መንግሥት ለጋዜጠኞች ደኅንነት ዋስትና ይስጥ!

0
610

ኢትዮጵያ ለጋዜጠኞች እና ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት መረጋገጥ በሯን ዳግም ከከፈተች ካንድ ዓመት በላይ አልሆናትም። ሆኖም ዛሬም ጋዜጠኞች እና ብዙኀን መገናኛዎች በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው ተደቅነውባቸዋል። ሌላው ቀርቶ በቅርቡ በጥቂት ቀናት ልዩነት ኹለት ጋዜጠኞች መዋከብ፣ ድብደባና እስር አጋጥሟቸዋል።

ጋዜጠኛ ምስጋና ጌታቸው የሳምንታዊዋ ኢትዮጲስ ጋዜጣ ባልደረባ ሲሆን ረቡዕ፣ ግንቦት 14 “ቤት የፈረሰባቸው” ግለሰቦች ጉዳያችንን ዘግቡልን የሚል ባደረሱት ጥቆማ መሠረት በቦታው ሲደርስ የኅብረተሰብ ሰላምና ደኅንነት ሊጠብቁ በሚገባቸው የፖሊስ አባላት መዋከቡና አካላዊ ጥቃት ወይም ድብደባ ሰለባ መሆኑን ተናግሯል፤ ምንም እንኳን ፖሊስ በጋዜጠኛው ላይ ድብደባ አላደረስኩም ብሎ ቢያስተባብልም።

ሌላውና ሰፊው የመገናኛ ብዙኀንን ትኩረት የሳበው አርብ፣ ግንቦት 16 አመሻሽ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ፣ የሰንዳፋ በኬ 02 ፖሊስ ጣቢያ አባላት አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው አሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ድረስ ከነሙሉ ትጥቃቸው በመሔድ በሥራ ላይ የነበረውን ጋዜጠኛ ታምራት አበራን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ነው። ጋዜጠኛ ታምራት ለሦስት ቀናት ከታሰረ በኋላ ሰኞ፣ ግንቦት 19 ፍርድ ቤት ሳይቀርብና ክስ ሳይመሠረትበት በመታወቂያ ዋስ ተለቋል።

የአሐዱ ሬዲዮ ሥራ አስኪያጅ ጥበቡ በለጠ ጋዜጠኛ ታምራት ታስሮ የተወሰደበት አግባብ ትክክል እንዳልሆነ ሲያብራሩ፥ “የታጠቀ የፖሊስ ኃይል ስቱዲዮ ድረስ በመግባት ታምራትን መውሰዳቸው ሌሎች ባልደረቦቻችን ላይ ጭምር የማሸማቅቅ ሥራ ነው የተሠራው” በማለት ነው። ይህም በሠራተኞቻቸው ሥነ ልቦና ላይ መረበሽ እንዳስከተለ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ሕግና ስርዓት አለ በሚባልበት አገር እና በሕጋዊነት በሚሠራ፣ አድራሻው በይፋ በሚታወቅ፣ በዘገባዎቹ ላይ ቅሬታ ሳይቀርብበት፣ በተቆጣጣሪው በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በኩል ምንም ዓይነት አስተያየት ሳይደርሰው፣ ከምንም በላይ ደግሞ የቃል ወይም የጽሑፍ የፍርድ ቤት መጥሪያ ቀድሞ ሳይደርሰው ወይም ደርሶት ላለመቅረብ እምቢታን ባላሳየ የመገናኛ ብዙኀን ተቋም ላይ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ መፈጠሩ ኀላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን ቀድሞ ኢትዮጵያ ትታወቅበት ወደነበረው የአፈና ስርዓት የመመለሳችን ምልክት እንዳይሆን በሚል ስጋቷን ትገልጻለች።

ወንጀል ሠርተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ጋዜጠኛም ሆኑ አልሆኑ በፖሊስ ወይም በዐቃቤ ሕግ በሚፈለጉበት ወቅት ሕግና ስርዓትን በጠበቀ መልኩ በቃል ወይም በጽሑፍ ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም ደግሞ የፍርድ ቤት ጥሪ ወጥቶባቸው ከሆነ ሕጉ በሚያዘው መሠረት በፍትሓዊ መንገድ መከናወን ይገባዋል። ይህም መሠረታዊ የሕግ ዕውቀት የሚጠይቅ በመሆኑ በየዕለቱ ሕግን ለሚያስከብሩ የፖሊስ ተቋም አባላት ይጠፋቸዋል ብላ አዲስ ማለዳ አታምንም።

በመሆኑም የጋዜጠኛው አያያዝ ሕጋዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ መካሔድ እንደነበረበት አዲስ ማለዳ ፅኑ አቋሟን ትገልልጻለች። በጋዜጠኛው ላይ የተካሔደው ከእገታ በምን እንደሚለይ ግልጽ አይደለም። ዛሬ የኦሮሚያ ፖሊስ በቀደደው መሥመር ሌሎች የክልል ባለሥልጣናት የሚፈልጉትን በየትኛውም ክልል ያለ ጋዜጠኛን እንደፈለጉ አንጠልጥለው መሔድ ላለመቻላቸው ምንም ዋስትና የለም።

በኢትዮፒስ ጋዜጣ ወይም በአሐዱ ሬዲዮ ጋዜጠኞች ላይ የደረሰው ጥቃት በመላው የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ላይ ተፅዕኖ እንዳደረሰ አዲስ ማለዳ ታምናለች፤ በመሆኑም መደገም የለበትም በማለት በፅኑ ታወግዘዋለች።

ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የጋዜጠኛ ሲኦል ከሆኑ አገራት ተርታ የምትመደብ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ይህም የአገሪቱን ገጽታ ክፉኛ መጉዳቱ ይታወቀል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ይህንን የጠለሸ ታሪክ በከፍተኛ ደረጃ ከመለወጥ አልፎ ኢትዮጵያ በሙያቸው ምክንያት አንድም ጋዜጠኛ ያልታሰረባት እንድትሆን አስችሏታል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን መሻሻል የጋዜጠኞች አያያዝ ከግምት ባስገባ መልኩ በቅርቡ ዓለም ዐቀፍ የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ እንዲከበር መደረጉ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥም ቢሆን በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ። ሕዳር ወር ላይ ጋዜጠኞች በጋምቤላ የወረዳ ባለሥልጣናት አጭር እስር እና እንግልት ደርሶባቸዋል። ሌላ ጊዜ ከድሬዳዋ የሚመጡ ጋዜጠኞች መንገድ ላይ እገታ ገጥሟቸው ነበር። በየካቲት ወር የለገጣፎ “የጨረቃ ቤቶች መፍረስን” ለመዘገብ የሔዱ ኹለት የመረጃ ቲቪ ጋዜጠኞች የመደብደብ አደጋ ደርሶባቸዋል። እነዚህ ሁሉ ችግሮች የደረሱት መንግሥት ለጋዜጠኞቹ የመሥራት መብትን ከደኅንነት ጥበቃ ጋር ማጎናፀፍ ባለመቻሉ ነው።

በመጨረሻም አዲስ ማለዳ ማንኛውም በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በሕጋዊና ሕጋዊ ስርዓቱን በተከተለ መንገድ መጠየቅ እንዳለባቸው ማስገንዘብ ትፈልጋለች። በአሐዱ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ እንዲሁም እንደዚህ ዓይነት የተዛባ አመለካከትና የሥራ አፈፃፀም የሚያደርጉ የክልል ወይም የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ማስተማሪያ እንዲሆን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል በይፋ የጋዜጠኛ አያያዙን ማውገዝ እንዲሁም ይፋዊ ይቅርታ መጠየቅ አለበት ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በተጨማሪ ጋዜጠኞች በነጻነት ሥራቸውን እንዲሠሩ መንግሥት የደኅንነት ጥበቃ እና ከለላ በመስጠት ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ታደርጋለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here