እንተሳሰብ!

ሠው ከሠው ጋር ካልተሳሰበ በቀር ሕግም ሆነ ጉልበት እንድንረዳዳና ፍትሐዊ ሥርዓት እንዲመጣ አያደርጉም። ሕግም ሆነ ሥርዓት በአስገዳጅነት የሚዘረጋው ኅብረተሰቡ ተስማምቶና ተሳስቦ በራሱ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ለመኖር ከተሳነው ነው። ሠው ብቻውን ይኖር ዘንድ አይሆንምና እርስ በእርስ ለመኖር ደግሞ ለአንዱ የሌላው ደኅንነት አስፈላጊ መሆኑን አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ሠው ለሠው ማሰብና እርስ በእርስም መተሳሰብ የሚያስፈልገው በዓል ሲመጣ ወይም ኮሮናን የመሰለ ወረርሺኝ ሲከሰት አልያም ጦርነት ሲመጣ ብቻ አለመሆኑ እሙን ነው። ሁልጊዜም የተቸገረና የሌሎችን ድጋፍ የሚፈልግ እንደሚኖር ይታወቃል። የዓለማችን ሀብት ውስን ቢሆንም፣ በዛው ልክ ካለው ላይ ቀንሶ የሚረዳ ደግሞ ይኖራል። ዛሬ ረጂ የነበረ ቆይቶ ተረጂ እንደሚሆን ኢትዮጵያ በኹለተኛው የዓለም ጦርነት ለእንግሊዝና ጃፓን መርዳቷን በማስታወስ አሁን ካለው ጋር በማስተያየት ልዩነቱን በማገናዘብ ማወቅ ይቻላል።

ሠው ብቻ ሳይሆን አገራትም ሆኑ ማኅበረሰቦች በተፈጥሮም ይሁን በሠው ሠራሽ ምክንያት፣ ካልሆነም በስንፍና የሌላን ድጋፍ እንደሚፈልጉ ይታወቃል። ይህ ዓለም ዐቀፍ የሆነና ማንም የሚያውቀው ሀቅ ቢሆንም፣ እርዱኝ ካልተባሉ በቀር እያወቁ ለመደገፍ የሚጥሩ ግን በጣም ትንሽ እንደሆኑ ኹላችንም ከራሳችን የልግስና ታሪክ መረዳት እንችላለን። ድጋፍ እንደሚያስፈልገው እያወቅን እስክንጠየቅ አልያም መጠየቃችንና መስጠታችን እስኪታይልን ድረስ የምንጠብቅ ምን ያህሎች እንደሆንም ቤታችን ይቁጠረው።

ለጋስነት የሚጀምረው በቤታችን ውስጥ ከልጅነት እንደሆነ የሥነልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ። አንድ ሰው ራሱ ለወደፊት ሊቸግረው እንደሚችል ሊያውቅ እንደሚገባ ሁሉ፣ የሌላውንም ችግር ሊረዳና ሊደግፍ እንደሚገባ መማር ያለበት ከቤተሰቦቹ ነው። ሕፃናትን የምናስተምረው የቀለሙን ትምህርት ብቻ ሳይሆን ለጋስነትን የመሳሰሉ በጎ ምግባሮችን ጭምር ነው። ይህ ካልሆነ ግን ብዙ ቢያውቁም ዕውቀታቸውን ማገልገያና መጥቀሚያ ከማድረግ ይልቅ መበዝበዣ እንደሚያደርጉት አሁን በአገራችን እየታየ ካለው ስግብግብነት መረዳት እንደሚቻል አዲስ ማለዳ ታመላክታለች።

በአገራችን ሠላም አጥቶ የሚሰቃይ በርካታ ዜጋ ቢኖርም፣ በኑሮ ውድነት በየቀኑ ቁም ስቅሉን የሚያሳየው ግን የትየለሌ ነው። ሠርቶ የሚያገኘው ገቢ ለሚያስፈልገው ወጪ አልበቃ እያለው ሲጨነቅ የሚያድረው ሕዝብ ቁጥር እያደር እንደሚጨምር የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አጋጣሚውን ባገኙ ቁጥር ይናገራሉ። በዋጋ ግሽበት ሀብታሙ የበለጠ ሀብታም የሚያደርገው ተግባር ውስጥ እየገባ እየተመለከትን እንደመሆኑ፣ መካከለኛ ገቢ ያለው በአብዛኛው ተቀጣሪ ደሞዝተኛ የሆነው ደግሞ እያደር ወደ ድህነት እያመራ መሆኑን ቆጠራ ማድረግ ሳያስፈልግ ኹሉም ሊመለከተው የሚችል ሐቅ ነው። ድሃው በበኩሉ በስንት ልፋት የሚያገኛት አነስተኛ ገቢ እንዳትበቃው ስለሚያደርገው ወደማይገባ ነገር እንዲገባ ሊያስገድደው ይችላል።

ዝርፊያና ሌብነት በየጊዜው እየጨመረ የሚታመን የጠፋበት ጊዜ ላይ የደረስንበት ምክንያትን ቆም ብለን ልናስበው ይገባል። የሚበላው ያጣ ማኅበረሰብ ለምኖም መብላት ከተሳነው እንደቀድሞ አባቶቻችን በረሃብ ተኮራምቶ ሞቱን ይናፍቃል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው። በሥነምግባር ያልታነፀ ማኅበረሰብ ይዘን ርቦት ዝም ብሎ ያደራል ብሎ መጠበቅም ሞኝነት ነው። ሠው ለሕይወቱ አስፈላጊ የሆነውን መብል ማግኘት መብቱ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። “አልሞት ባይ ተጋዳይ” እንደሚባለው፣ ሊገድለው ካለ ነገር ራስን ለማዳን ሲል እንደሚገድል፣ ርቦት ላለመሞት ሲል የሌላን ንብረት ቢሰርቅ በምን ሕሊና ነው ለወደፊቱም ሠርቶ እንዳይበላ አስረን የምናበላው?

ሕዝብ እንደአንድ ቤተሰብ ተስማምቶ ተሳስቦ እየተረዳዳ መኖር ካልቻለ፣ አንዱ ለሁሉም ብሎ ለምን እንደሚገብርና በተተመነለት ሒሳብ ለምን እንደሚገበያይ ይረዳል ወይ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። ሠው ተርቦ ሕይወቱ አደጋ ላይ ከመውደቁ በፊት አስቀድሞ እርስ በእርስ ሊተሳሰብ የሚያስችለው አሠራር ሊዘረጋ ይገባል።

መንግሥት የቅድሚያ ተግባሩ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ቢሆንም ይህንንም ማከናወን አለመቻሉን ለማሳየት በያዝነው ሳምንትም በሰሜን ሸዋ አካባቢ የተከሰተውን ጥፋት ማስታወስ በቂ ነው። ይህን ቀዳሚ ተግባሩን ማከናወን ሳይቻለው የኑሮ ውድነትን ይቀንሳል፤ ነጋዴዎችን ይቆጣጠራል፤ ለተቸገሩም ይረዳል ብሎ መጠበቅ አይቻልም። መንግሥት ቻለም አልቻለም ዝም ተብሎ አይሞትምና ኅብረተሰቡ የራሱን አደረጃጀትም ሆነ ማኅበር እየመሠረተ፣ ተረጂንና ድጋፍ የሚፈልግን እየለየ በራሱ መንገድ ዜጎችን መታደግ እንደሚጠበቅበት አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ኅብረተሰቡ የሚረዳው ሲያጣ መሰደድና የተሻለ መኖሪያ መፈለግ አንዱ አማራጩ ቢሆንም በሳዑዲ አረቢያና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ኢትዮጵያዊያን ሥራ ፈላጊዎች የሚደርስባቸውን እየተመለከትን ማበረታታት አንችልም። ዜጎች የለፉበትን አጥተው ወደ ተሰደዱባት አገራቸው በግድ ሲመለሱ ማየት እጅግ አሳዛኝ የመሆኑን ያህል፣ እዚህስ መጥተው ምን ይሆናሉ የሚለውም ሌላ ራስ ምታት ነው። ሕይወታችንን ይለውጣሉ ብሎ የሚጠብቅ ቤተሰብ ልጆቹ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ሲመለሱበት ሲያይ ተስፋ መቁረጡ የማይቀር ነው። እንዲህ ዓይነት ክስተቶችን ፍራቻም ወደ አውሮፓ ለመግባት ብለው ፍዳቸውን የሚያዩ እንዲሁም ባሕር ሰጥመው የሚቀሩ በርካቶች አሉ።

አብዛኛው የኢትዮጵያዊያን መከራ የሚጀምረው ለሀብት ያለን ስንኩል አመለካከት ጠፍሮ ስለሚይዘን ይመስላል። አገራችን ተፈጥሮ ያደላት መሆኗን እያወቅን ሰላምና አብሮ የመኖር እሴታችን ስለተሸረሸረ ለችግር ተዳርገናል። መተሳሰብ ስለሌለ አንዱ ሀብቱን ቆልሎ የሚያደርግበት እያጣ፣ ‹ምሳዬን የት እንደምበላ ነው የሚያስጨንቀኝ!› እያለ ሲሞላቀቅ እየታዘብን ነው። ‹እንደፈለኩ ባደርግ ምን አገባችሁ› የሚሉ በሕዝብ ሥም ዝና ላይ ነን የሚሉ አፋቸውን ሞልተው ሲናገሩም እያደመጥን እንገኛለን።

በየቦታው ምን ያህል ምግብና ሀብት እየባከነ እንደሆነ፣ ምን ያህሉስ ተደብቆና ተከማችቶ ሌላው ርቦት ሲያለቅስ እንደሚያድር መገመቱ አስቸጋሪ አይደለም። ‹‹ያለኝ ሀብት ሕዝብ ነው›› መባሉ ቀርቶ፤ ሕዝብ እየተራበ በመደበኛነት መርዳት እየቻሉ እንዳላየ የሚሆኑ፤ ምንአገባኝ የሚሉ፤ ሁሉን ረድቼ አልችለውም የሚሉም በርክተዋል። መርዳት የሚችለው ሰው መጠን ከችግረኛው ባይመጣጠንና ጥቂቶች ያላቸውን ሀብት ቢያስተባብሩ ሙሉ በሙሉ በአጭር ጊዜ ችግሩን መቅረፍ ባይቻላቸውም፤ በከፍተኛ መጠን ችግሩን መቀነስ እንደሚችሉ የአዲስ ማለዳ እምነት ነው።

በሌላ በኩል፣ በነጻ ምግብ የሚቀርብባቸው ቦታዎች ቢዘጋጁ እንኳን፣ ምን ያህል ሰው ሀብት እያለው ለመቆጠብ ሲል ከእውነተኛ ድሃ ላይ መጥቶ ይነጥቃል ብንል በርካታ እንደሚሆን የሚናገሩ አሉ። ጥንት የነበረው የመተሳሰብ ባሕላችን መልሶ እስኪዳብር የተቸገረውን ከአጭበርባሪው የምንለይበት መንገድ በቶሎ ሊዘጋጅ ግድ ይላል። ጊዜያዊ ችግር ላይ ሆኖ ለወደፊት ሠርቶ የሚበላ እንዳይሆን፣ አቅም እያለው ግን በእርዳታ ብቻ ተማምኖ እጁን አጣጥፎ እንዳይበላም ሊታሰብብት ይገባል። በ77 ድርቅ ጊዜ ተረጂዎች እርዳታን ዝም ብሎ መቀበል እንዳይለምዱ ተብሎ፣ ‹ምግብ ለሥራ› በሚል ዘመቻ ለራሳቸው ጠቃሚ የሆነን መንገድ በየአካባቢያቸው እንዲሠሩ ከተደረገበት ታሪክም መማር እንችላለን።

ጀርመኖች፣ ‹አሳ ከምትሰጠው ማጥመጃውን ሰጥተህ አሰጋገር አስተምረው› የሚሉትን ብሂል ተግባራዊ ማድረግም ይጠበቅብናል። አብዛኞቻችን እስከመቼ ብለን መንግሥትን ጨምሮ ተረጂ እንሆናለን ብለንም ማሰብ ይጠበቅብናል።

ወቅቱ የበዓል እንደመሆኑ የተለመደ ነገር ሲጎድል ምን ያህል የልቦና ቁስል እንደሚሆን ተረድተን፣ መንፈሳዊነቱ ቢቀርብን እንኳን ሠብዓዊነቱ ተሰምቶን ያለንን ብናጋራ መልካም ነው። ያለው ከሌለው ጋር ተቀናጅቶ እየተጠራራ ማብላት ብቻ ሳይሆን፣ የተቸገረም በተዋረድ እንዲረዳ የሚያስችለውን የሚዘልቅ ድጋፍንም ማድረግ ይጠበቃል። ብዙም ሆነ ትንሽን የተቀበለ ሰው፣ ከደረሰው ላይ በመቶኛ እያሰላ ከሱ ለሚያንሱት ቢያስተላልፍ የረጂና ተረጂን መራራቅም መቀነስ ይቻላል ስትል አዲስ ማለዳ ይበልጥ እንድንተሳሰብ ታሳስባለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች