ቤቶቻቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው የሕወሓት ታጣቂዎች የተቃጠሉባቸው በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ልዩ ቦታው ጎረንጎሮ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ የሚገኙ ዜጎች ድጋፍ ባለማግኘታቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ከ80 በላይ የሚሆኑት እነዚህ ቤታቸው የተቃጠለባቸው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ ቤታቸው የተቃጠለባቸው ባሳለፍነው ጥር ወር 2014 መጀመሪያ ላይ ሲሆን፤ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ከቤተሰብ አባሎቻቸው ጋር የተስተካከለ መጠለያ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ተመስገን ውድዬ የተባሉ ግለሰብ የአምስት ልጆች አባት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ቤታቸው በሕወሓት ታጣቂዎች የተቃጠለባቸው ሲሆን፤ ድጋፍ ባለማግኘታቸው እስከ አሁን ብርድና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አሳውቀዋል።
‹‹ታጣቂዎቹ ከወደ አቦሄ ተራራ (አቡዬ ሜዳ) በድንገት መጥተው ነው ቤታችንን ያቃጠሉት።›› ያሉት ተመስገን፤ ነፍሳችንን ለማዳን ከመሸሽ ውጭ ከመቃጠል ያተረፍነው ንብረት የለም። ኹሉም ተቃጥሏል›› ነው ያሉት።
በወቅቱ የኹለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተመስገን ያስታወሱ ሲሆን፤ ሰዎቹ የሞቱትም ከታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት መሆኑን አብራርተዋል።
የቃጠሎው አደጋ የደረሰው ቀን ላይ በመሆኑ በዱር ተሰማርተው ስለነበር በእንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ማወቅ ተችሏል።
ሌላኛው ብርሃኑ ማረው የተባሉት ግለሰብ በበኩላቸው፤ ቤታቸው እንደተቃጠለባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረው፤ ቤታቸው ከተቃጠለባቸው ቦታ ላይ የጠጋገኗትን ትንሽ የሳር ጎጆ ቤት ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ‹‹አቅም የለኝም እንዴት ልሥራው” ሲሉ ተናግረዋል።
አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የጠቀሱት ብርሃኑ፤ ‹‹ቤቴን በጭቃ እንዳልመርግ እንኳ ውሃ በቅርቡ የለም›› ሲሉ ነው ችግራቸውን ያብራሩት።
ከነዋሪዎቹ በተገኘው መረጃ፤ 17 አባወራዎች ከ80 በላይ የሚሆኑ የቤተሰብ አባላት የተስተካከለ የመጠለያ ችግር እንዳለባቸው ማወቅ ተችሏል።
በተቃጠሉት ቤቶች ምትክ ትንንሽ ሳር ቤቶች የተሠሩ ቢሆንም፣ ከብርድና ከፀሐይ ሊከልሉ የማይችሉና የተሸነቋቆሩ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ ተመልክታለች።
በተያያዘ ዜና ትራንስፖርት ክፍያ ከዕጥፍም በላይ እንደጨመረባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የትራንስፖርት ጭማሪ አለ የተባለው ከቆቦ ወደ ተኩለሽ ከተማ በሚደረገው ጉዞ ነው።
ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት፤ በአነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ታሪፉ 30 ብር ሲሆን፤ ሰሞኑን ግን እየከፈሉ ያሉት 100 ብር መሆኑን ነው።
ዓለምነሽ ሲሳይ የተባሉት እናት፣ ‹‹የሚያስከፍሉን እነሱ በፈለጉት መጠን ነው። አንዳንድ ጊዜ 50 በሌላኛው ጊዜ ደግሞ 100 ብር ነው የሚያስከፍሉን።›› ብለዋል።
አክለውም፤ በጦርነት ከበባ ውስጥ የነበረ ማኅበረሰብ ሊታገዝ ሲገባ፤ ይባስ ብሎ ከታሪፍም በላይ በሆነ የትራንስፖርት ክፍያ እየተሰቃየ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከቆቦ ወደ ተኩለሽ ከተማ ለመጓዝ ክፍያው 100 ብር መሆኑንም አዲስ ማለዳ በቦታቸው ተገኝታ ማረጋገጥ ችላለች።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ከከተማው አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት በአካልም ሆነ ስልክ በመደወል ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።
ተኩለሽ፤ ጎሮንጎ፤ ቀይ አፈር፤ አቦሄ ሜዳ የሚባሉት ቦታዎች በራያ ቆቦ ወረዳ ውስጥ በደጋማው ክፍል የሚገኙ ስፍራዎች ሲሆኑ፤ ሕወሓት ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014


