መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየላሊበላ ታሪካዊ ሙዝየም ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ በሚፈጅ ወጪ ግንባታው ተጀመረ

የላሊበላ ታሪካዊ ሙዝየም ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ በሚፈጅ ወጪ ግንባታው ተጀመረ

ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ በሚፈጅ ወጭ የላሊበላ ታሪካዊ ሙዚየም ግንባታ መጀመሩን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳዳሩ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የፈረንሳይ መንግሥት ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከሚያደርገው ጥገና ጎን ለጎን ባገኘው የ35 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አማካኝነት የላሊበላ ታሪካዊ ሙዝየም ግንባታ ሥራ የተጀመረ ሲሆን፣ አጠቃላይ ግንባታው ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልገው የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሙሉጌታ አዳሙ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የሙዝየሙ ግንባታ በአገር ውስጥ ተቋራጮች አማካኝነት ከተማ አስተዳደሩ ያስጀመረው ሲሆን፤ ተጨማሪ የክልሉን እና የፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ርብርብን እንደሚጠይቅም ኃላፊው ተናግረዋል።
ግንባታው ከኹለት ሳምንት በፊት የተጀመረ ቢሆንም፤ ሙሉ ለሙሉ የሚጠናቀቅበት ቀነ ገደብ ግን እንዳልተቀመጠለት ሙሉጌታ አብራርተዋል።

የሙዝየሙ ሥም እስከ አሁን ባለው የቅዱስ ላሊበላ ሙዝየም ተብሎ እንደሚጠራ እና ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ግን የሙዝየሙ የመጠሪያ ሥም ሊቀየር የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ነው ለማወቅ የተቻለው።

ሙሉጌታ በተጨማሪም የሙዝየሙን ግንባታ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ለማጠናቀቅ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ የፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲሁም የተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶችን ርብርብ ይጠይቃል ሲሉ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

ይህ ሙዝየም ጥሩ በሚባል ደረጃ ግንባታው ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን፤ ግንባታውም ዓለም ዐቀፋዊ ደረጃን በጠበቀ መልኩ እንደሚሠራ ነው የተብራራው።
በመሆኑም የተለያዩ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት ለሙዝየሙ ግንባታ እና ማስፈፀሚያ የሚውል ገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት መጠየቁም ተጠቁሟል።

ኢትዮጵያ ባሳለፈችውና አሁንም በምትገኝበት ጦርነት እንዲሁም የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት እድሳት ተቋርጦ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ጉዳዩ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ሙሉጌታ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሙሉጌታ ለአዲስ ማለዳ በገለጹት መሠረት፤ ከዚህ በተጨማሪ በኮቪድ 19 እና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት እድሳት ለማስቀጠል በ24 የተለያዩ ቦታዎች ላይ የቅድመ ጥገና ሥራ ለመሥራት አስፈላጊ ቁሳቁሶች መግባታቸውንም ማወቅ ተችሏል።

በሚደረገው ጥገና ዙሪያ ከማኅበረሰቡ ጋር ምክክር መደረጉን የተናገሩት ኃላፊው፤ የቀድሞ ይዘቱን ሳይለቅ በአገር በቀል ቁሳቁሶችና ግብዓቶች ጥገና ይደረጋል ብለዋል።
የቅድመ ጥገናው አንገብጋቢ ችግሮችን ቅድሚያ መፍትሄ ለመስጠት የሚጀመር ሲሆን፤ ዋናው የጥገና ሥራም ጎን ለጎን ተግባራዊ እንደሚደረግ ተጠቅሷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች