161 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያዋ 104 ሰዎች በእሳት እና ድንገተኛ አደጋ መሞታቸውን የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በ2014 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የ104 ሰዎች ሕይወት በእሳትና ድንገተኛ አደጋ እንደሞቱ እና 154 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋት ማሞ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ባለሙያው አክለውም 13 ሰዎች በእሳት አደጋ፣ ቀሪዎቹ 89 ሰዎች እንዲሁ በጎርፍ፣ በኩሬ፣ ኮንስትራክሽን አደጋዎች ሞተዋል ብለዋል። አያይዘውም በዘጠኝ ወራት በአዲስ አበባ ከተማ 342 እና በአዲስ አበባ ከተማ ኦሮሚያ ልዩ ዞን 35 በአጠቃላይ በድምሩ 377 አደጋዎች አጋጥመዋል። ከዚህ ውስጥ 251 በእሳት፣ ቀሪዎቹ 176 እንዲሁ በጎርፍ እና በግንባታ ሥራዎች ያጋጣሙ አደጋዎች መሆናቸው ተጠቁሟል።
ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር፣ ባለፈው በጀት ዓመት 74 ሞት እና 86 እንዲሁ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል። በአንጻሩ በተያዘው ዓመት የደረሰው አደጋ 30 የሞት መጠን እና 68 ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ጭማሪ ማሳየቱን ባለሙያው ገልጸዋል።
በተጨማሪ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ161 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት እና ንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ እና በኮሚሽኑ ሠራተኞች አማካኝነት በተደረገ ርብርብ 307 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረት መታደግ መቻሉንም አያይዘው ጠቅሰዋል።
የ2014 የትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ የተለያዩ ድንገተኛ አደጋዎች ሊያጋጥም የሚችልበት እድል ሊኖር ስለሚችል፣ ይህን መሠረት ባደረገ መልኩ ኹለት ዝግጅቶች ተደርገዋል ተብሏል።
ኮሚሽኑ የመጀመሪያው አደጋ እንዳያጋጥም እና ምን ዓይነት አደጋዎች ሊከሰቱ ይችላሉ ብሎ በመለየት ኅብረተሰቡ ቀድሞ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ብሮሸር እና በበራሪ ወረቀቶችን በገበያ ቦታዎች፣ በኃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ብዙ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች አደጋ ከመድረሱ በፊት በመበተን ወይም በመለጠፍ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን ባለሙያው ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገር ኮሚሽኑ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በትኩረት ዝግጅት እንዳደረገበት እና እሳትና ድንገተኛ እንዲሁም ተያያዥ አደጋዎች ቢከሰቱ፣ በኮሚሽኑ እና በዘጠኝ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ከ100 በላይ ሠራተኞችን እንዲሁም ከ20 በላይ ተሽከርካሪዎችን በማዘጋጀት ለመሥራት ዝግጅት መደረጉን ባለሙያው ገልፀዋል።
ኮሚሽኑ በተጨማሪ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የሰዎች እንቅስቃሴ ሊበረክት ስለሚችል ኅብረተሰቡ ራሱን ከትራፊክ አደጋ እንዲጠብቅ አሳስቧል።
ኅብረተሰቡ ከበአላቱ አከባበር ጋር ተያይዞ ከሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ጎን ለጎን የአደጋ ስጋቶችን ሲመለከት እና አደጋ ሲያጋጥም በ939 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ዘጠኝ ቅርንጫፎች ፈጣን አገልግሎት መጠየቅ ይኖርበታል ሲሉም ጠቁመዋል። ለዚህም ተቋሙ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ከሕዝቡ በሚደርሰው ጥቆማ መሠረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋት ማሞ ተናግረዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014



