ከአዲስ አበባ ወደ ክፍለ አገር እንዲሁም ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ የሚጓዙ ተሳፋሪዎች ከታሪፍ በላይ በመክፈላቸው እየተማረሩ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ትራንስፖርት ሰጭዎች በተሳፋሪዎች ላይ ከሕግ አግባብ ውጪ እያስከፈሉ እንደሆነና ተቆጣጣሪ ባለመኖሩም ኅብረተሰቡን እያማረረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎች ለአብነትም ከአዲስ አበባ ፍቼ በታሪፍ ከተወሰነው ዋጋ ውጪ ከ30 እስከ 50 ብር ጨምረው እንደሚያስከፍሉ ገልጸው፣ ከጎሃ ጽዮን ደጀን ለመሄድም በሕጋዊ መንገድ የተተመነው ታሪፍ በደረጃ አንድ የሕዝብ ትራንስፖርት 31 ብር እንዲሁም በደረጃ ኹለት ትራንስፖርት 28 ብር ሆኖ ሳለ፣ አሽከርካሪዎች ግን 150 ብር ካልሆነ እንደማይጭኑ እና ይህን ማድረግ ከጀመሩም ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆናቸው ተናግረዋል።
አሽከርካሪዎች በተተመነው ታሪፍ አገልግሎት መስጠት እንደማያዋጣቸውና በዚያ ዋጋ እንደማይጭኑ በመናገር፣ ከመናኽሪያ ሲወጡ የጉዞ ደረሰኙ ላይ ትክክለኛ ዋጋውን ጽፈው የሚወጡ ቢሆንም፣ ተሳፋሪዎች መንገድ ላይ ትራፊክ ፖሊስ ቢጠይቃቸው ትክክለኛውን ታሪፍ ከፍለው እንደሚጓዙ እንዲናገሩ ያስገድዷቸዋል። ተሳፋሪዎችም ደጋግመው ቢጠይቁም የሚሰማ አካል ባለመኖሩና በሕግ አስከባሪዎች ላይም ጠንካራ እምነት ስለሌላቸው ለትራፊክ ተቆጣጣሪዎች መናገርን አይመርጡም ነው ያሉት።
ብዙ አሽከርካሪዎችም መናኽሪያ ሳይገቡ ከታሪፍ ውጭ በማስከፈል እንደሚጭኑ ቅሬታ አቅራቢዎች ይገልጻሉ። በየቀኑ ከሚጓዘው ሕዝብ አንጻር ያለው ተሸከርካሪ ቁጥር በቂ ባለመሆኑም ተሳፋሪዎች አማራጭ በማጣት አላግባብ የተጠየቁትን ክፍያ ለመክፈል እንደሚገደዱ ያነሳሉ።
እንዲሁም ከአዲስ አበባ ደብረ ብርሃን ታሪፉ 70 ቢሆንም ተሳፋሪዎች የሚከፍሉት 100 ብር ሲሆን፣ ከደብርረ ብርሃን አጣዬም እንዲሁ ከ15 ብር በላይ ጭማሪ ያደርጋሉ ነው የተባለው። ወደ ደቡብ በሚደረጉ ጉዞዎችም ከታሪፍ ውጭ የሚያስከፍሉ ትራንስፖርት ሰጭዎች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ማለዳ ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የክልል ከተሞች እንዲሁም በክልል ከተሞች መካካል በሚደረጉ ጉዞዎች ያለውን የጉዞ ታሪፍ ባጣራችበት ወቅትም፣ በብዙ ቦታዎች ተሳፋሪዎች ከታሪፍ ውጭ እንደሚከፍሉና አሁን አሁን እንደ መደበኛ ዋጋ እንደቆጠሩት ተናግረዋል።
ስለሆነም የሚመለከተው የመንግሥት አካል ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል። ባለንብረቶችን የሚጎዳ ሲሆንም በየጊዜው የታሪፍ ማስተካከያ ማድረግ ወይም የተወሰነውን የታሪፍ ህዳግ አክበረው እንዲሠሩና ማኅበረሰቡ ቢጮህም የሚሰማኝ የለም በማለት እድሜ ልኩን ሲማርር መኖር የለበትም ብለዋል።
በተለይ በበዓላት ወቅት አላግባብ የሆኑ የታሪፍ ጭማሪዎች የሚበዙ ሲሆን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብም ከትራንስፖርት እጦቱ በላይ በተጋነነ ክፍያ እንደሚሰቃይ በተደጋጋሚ ይገለጻል።
አዲስ ማለዳ ስለጉዳዩ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ምላሽ የጠየቀች ሲሆን፣ ተሳፋሪዎች እንዲህ ዓይነት ተግባር ካለ መከላከል እንደሚገባቸው ብሎም ቁጥጥር ለማድረግ ያመች ዘንድ ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ የጉዞ መስመሮችን ጥቆማ ቢሰጡኝ መልካም ነው ሲል ገልጿል።
በትራንስፖርት ሚኒስቴር የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት ዳይሬክተር ይርጋ ታደሰ፣ ቅሬታ አለ ተብሎ ለመሥሪያ ቤቱ አለመቅረቡን አንስተው፣ ሆኖም ግን እንዲህ ዓይነት አግባብ ያልሆኑ ተግባራት በተለይ በበዓላት ወቅት ሊኖሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ብዙ ጊዜ መሰል ድርጊቶች የሚፈጸሙትም፣ ትራንስፖርት ሰጪዎች ከመናኽሪያ ውጪ በሕገወጥ መንገድ በሚጭኑበት ወቅት መሆኑን አመላክተዋል። ትራንስፖርት ሰጪዎች ከመናኽሪያ ሲወጡ ስምሪት ወስደው ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ሰዎች ቅሬታ ሲያቀርቡም ከየት ነው የተሳፈሩት የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
ማኅበረሰቡ ከመናኽሪያ ውጪ የሚጭኑትን ትራንስፖርት ሰጪዎች በሚጠቀምበት ጊዜ ከታሪፍ በላይ ያስከፍሉታል፣ ለዚህም ማኅበረሰቡ ተባባሪ መሆን እንደሌለበት ጠቁመዋል። አያይዘውም በሚቀጥለው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆነን የምንሠራበት ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከታሪፍ በላይ የሚፈቀዱ ጉዞዎችን በተመለከተ ይህ የሚሆነው ልዩ ጉዞዎች በሚፈጠሩበት ወቅት ሲሆን፣ ይህም እንደ መከላከያ ግዳጅ ዘመቻ፣ የበዓላት ሰሞንና ሌሎች ናቸው። በዚህ ጊዜም ብዙ ተሽከርካሪዎች ይወጡና ሲመለሱ ጭነት የላቸውም። ስለሆነም ከታሪፍ በላይ ጉዞዎች የሚፈቀዱት በእነዚህ ዓይነት ልዩ ጉዞዎች ብቻ ሆኖ፣ ጭማሬውም 25 በመቶ፣ 30 በመቶ፣ 50 በመቶ እና 60 በመቶ ድረስ ነው ብለዋል። ዳይሬክተሩ ቁጥጥሩን በማጠናከር በአጠቃላይ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል እያሰብንበት ነው፣ ነው ያሉት።
ለወታደራዊ ግዳጅ ተሰማርተዋል በሚል፣ ተሽከርካሪዎች የሉም ወይም መናኽሪያ አልገቡም እየተባለ የተጀመረ ትኬት ቀድሞ ያለመቁረጥ ሂደት እስከ አሁን እንደቀጠለ የሚናገሩም አሉ። ‹ፐርሰንት› እየተባለም ይዘው የሚመለሱት ሰው አያገኙም በሚል ከታሪፉ በላይ እንዲያስከፍሉ ቢፈቀድላቸውም፣ ባዷቸውን ሲመለሱ እንደማያዩ መንገደኞች ቅሬታ ሲያቀርቡም ይሰማል።
ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014



