የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዳለበት አስታወቀ

0
605

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዳለበት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም፣ ጽሕፈት ቤቱ በትንሽ የሰው ኃይል በርካታ ሥራዎችን እንደሚሠራ ገልጸው፣ አሁን ላይ ግን ባለው የበጀት እጥረት ብዙ ሥራዎችን መሥራት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል።

እስከ አሁን ትልቁ በጀቱ (የዚህ ዓመት በጀቱን ጨምሮ) 22 ሚሊዮን ብር መሆኑን ጠቁመውም፣ ከዚህ ውስጥ 14 ሚሊዮን ገደማ የሚሆነው በደሞዝና ሌሎች ጉዳዮች እንደሚወጣና ይህም ተቋሙ ከሚሠራቸው ሥራዎች አንጻር ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዳለበት አመላክተዋል።
ሲቋቋምም አምስት ሚሊዮን ብር ነበር በጀቱ የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹በጀት ስንጠይቅ በጀት የለም አስተባብራችሁ ሥሩ ነው የምንባለው›› ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹በዚህ በጀት ከሕዝብ የሚመጡ ፕሮጀክቶችን ሳይቀር መሸፈን አንችልም። ሰፊ ሥራ መሥራትም ያስቸግራል።›› ካሉ በኋላ፣ በዚህ የተነሳ ከዚህ የበለጠ መሥራት እንዳልተቻለና ታላላቅ ፕሮጀክቶችም እየቀሩ መሆኑን አብራርተዋል።
የጽሕፈት ቤቱ ዋነኛ ዓላማ ለሕዳሴ ግድቡ ገቢ ማሰባሰብ ብቻ አይደለም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ሕዝቡ የሞራል ድጋፍ እንዲሰጥ፣ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው፣ ግድቡ የሰላም አስተዋጽኦ እንዲኖረው ከመሥራት ጀምሮ ግድቡ ሲጠናቀቅ በደለል እንዳይሞላ የአካባቢ ጥበቃ ሥራም ይሠራል ሲሉ ነው የገለጹት። ለዚህም በቂ በጀት ሊኖር እንደሚገባ አስምረውበታል።

ካለው ከፍተኛ የበጀት እጥረት ጋር ተያይዞም በየጊዜው ከፍተኛ የሠራተኛ ፍልሰት መኖሩን ጠቁመዋል። በበጀት እጥረቱ የሠራተኞች ደሞዝ አነስተኛ መሆኑን ተከትሎም፣ ከዚህ በፊት የነበሩ ብዙ ዳይሬክተሮች እና ሠራተኞች ተቋሙን ለቀው ሄደዋል ነው ያሉት።
‹‹በወቅቱ የሠራተኞች ደሞዝ ከጉምሩክ ተቋም ጋር ተመጣጣኝ ሆኖ ነበር የተተከለው። ይህ ግን በወቅቱ በነበሩ ባለሥልጣናት እሳቤ እንጂ በዝርዝር ጥናት የተሠራ ባለመሆኑ አሁን ያለው የደሞዝ እርከን ከጉምሩክ ጋር ሲነጻጸር በተመሳሳይ የሥራ ሂደት ከ10 ሺሕ ብር ያላነሰ ልዩነት አለው ሲሉም አስገንዝበዋል።

‹‹ሠራተኞች በየዓመቱ ኮንትራት እየፈረሙ የሚሠሩ በመሆናቸውም እንደሌሎች ተቋማት የትምህርት እድልና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ማግኘት አይችሉም። የቋሚነት ጥያቄ ሲነሳም እናንተ ኮንትራት ናችሁ የሚል ምላሽ ነው የሚሰጠው።›› ብለዋል።
ጽሕፈት ቤቱ ጥያቄ ማቅረብ ከጀመረ የቆየ መሆኑን አንስተውም፣ ጥያቄዎች በየጊዜው ለሚመለከታቸው አካላት በየጊዜው ይላካሉ። ሆኖም ግን ተከታትሎ የሚያጸድቅ ባለመኖሩ እስከ አሁን ውሳኔ ሳይሰጥ ቆይቷል ነው ያሉት።

ሥራ ላይ ያለው የኮንትራት ሕግ ባለመሻሻሉም ሠራተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንደማይከፈላቸው፣ የሥራ ዋስትና ስለሌላቸውም ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው እንደሚያሳስባቸው፣ የደመወዝ ዕድገት ማስገኘት እንዳልተቻለና ሠራተኞች ተረጋግተው ለመሥራት መቸገራቸውም ተገልጿል። በዚህም አንድ ሠራተኛ ብቻ ያላቸው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ስለመኖራቸውም ተጠቁሟል።

‹‹አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ይታወቃል። ቢሆንም ግን ተቋሙ ካለበት አገራዊ ኃላፊነት አንጻር ያሉት ችግሮች ቢስተካከሉ ጽሕፈት ቤቱ የበለጠ ይሠራል። ለሠራተኞች ሞራልም ጥሩ ነው።›› ሲሉ ዳይሬክተሩ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሕዳሴ ግድቡ ያለውን ከፍተኛ ድጋፍ መስመር ለማስያዝና በተገቢው ሁኔታ ለማስተባበር ኃላፊነት ያለው ገለልተኛ ተቋም ማቋቋም በማስፈለጉ፣ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በወቅቱ በነበረው የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አማካይነት የመንግሥት ጊዜያዊ ፕሮጀክት ሆኖ በአዋጅ እንደተቋቋመ ተጠቁሟል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እስከ መጋቢት 2014 ድረስ ከ16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here