በክልሎች የቆዳ ምርቶችን በሚጠበቀው ልክ መሰብሰብ እንዳልተቻለ ተነገረ

0
1094

የጨው እና የምርት ማጓጓዣ ከፍተኛ ወጪ መጠየቁን ተከትሎ የቆዳ ምርቶችን በሚጠበቀው ልክ መሰብሰብ እንዳልቻለ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል አስታወቀ።

የጨው ምርት በአግባቡ እና በተመጣጠነ ዋጋ ማግኘት ባለመቻሉ፣ ለትራንስፖርት አገልግሎት መጓጓዣ ከፍተኛ ወጪ በመውጣቱ፣ የሚወጣውን ወጪ በአግባቡ ሊሸፍን ባለመቻሉ ከክልሎች በሚጠበቀው ልክ የቆዳ ምርቶችን መሰብሰብ እየተቻለ እንዳልሆነ ታውቋል። ከትንሣኤ እና ከረመዳን በዓል ጀምሮ ምርቱን በአግባቡ ለመሰብሰብ ከንግድ ሚኒስቴር አመራሮች፣ ከቆዳ ፋብሪካ ባለቤቶች ጋር በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብርሀኑ ሰርጀቦ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አክለውም፣ በመንግሥትና በኅብረተሰቡ በኩል በእርድ ወቅት በቢላዋ መተርተር፣ መቀደድ፣ በአፈር ላይ መጎተት፣ በደም መለወስ እና ከእርድ በኋላ እንዲሁ ቆዳን በአግባቡ በአቅራቢያ ለሚገኙ ነጋዴዎች አለማስረከብ፣ በጨው ነስንሶ አለማስቀመጥ፣ ተጨማሪ ችግሮች ተብለው እንደተለዩ እና ይህን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሠራ ተገልጿል።

አሁን ባለው ሁኔታ ችግሩ የጨው ምርት እጥረት ሳይሆን ምርቱን በቅንጅት ተባብሮ በቂ በሚባል ደረጃ ማከፋፈል አለመቻል ሲሆን፣ ከጨው አቅራቢ ድርጅቶች ጋር የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ ተጠቁማል።

ከዚህ ባሻገር ኅብረተሰቡ፣ ‹‹ቆዳ የራሱና የኢትዮጵያ ሀብት ነው›› የሚለውን መርህ እና ኃላፊነት በመከተል ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ተብሏል።

በአሁን ወቅት የበሬ እና የበግ ቆዳ እጥረት እንዳጋጠመ እና ወቅቱ የትንሣኤ እና የኢድ አልፈጥር በዓል እንደመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ርብርብ እንዲያደርግ ኃላፊው አሳስበዋል።

ከአንድ ወር በፊት የቆዳ ፋብሪካዎች ተረፈ ምርት ወይም ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻዎችን ጥቅም ላይ በሚውል መልኩ መቀየር የሚያስችልና የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት የቆዳ ውጤቶችን ወደ አገልግሎት እንዲገቡ የሚያስችል ማሽን በተቋሙ ዲዛይን መደረጉ ተገልጿል። ይህ ማሽን በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ብዙም ያልተሠራበት ነው ተብሏል።

የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ውጤቶች ከዚሁ ጎን ለጎን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ከመቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር፣ በአዲስ አበባ እና በሞጆ ከተማ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን እንዴት መገንባት እንደሚቻል እና ማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ምክክር መደረጉ ተነግራል።

ከዚህ ቀደም ኢንዱስትሪዎችን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ የነበረ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን ምሁራን እና አቅም ተጠቅመው ኢንዱስትሪውን እንዴት መቀየር ይችላሉ በሚለው ላይ ለመሥራት ምክክር ተደርጓልም ተብሏል።

ይህ ደግሞ የቆዳ ምርቶችን ከመጨመር በተጨማሪ በየአካባቢው የቆዳ እና የቆዳ ውጤቶችን ክላስተር በማቋቋም ቆዳውን በዚያው በአካባቢው ተጠቅሞ ለማኅበረሰቡ በተመጣጠነ ዋጋ ለገበያ የሚቀርብበት ሂደት ላይ እየተሠራ መሆኑን ጠጠቅሷል።

ማኅበረሰቡ የቀንድ ከብቶችን በሚያርድበት ወቅት የቆዳ ምርቶችን በአግባቡ ሰብስቦ ለገበያ እንዲያውል ኃላፊው መክረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here