 ሕጻናት ወላጆቻቸውን ማጣታቸውን የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባካሄደው ዳሰሳዊ ቁጥጥር ማረጋገጡን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአማራና አፋር ክልሎች በሚገኙ አካባቢዎች በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረግ ሰብአዊ ድጋፍ፣ መሠረታዊ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ እና መልሶ የማቋቋም ሥራ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ያካሄደውን ዳሰሳዊ ቁጥጥር ይፋ አድርጓል። በተቋሙ የዳሰሳ ቁጥጥር ሥራ መሠረት በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን 700 ሕጻናት ኹለቱንም ወላጆች፣ 853ቱ አንድ ቤተሰብ፣ 52ቱ ከቤተሰብ የተለያዩ ሲሆን በሰሜን ሸዋ 113 ሕጻናት፣ ሰሜን ጎንደር 4 ሺሕ 587 ወላጆቻቸውን አጥተዋል ተብሏል።
በክልሉ በጦርነቱ ወቅት መደፈርና ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ደግሞ በሰሜን ጎንደር 56፣ ደቡብ ጎንደር 89፣ ሰሜን ወሎ 548፣ ዋግኸምራ 111፣ ደቡብ ወሎ 342፣ ሰሜን ሸዋ 119፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ 8፣ በድምሩ ከ1217 በላይ (እናቶች፣ ልጃገረዶች፣ ወንዶችና አረጋውያን) ናቸው ተብሏል።
በሞት ሕይወታቸውን ያጡ ደግሞ ደቡብ ወሎ 548፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ 297፣ በሰሜን ሸዋ 134 መሆናቸውን የዕንባ ጠባቂ ተቋም ዳሰሳዊ የቁጥጥር ሥራ ሪፖርት ያመላክታል።
በጦርነቱ ወቀት አካል ጉዳተኛ የሆኑ ሰዎችን የለየው ተቋሙ፣ በደቡብ ወሎ ዞን 213 ሕጻናት፣ በሰሜን ጎንደር 784፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ 402፣ በሰሜን ወሎ 75 አካል ጉዳተኞች ሆነዋል ተብሏል።
ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት በክልሉ በሚገኙ የመንግሥት፣ የግልና የሕዝብ ተቋማትና ንብረቶች እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ቁሶች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የከፋ ጥፋት ደርሷል ብሏል። ጉዳቱ በኢኮኖሚ ዘርፍ፣ በማኅበራዊ ዘርፍ እና በሰብአዊ ዘርፍ የደረሰ መሆኑም ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል፣ በአፋር ክልል ቀደም ሲል በጦርት ተፈናቅለው ወደ ቀያቸው የተመለሱ ዜጎች በመሠረተ ልማትና በአገልግሎት እጦት እየተንገላቱ መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል። የመንግሥት ተቋማትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በተሟላ ሁኔታና ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸው ማኅበረሰቡ የጤና፣ ትምህርት፣ ስልክ፣ መብራት፣ ውሃና የባንክ አገልግሎት እንዳያገኝ አድርጎታል ተብሏል።
ባንኮች በተለይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጦርነት ስጋት ምክንያት በዞን አራት በሁሉም ወረዳዎች አገልግሎት መስጠት ባለመጀመሩ ኅብረተሰቡና የመንግሥት ተቋማት ለከፍተኛ እንግልትና ወጪ ከመዳረጋቸውም በላይ፣ በክልሉ ዋና ከተማ በሚገኙ ቅርንጫፎች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ተቋሙ አስታውቋል።
በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች (ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን) የሚደረግላቸው ሰብአዊና ቁሳዊ ድጋፍ በቂና ተመጣጣኝ አለመሆኑን የገለጸው ተቋሙ፣ የሕጻናት አልሚ ምግብ፣ ለአጥቢ እናቶች ወተት አለመኖር፣ ለሴቶች የንጽህና መጠበቂያ አለመሟላት፣ አቅም ላጡ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ወገኖች እርዳታው ባሉበት ቦታ እየደረሰ አለመሆኑን ጠቁሟል።
ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች፣ ለተመላላሽ ታካሚዎችና በቋሚነት መድኃኒት ለሚወስዱ የመድኃኒት አቅርቦቱ ሲታይ ውስንነት መኖሩን መታዘቡን የገለጸው ዕንባ ጠባቂ፣ የመንገድ፣ መብራት፣ ውሃ፣ ባንክና ቴሌ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ችግር ምክንያት የሸቀጦች ዋጋ መናር በመፈጠሩ የአካባቢው ኅብረተሰብ ለኑሮ ውድነት መባባስ መዳረጉ ተመላክቷል።
በአፋር ክልል 653 ንጹሃን ሰዎች መሞታቸውን በቁጥጥር ሥራው ማረጋገጡን ተቋሙ አስታውቋል። ዕንባ ጠባቂ ተቋም ይፋ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት በጦርነቱ ሕይወታቸውን ካጡ ንጹሃን ሰዎች በተጨማሪ 6 ሺሕ 609 ሰዎች አካላዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው አረጋግጫለሁ ብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014


