በኢትዮጵያ አዲስ የኮሚኒኬሽንና የብሮድካስት ሳተላይት ሊገነባ ነው

0
628

በኢትዮጵያ አዲስ የኮሚውኒኬሽንና ብሮድካስት ሳተላይት ለመገንባት ከቻይና መንግሥት ጋር ስምምነት ተፈረመ። ስምምነቱ በተለይም የብሮድካስት ዘርፉን ለማዘመን ያገለግላል ሲል የኢኖቬሽን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። ሚኒስቴሩ አያይዞ እንደገለፀውም ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠርና ለተጨማሪ ገቢ ማስገኛ እንዲውልም ሌላው የግንባታው ዓላማ መሆኑን አስረድቷል።

ስምምነቱ የተፈረመው በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት ሰለሞን በላይ (ዶ/ር) እና በቻይናው የሮኬት ኪባንያ ምክትል ዳይሬክተር ሃን ቺንፒንግ መካከል ሲሆን፥ ግንባታው የሚከናወነውም በኢትዮጵያና በቻይና ባለሙያዎች አማካኝነት እንደሆነ ተገልጿል። በግንባታውም ወቅት 50 በመቶ አገር ውስጥ እሴት እንዲካተትበት እንደሚደረግም ታውቋል።

የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ተስፋዬ ዓለምነው ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት፤ የሳተላይት ግንባታው ላይ የሚሳተፉት ኢትዮጵያዊያን ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በቻይና አገር ሔደው ሥልጠና እንደሚወስዱና የወሰዱት ሥልጠና በበቂ ሁኔታ መሆኑ ከተረጋገጠ ብቻ ወደ ሥራ እንደሚሠማሩ አስረድተዋል። አያይዘውም በግንባታው ወቅት ኢትዮጵያዊነትን የሚያንፀባርቁ ግብዓቶች እንደሚካተቱም ተናግረዋል።

በኹለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የሳተላይት ግንባታ ስምምነት ምን ያህል መዋዕለ ንዋይ ወጪ እንደሚደረግበትና ወጪው በማን እንደሚሸፈን በግልፅ አልተቀመጠም የሚሉት ተስፋዬ ግንባታው ግን በሦስት ዓመታት እንዲጠናቀቅ የጊዜ ገደብ ተይዞለታል።

ስምምነቱ በግንቦት 19/2011 አዲስ አበባ ላይ የተፈረመ ሲሆን፤ ለግንባታው የሚሆን ቦታ መረጣ፣ ተጠቃሚነት የመለየት፣ እና ተዛማጅ ጉዳዮችን የማካሔድ ሥራ በቀጣዩ ሰኔ 2011 እንደሚጀመር የአዲስ ማለዳ መረጃ ያመላክታል።

ከሳተላይት ግንባታ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ እና ቻይና ከዚህ ቀደም ስምምነት ላይ ደርሰው ወደ ሥራ የገቡበት የገቡ ሲሆን፤ በኹለቱ አገራት ትብብር የተገነባችው የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጣዩ ዓመት ሕዳር 2012 ወደ ሕዋ እንደምትላክ ታውቋል። ሳተላይቷ ወደ ሕዋ የምትላከው ከቻይና ቢሆንም የመቆጣጠሪያና የዕዝ ጣቢያው በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚሆን ሰለሞን ተናግረዋል።

ሳተላይቷን ለመገንባት ከቻይና መንግሥት በኩል የ6 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በሥልጠናና ግንባታ ዘርፍ የተደረገ ሲሆን፤ ቀሪውን ኹለት ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ወጪ ተደርጎ በአጠቃላይ ግንባታው 8 ሚሊዮን ዶላር መሆኑም ታውቋል፡፡

ይህች ሳተላይት ወደ ህዋ ስትላክ ኢትዮጵያ ስምንተኛዋ የራሷ ሳተላይት ያላት አፍሪካዊት አገር ትሆናለች። ከዚህ ቀደምም ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ናይጀሪያ፣ ጋና፣ አልጀሪያ፣ ሞሮኮ እና ጎረቤት አገር ኬንያ ሳተላይ ወደ ሕዋ የላኩ አገራት ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here