በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ ኦነግ ሸኔ በሚሰነዝረው ጥቃት ነዋሪዎቹ መፈናቀላቸውን ተከትሎ፤ በወረዳው ያለው ማሳ የመታረሻ ወቅቱ ማለፉ አሁን ካሉበት ሁኔታ ይበልጥ የከፋ ችግር ሊያመጣባቸው እንደሚችል ነዋሪዎቹ ስጋታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ስሜ ባይጠቀስ ያሉ የአዲስ ማለዳ የመረጃ ምንጭ፤ ‹‹መሬቱ ዝም ብሎ ጫካ እየለበሰ ነው። ቦታውንም ለቀነዋል። መሬቱም ከጥቅም ውጭ እየሆነ ነው። የማረሱም የመዝራቱም አቅም የለንም፣ ገንዘባችንን ጨርሰናል። አሁን ደግሞ የርሃብ ጦርነት በፊታችን ተጋርጦ ነው ያለው›› ብለዋል።
ያልታረሰው ማሳ ቁጥር ስፍር የለውም የሚሉት የአካባቢው ነዋሪ፤ ‹‹በቀበሌ ብሎ መግለጽ ይሻላል እንጂ በሔክታር መግለጽ ይከብዳል›› ሲሉ ነው የመሬቱን ስፋት የገለጹት።
አክለውም፤ መደበኛ ዘር መዘራት የሚጀምረው ግንቦት እኩሌታ ላይ መሆኑን አውስተው፤ የማሳ ጽዳትና ማለስለሻው ወቅት እንዳለፈና ይህ ደግሞ ለማሳው ጾም ማደር ምክንያት እንደሚሆን አስረድተዋል።
ሌላኛው ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው፤ ማሳው ወቅቱ ካለፈበት ሌላ እንደ ጤፍ፤ ሽምብራ ዓይነት ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን ማብቀል እንደማይችል ተናግረዋል።
በተያያዘም፤ ማንኛውንም ዘር ለመዝራት ማሳው የሚጸዳው ካለንበት ወር በፊት እንደነበር የገለጹ ሲሆን፤ አሁን ግን መሬቱ አንድ ጊዜ እንኳ እንዳልታረሰ ነው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።
ነዋሪዎቹ የገለጹት፤ በተለይም የበቆሎ መሬት የሚታረሰው ቀድሞ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት ምንም የታረሰ መሬት እንደሌለ ነው። እንዲሁም የሰሊጥ፤ የአኩሪ አተር፤ የቦለቄ መሬት ደግሞ የሚጸዳው ቀደም ብሎ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ግን ማሳ ማጽዳት ቀርቶ በዚያ አካባቢ ሰው ከተገኘ እንደሚታገት አብራርተዋል።
‹‹ምንም ነገር እየተሠራ አይደለም። ለዘር የታሰበ ነገር የለም።›› የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከዚህም በተጨማሪ በሊሙም ሆነ በጊዳ ወረዳ የማዳበሪያና የዘር አቅርቦት እንደሌለም ጠቁመዋል።
አንድ አርሶ አደር እስከ 10 ኩንታል ማዳበሪያ ነው የሚፈልገው ያሉት የሊሙ ወረዳ ነዋሪ፤ ‹‹በፊት በኮንትሮባንድ ይገባ ነበር፤ አሁን የለም›› ብለዋል። አክለውም፣ በአንዳንድ ቦታዎች የማዳበሪያ አቅርቦት ቢኖርም ዋጋው ግን እንደናረ ነው የተናገሩት።
ነዋሪዎቹ ባለፈው ዓመት አንድ ኩንታል ዳፕ ከአንድ እስከ ኹለት ሺሕ ብር ይገዙ እንደነበር አስታውሰው፤ በ2014 ግን የአንድ ኩንታል ዳፕ ዋጋ አምስት ሺሕ ብር እንደገባ ነው ያስታወሱት። በመሆኑም አርሶ አደሩ ማረስ አለመቻሉን ተገንዝቦ መንግሥት መፍትሄ አለመስጠቱ ለወደፊት ተረጂ/ድጋፍ ፈላጊ ሰዎችን እንዲጨምሩ የሚያደርግ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ማሳው ላይ ሳይዘራ ማደሩ ጉዳቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰው ነው የሚሉት ተፈናቃዮቹ፤ ዘይት እንኳ ማምረት የሚቻለው አኩሪ አተርና ሰሊጥ ሲመረት ነው። በአኩሪ አተር ምርት የሚታወቀው መሬት ደግሞ ሳይታረስ ሊከርም ነው ብለዋል።
በአገር ውስጥ የሚገኙ 15 ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች በዓመት ከኹለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ አኩሪ አተር እንደሚያስፈልጋቸው የምግብ መጠጥና ፋርማስዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2013 ያወጣው ጥናት ያሳያል።
በተያያዘም ሰሊጥ ከፍተኛውንና 48 በመቶ የሚሆነውን የቅባት እህሎች የዘይት ይዘት መጠን እንደሚይዝም ከተቋሙ በተገኘው መረጃ ተመላክቷል። ታዲያ ነዋሪዎቹም ይህን መረጃ አስታውሰው ጉዳዩ መፍትሄ ካልተሰጠው ጉዳቱ ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል እንደሚሆን አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ነዋሪዎቹ የገለጹት፣ ምንም እንኳ ከሸኔ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አመራሮች ‹መንግሥት ሊለያቸው ባይችልም›፤ ተፈናቃዮች ወደየቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን ነው።
ለአብነትም ጊዳ ወረዳ የነበሩ የመንደር አራት፤ በጉትን የነበሩ የመንደር አምስት እና የመንደር 10 ተፈናቃዮች ወደየ ቀየአቸው ተመልሰዋል ተብሏል። የጊዳ ወረዳ ተፈናቃዮች እየተመለሱ ቢሆንም፤ የአንዶዴ ነዋሪዎች ግን ገና መሆናቸውንም ማወቅ ተችሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014


