በሐምሌ 2010 በሶማሌ ክልል በጅጅጋ ከተማ በተነሳው ኹከትና ብጥብጥ ምክንያት ቤት ንብረታቸውን እንዲሁም የተለያዩ የንግድ ሥራዎቻቸውን ላጡ ሰዎች በክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል የሚሰጠው ድጋፍ በትውውቅ እየታደለ ነው ሲሉ 400 የሚጠጉ ነዋሪዎች ቅሬታ ማቅረባቸው ተሰማ።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ሠራተኞች ምንም ጉዳት ላልገጠማቸው ቤተሰቦች እርዳታ እንዲሰጥ ከማድረጋቸውም በላይ ከአንድ ቤት እስከ አምስት ሰው ድጋፍ እንዲያገኝ እያደረጉ ነው ሲሉ ወቅሰዋል። እጅግ የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ግን ምንም ዓይነት ዕርዳታ እንዳልደረሳቸው ለአዲስ ማለዳ ገለፀዋል። መኖሪያ ቤታቸው ለወደመባቸው ሰዎች መንግሥት ከአምስት እሰከ ዐሥር ሺሕ ብር ድረስ ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም ምንም ጉዳት ላልደረሰባቸው ሰዎች ድጋፉ በመተላለፍ ላይ በመሆኑ ቁጣ መቀስቀሱ ታውቋል።
የንግድ ቤቶች ለተጎዱባቸው ሰዎች ከ 10 ሺሕ እስከ 600 ሺሕ ብር ድረስ ድጋፍ መደረጉን መስማታቸውን እና ይህ ድጋፍ ግን በአደባባይ ንብረቶቻቸው ሲዘረፉ ለታዩ ፋብሪካዎች እና ሆቴሎችን ጨምሮ በእርግጥም ለተጎዱ ነጋዴዎች ባለመሰጠቱ ሙሰኞች በሕዝብ እንባ ለመበለፀግ እየተጠቀሙበት ነውም ተብሏል።
በሐምሌ 21/2010 በጅጅጋ ከተማ በተደራጁ ወጣቶች አማካኝነት በተለያዩ የእምነት ተቋማት በተለይም በኪዳነ ምህረት እና ሚካኤል ቤተክርቲያኖች ላይ፣ በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች እና በንግድ ማዕከላት ላይ በተፈፀመው ጥቃቶች ብዙ ሺሕ የከተማዋ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የነበረ ሲሆን የብዙዎችም ሕይወት አልፏል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አብዲ መሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) ከሥልጣናቸው ተነስተው ከሌሎች 45 አጋሮቻቸው ጋር በዚህ ድርጊት ተጠርጥረው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን አብዲን ጨምሮ ዘጠኝ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ባለሥጣናት ባሻገር ጉዳት ያደረሱባቸው ግለሰቦች ላይ ምንም ዓይነት ቅጣት ሳይጣል መቅረቱን ተናግረው, ነገም ይህ ድርጊት እንዳይደገም ማስተማሪያ አልሆነም ሲሉ ገልፀዋል።
አሁን ያለውን የኢ-ፍትሓዊ የድጋፍ ሒደት ከሥር ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣኖች የሚያደርጉት በመሆኑ ለበላይ አመራሮች ጉዳዩን በማጋለጥ መፍትሔ እያፈላለጉ እንደሆነ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል። “ይሄንን ሁሉ ሙስጠፌ ያውቃል ብለን አናምንም፣ ከሔደበት አገር እስኪመለስ በትዕግስት እየተጠባበቅነው ነው” ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ። ‹‹ከሥር ያለው የመንግሥት መዋቅር ይህንን ነገር እየደረገ እንዳለ እናምናለን” ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አዲሱን ምክትል ፕሬዘዳንት ሙሰጠፌ ኡመርን ወደ ሥልጣን ካመጣ በኋላ በክልሉ የተከሰቱት ግጭቶች የረገቡ ሲሆን ከተማዋም ወደነባር ሰላሟ ተመልሳለች። በተጨማሪም የተለያዩ የለውጥ ሥራዎችን በማካሔድ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ጥረት ማድረግ የጀመረው አዲሱ አመራር የመሪ ፓርቲው ሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርተ (ሶሕዴፓ) የሶማሊኛ ቋንቋን ለሚናገሩ ሁሉ በሩን ክፍት ማድረጉ እንደ አንድ ማሳያ ተደርጎ በዘርፉ ተንታኞች ሲነሳ ቆይቷል።
አዲስ ማለዳ የክልሉን የተለያዩ የሥራ ኀላፊዎች በስልክ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም።
ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011



