በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ባምባሲ ወረዳ ከ150 በላይ ዜጎች መታሰራቸው ተሰማ

0
839

ባሳለፍነው ሚያዚያ 21/2014 ስድስት ሴቶች ተደፍረዋል

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ባምባሲ ወረዳ መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ወደ አማራ ክልል እንዲወጡ የተገደዱ ከ150 በላይ ንጹሃን ዜጎች በባምባሲ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን ታማኝ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የባምባሲ ወረዳ ነዋሪ ለበርካታ ዓመታት ኑሯቸውን በወረዳው የመሠረቱ የአማራ ተወላጆች በወረዳው አመራሮች አማካኝነት ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ እየተገደዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

መረጃውን የተናገሩት ነዋሪው እንደገለጹት ከሆነ፤ እስከ አሁን በርካታ ነዋሪዎች ወደ አዲስ አበባ ተሳፍረው እንዲላኩ የተደረጉ ሲሆን፤ መሳፈሪያ ብር የሌላቸው ሰዎች ግን በእስር ቤት መሆናቸውን ነው ያሳወቁት።
በባምባሲ ወረዳ ኑሯቸውን ከመሠረቱ 14 ዓመት እንዳስቆጠሩ ያብራሩት ቅሬታ አቅራቢው፤ ቤት ንብረታቸውን ለቀው እንዲወጡ መገደዳቸውን ገልጸው ለጊዜው በዘመድ ቤት ተጠግተው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

‹‹በዋነኝነት ይህን ድርጊት የሚፈጽሙት ከዞን እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች ናቸው።›› ያሉት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፤ በተደጋጋሚ ቅሬታ ለአመራሮቹ ቅሬታውን ቢያሰሙም ‹‹ለቃችሁ ውጡ። ካልሆነ ለሸኔ ተላልፋችሁ ትሰጣላችሁ›› የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ነው የገለጹት።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ፤ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ በይበልጥ እየተገደዱ ያሉት ከሦስት ሳምንት ጀምሮ መሆኑን ነው።

ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ በበኩላቸው ካሳለፍነው ሚያዚያ 05/2014 ጀምሮ ለሥራ ወደ ባምባሲ ወረዳ የሄዱና ነባር ነዋሪዎች ወደ አማራ ክልል ተሳፍረው እንዲሄዱ እየተደረጉ ነው ብለዋል።
አስከትለውም መሳፈሪያ የሌላቸው ሰዎች መንዲ አካባቢ ወደሚገኙ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እየተላለፉ እየተሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለአብነትም ባሳለፍነው ሚያዚያ 05/2014 በኹለት አውቶብስ የተሳፈሩ 60 የሚሆኑ ሰዎች በትእዛዙ መሠረት ቤታቸውን ለቀው ወደ አማራ ክልል እንዲሄዱ ቢነገራቸውም መሳፈሪያ ብር ስለሌላቸው መንዲ ወደሚገኙ የሸኔ ታጣቂዎች ተላልፈው ተሰጥተዋል ነው ያሉት።
የመረጃ ምንጩ በተያያዘም ከዚያ ወዲህም ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ በርካታ ሰዎች ወደ መንዲ እንደተላኩና እስከ አሁን ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እንዳልተቻለ ነው የተናገሩት።

‹‹የሚሰማ ሰው ስለታጣ ነው እንጂ የሚፈጸመው ግፍ ቀላል አይደለም።›› የሚሉት ነዋሪው፤ ‹‹ሕጉ ማንኛውም ሰው በፈለገው ቦታ የመንሳቀስ ሙሉ መብት እንዳለው ይደነግጋል። ታዲያ ይህ ግፍ ሲፈጸም ተግባራዊ የማይደረገው ለምንድን ነው?›› የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
በሌላ በኩል ‹‹ሽቦላ›› በተባለቸው የባምባሲ ወረዳ ቀበሌ ባሳለፍነው ሚያዚያ 21/2014 ስድስት ሴቶች ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግተው መደፈራቸውና ከኹለት ቀን በኋላ መለቀቃቸው ነው የተመላከተው።

የመንግሥትን ምላሽ በአስቸኳይ እንደሚሹ ያሳሰቡት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ እስከ አሁን (ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት እለት ድረስ) በባምባሲ ወረዳ የሚገኙ የአማራ ተወላጆች እየታሰሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ለጉዳዩ ምላሽ እንዲሰጡ ያነጋገረቻቸው የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ መለስ በየነ በበኩላቸው፤ ‹‹አሁን መኪና ላይ እየወረድኩ ነው። ቆይቼ እደውላለሁ›› ያሉ ሲሆን በድጋሚ ሲደወል ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆኑም።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here