“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
አንድ ነገር መሆን ካለበት ጊዜና ቦታ ውጪ ከሆነ ዋጋ የለውም ወይም ውጤት አያስገኝም። ከዛም ባሻገር የጊዜ፣ የጉልበት፣ የገንዘብ ወዘተ ብክነት ነው የሚሆነው። በሴቶች ጉዳይ ዙሪያ ተመሳሳይ ጥንቃቄን የሚሹ የተለመዱ አካሄዶች አሉ። አንዱና ለዛሬ ላነሳ የወደድኩት በተለያየ ጊዜ የሚሰጥን ሥልጠና ነው።
እንደሚታወቀው በስርዓተ ጾታ ዙሪያ የተለያዩ ሥልጠናዎች በየጊዜው ይሰጣሉ። እነዚህም በተለይ ለመንግሥታዊ እንዲሁም መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ሲሰጥ፣ አንዳንዴም በእነርሱ አስተባባሪነት ይዘጋጃል። ይህ ይበል የሚያሰኝ ነው። እንዲህም ሆኖ እውነተኛ የሚባሉ ለውጦች ለመምጣት ደጅ እያስጠኑ ይገኛሉ።
ልብ ያልተባሉ ነገር ግን ጾታዊ ትንኮሳ በብዛት የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ግን የተረሱ ይመስላል። ሥልጠና እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በእርግጥ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ከታመነ፣ መሬት ወርዶ ማኅበረሰቡ ጋር መሥራት ተገቢ ነው። ማለትም አሠራርና ሕጎች ላይ ለውጥን ከማምጣት፣ በየተቋማቱ ያሉ ችግሮችን ከመጋፈጥ ጎን ለጎን፣ ሊነቁ የሚገቡትን አስተውሉ ብሎ መቀስቀስ ያሻል።
ይህን እንድል ያደረገኝ ከዚህ ቀደም <ሴቶች ለብቻቸው ወደ ሆቴል አይገቡም> የሚል ሕግ ያለበትን ሆቴል ጉዳይ ካነሳን በኋላ ነው። የጥበቃ ሥራ ላይ ያሉ ሰዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ የታክሲ ረዳቶች፣ ባለሱቆችና የመሳሰሉትን በስርዓተ ጾታ ግንዛቤ መስጫ አውዶች ላይ ማስታወስና ማካተት ተገቢ ነው።
እነዚህና መሰል የማኅበረሰቡ ክፍሎች ምን እንደሚያስቡና እንደሚያውቁ መገመት አይቻልም። ምንአልባት አልፎ አልፎ በሚድያ የሚሰሙትን ብቻ ይዘውና ያንን በጥልቅ ሳይመለከቱ እንዲሁ በጥራዝ ነጠቅ፣ <አሁንማ ጊዜው የእናንተ ነው፣ ሁሉም ነገር ለሴቶች ነው> የሚሉ በርካታ ናቸው።
እነዚህ ሰዎች እንደወረደ ያለውንና ማኅበረሰቡ ለስርዓተ ጾታ ያለውን ዕይታ ልንመለከትባቸው እንችላለን። ንቃት የሚገባውን የረሳን ይመስላል። የሚገባው ስንል ተገቢ የሆነውን ለማለት እንደሆነ ያዙልኝ። ከላይ ከላይ ብቻ ስንል፣ ከታች ሰፊው ማኅበረሰበ አብሮ በሚኖርበት መስክ ያለውንም በሚገባ ማጤን ጠቃሚ ነው። ይህም የቱ ጋር ነው ችግር ያለው ብሎ ከመለየት የሚጀምር ነው።
አንድ ጊዜ በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫዎች ውስጥ (አውቶብስ፣ ሀይገር፣ ታክሲ) በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በሚመልከት ንግግሮች ይደርጉ ነበር። ይሄኔ የትራንስፖርት አማራጮችን ማስፋት የሚል ምክረ ሐሳብ ቀረበ። ነገር ግን መፍትሄ አልተገኘም። ጉዳዩ አሁን ምን እንደደረሰ መረጃው ባይኖረኝም፣ ለውጥ እንዳልመጣ ግን ራሴም እንደትራንስፖርት ተጠቃሚ ምስክር መሆን እችላለሁ።
ነገር ግን አገልግሎት ሰጪዎቹ ተጠርተው ምን ይደረግ ቢባሉ፣ ሐሳብ ቢያዋጡ ችግሩ በቀለለ ነበር። ለዚህ ነው ማንቂያ፣ ሥልጠና ሲባል ሁሉን መመልክት ይገባል ያልኩት።
መቅደስ ቹቹ
ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014


