የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ጋር በተወያየበት ወቀት ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዳደርግ ጠይቋል፡፡
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ(ፕ/ር) የኮሚሽኑን ዓላማና ምስረታ፣ አወቃቀር፣ የአገራዊ ምክክር አሰራር ሂደት፣ የእስካሁኑ ቅድመ-ዝግጅት ምዕራፍ ክንውኖችና ቀጣይ የዝግጅትና ትግበራ ሂደትን ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ማበራራታቸውን ኢኤአ ዘግቧል፡፡
በሕዝብ ጥቆማ የተመረጡ 11 አባላትን ያቀፈው ኮሚሽኑ በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ከታች ወደ ላይ አካታችና አሳታፊ ውይይት በማድረግ አገራዊ መግባባት እውን እንዲሆን ማስቻል ነው ብለዋል። የኮሚሽኑ ተልዕኮ ይሰምር ዘንድ ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየት፣ የቀደሙ ሁለት ኮሚሽኖችን ሰነድ በግብዓትነት መጠቀምና በብሔራዊ ውይይት ልምድ ካላቸው አገራት ተሞክሮ ይቀስማል ብለዋል።
ሌሎች ኮሚሽነሮችም ስኬታማ፡ አካታችና ውጤታማ አገራዊ ምክክር በማድረግ ኢትዮጵያን በፅኑ መሰረት ለማንበር ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል። ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ያገኘ፣ የተለመደ ልሂቃን ውይይት ሳይሆን ከታኛው ህብረተሰብ ጀምሮ ሁሉን አሳታፊና ሀሳብ የሚንሸራሸርበት፣ በግልፀኝነትና ተጠያቂነት መርሆች የሚመራ ነው ብለዋል።
አገራዊ ጉዳዮች በሚገባ ውይይት ተደርጎባቸው ብሔራዊ ዕርቅን ዕውን ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ዝግጀት ምዕራፍ እየገባ መሆኑን ተናግረዋል። አገራዊ ምክክሩ የሚመራው ካለምንም የውጭ ጣልቃገብነትና ጥምዘዛ በኢትዮጵያዊያን እንደሆነና ለዴሞክራሲም ትልቅ አሻራ ጥሎ የሚያልፍ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት የሁሉንም ወገን አካታችነት፣ ገለልተኝነት፣ በፋይናንስና መሰል ጉዳዮች ጥያቄዎችን አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል። በውይይት መድረኩ ኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ለማድረግ የያዘችው ፕሮጀክት ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም በቅጡ ተረድተናል ማለታቸውን ኢዜአ አስነብቧል፡፡
በኢትዮጵያ ከሩሲያ አምባሳደር የቭጊኒ ተርኪን ከኮሚሽነሮቹ ጋር በመወያየታቸው ደስታቸውን በመግለጽ፣ ኮሚሽኑ ብሔራዊ እርቅን እውን በማድረግና የኢትዮጵያን ሕልውናዋን በማረጋገጥ ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ካትሪን ሶዚ(ዶ/ር) ለተመድ ጠንካራ አባሉ ለሆነችው ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ይደግፋል ብለዋል። በአገራዊ ምክክር ሰላምና መረጋጋት ከተረጋገጠ ለችግር ተጋላጭ ወገኖች መጠን ስለሚቀንስ ለምክክሩ ስኬታማነት ተመድ የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014


