የ‘ለሁሉ’ አገልግሎት ኮንትራት ውል ያላግባብ ‘ለክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ’ ተላልፏል

0
1136

የ“ለሁሉ” አገልግሎትን ለመተግበር ጨረታውን ያሸነፈው ግሎባል ኮምፕዩቲንግ ሶልዩሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ምንም ዓይነት ድርሻ ወይም ባለቤትነት ለሌለው ለክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ከሕግ ውጪ ማስተላለፉ ታወቀ። በቀድሞው የመገናኛ ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጨረታውን ላሸነፈው ግሎባል ኮምፕዩቲንግ ሶልዩሽን የሰጠ መሆኑ ታውቋል። ይሁን እንጂ ጨረታውን ያሸነፈው ድርጅት በሰኔ 26/2003 በተጻፈ ደብዳቤ ባለቤትም ሆነ ድርሻ ለሌለው ‘ክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር’ ማስተላለፉ ተረጋግጧል።

ጨረታውን ያሸነፈው ድርጅት በጊዜው ከነበረው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር የተፈራረመው ሰነድ አንቀፅ 24 ላይ እናት ድርጅት ወይም አጋር ካልሆነ በስተቀር ለሦስተኛ ወገን እንደማይተላለፍ በግልጽ አስቀምጦ ነበር። ነገር ግን የመገናኛ ኢንፎርሚሽን ሚኒስቴር ጨረታውን ካሸነፈው ድርጅት ጋር ያደረገው ሥምምነት በግዥ ሰነዱ መሠረት መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ ግን የተገኘው ከሕጉ የተለየ እና ያለ አግባብ ለሦስተኛ ወገን መተላለፉን የፌደራል ዋና ኦዲተር አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ የተቋቋመው የካቲት/2002 መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፥ ግንቦት 30/2002 በወጣው ጨረታ ሰነድ የሚጠይቀው የ5 ዓመት ሥራ ልምድ እና ቢያንስ በ4 የመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ የሠራ የሚል መሥፈርት ቢኖረውም ይህን ሁሉ መሥፈርት ሳያሟላ ለክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ተላልፎ ተሰጥቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራል ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2010 በጀት ዓመት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የፋይናንስና ሕጋዊነት እንዲሁም የክዋኔ ኦዲት ባቀረበቡበት ወቅት እንደተናገሩት፥ አሸናፊ ተጫራቹ ለአንድ ክፍያ ያቀረበው ዋጋ 1 ብር ከ43 ሳንቲም ሆኖ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር ድርድር ማድረጉን ጠቁመዋል። በዚህም መሠረት ድርድር የሚደረገው ለማስቀነስ ቢሆንም ለአንድ ገንዘብ ዝውውር ከቀረበበት ዋጋ በ1 ብር 13 ሳንቲም እንዲጨምር በማድረግ 2 ብር ከ56 ሳንቲም እንዲሆን በማድረግ ውል እንዲፈፀም መደረጉንም ገመቹ ጨምረው ገልጸዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የለሁሉ አግልግሎት ከተጀመረበት ከየካቲት 2005 እስከ ሕዳር 2011 ድረስ ባሉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ሊከፈል የማይገባ 70 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር አላግባብ መከፈሉን ለማወቅ ተችሏል።

ከግሎባል ኮምፒዩቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርም በገባው ውል መሠረት ከሦስት ዓመት ከስድስት ወር በኋላ በጥር 2007 ላይ ሥራውን ለሚኒስቴሩ ማስረከብ ቢኖርበትም ባልተራዘመ ውል ለአንድ ዓመት ሲሠራ ቆይቶ ጥር 2008 የውል ማሻሻያ ተደርጎ ውሉ ለኹለት ተጨማሪ ዓመታት ተራዝሟል።

ጉዳዩን በሚመለከት አዲስ ማለዳ የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ሙኒር ዱሪን ያነጋገረች ቢሆንም ምንም ዓይነት ኦዲት ግኝት እንደሌለ እና ስለሚባለው ነገር መረጃ እንደሌላቸው ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here