የጣራ ላይ የዝናብ ውሃን ሰብስቦ ምድር ውስጥ በማከማቸት ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ሊውል መሆኑን የኢትዮጵያ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ቴክኖሎጅው (Roof rain water harvesting) በተለይ በድርቅ የተነሳ የዝናብ እጥረት ባለባቸው እንደ ቦረና፣ አፋር፣ ጉጅና ሶማሌ ባሉ ቆላማ አካባቢዎች ከፍተኛ ጠቃሜታ እንዳለውና ምናልባትም ከመጪው ክረምት ጀምሮ በእነዚህ አካባቢዎች ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ዋሲሁን ዓለማየሁ፣ ቴክኖሎጂው ቀላልና ለአጠቃቀም የማያስቸግር መሆኑን ገልጸው፣ መሬት ውስጥ ጉድጓድ ከተቆፈረ በኋላ ከጣራ ላይ ውሃውን ወደ ጉድጓዱ የሚያስገባ ቱቦ/አሸንዳ ይገጠምለታል ብለዋል።
ጉድጓዱም ከብሎኬት ተገንብቶ በሲሚንቶ የተለቀለቀ ሲሆን ውሃው እንዳይተን፣ ቆሻሻ እንዲሁም ነፍሳት እንዳይገቡበት በጠንካራ የፕላስቲክ ሸራ የተሸፈነ እንደሚሆን አስረድተዋል።
ውሃውን በቀላሉ ከጉድጓዱ አውጥቶ ለመጠቀም ኹለት የእጅ ፓምፖች እንደሚገጠሙለት ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ ውሃው ለመጠጥ፣ ለጓሮ አትክልት፣ ለመስኖ፣ ለእንስሳት እና ሌሎች አገልግሎቶች ይውላል ነው ያሉት።
ውሃ ከማቆር ጋር ያለውን ልዩነት አንስተውም፣ የታቆረ ውሃ ስለማይከደን ለወባና ሌሎች ውሃ ወለድ በሽታዎች ያጋልጣል። ተኖ ሊያልቅ ከመቻሉም በላይ ከመስኖ ውጭ አያገለግልም። በዚህ ቴክኖሎጂ ግን የሚተንም ውሃ የለም፣ ውሃውም ለኹሉም ዓይነት ጥቅም ይውላል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ህንድ ያሉ አገራት ይህን ቴክኖሎጂ ቀደም ብለው በመጠቀማቸውም በምግብ ሰብል ራሳቸውን ከመቻል ጀምሮ ከፍተኛ ጥቅም እንዳገኙበት የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በኢትዮጵያም የገቢ መጠኑ ዝቅተኛ የሆነ አርሶ አደር ኹሉ በየቤቱ አስገብቶ ሊጠቀምበት የሚችል ነው ብለዋል።
አዋጭነቱና አስፈላጊነቱ በጣም የታመነበት ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ ‹‹ኢንስቲትዩቱ አሁን የሸራው በናሙና ደረጃ ነው፣ በመቀጠል ኹሉም ክልሎች በራሳቸው አቅም ቴክኖሎጂውን እንዲያለሙ እገዛና ክትትል በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል።›› ነው ያሉት።
ቴክኖሎጂው በገጠር ያሉ ቦታዎች ታሳቢ ተደርገው ይሠራ እንጂ፣ ከተማ ላይም ጥቅም ላይ የማይውልበት ምክንያት የለም ነው ያሉት። ከተማ ላይ የውሃ እጥረት መኖሩ እንዳለ ሆኖ ውሃን ለማከም ከፍ ያለ ገንዘብ ነው የሚወጣው ካሉ በኋላም፣ ‹‹ለመኪና ማጠቢያ እና ለሲሚንቶ ማቡኪያ ሳይቀር የታከመ ውሃ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው ካለን ዝቅተኛ የውሃ አጠቃቀም ልምድ ነው።›› ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የውሃ እጥረት ሲኖር ውሃ አቁረው የሚሸጡ አካላት እንደነበሩ የተነሳ ሲሆን፣ አሁንም ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚገኘው ውሃን ከመጠጥና መስኖ በተጨማሪ በርካታ ጥቅሞች እንደሚኖሩት ነው የተገለጸው።
ይህን ቴክኖሎጅ ለማበልጸግ 20 ሺሕ ብር ገደማ የፈጀ ሲሆን፣ ውሃው ከተሰበሰበ በኋላ ውሃውን ለመፈተሸ የባዮሎጂካል፣ ኬሚካል እና ፊዚካል ላብራቶሪዎች እንዳሉትም ለማወቅ ተችሏል።
ቴክኖሎጂው በተለይ አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ ውሃ እንዲያገኝ እንደሚረዳ የተገለጸ ሲሆን፣ ከኹሉም ክልሎች በተመረጡ 100 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ፋይናንስ እየተፈለገ እንደሚገኝ ተሰምቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014



