ኤጀንሲው ለማረሚያ ቤቶች በ5 ሚልዮን ብር መጻሕፍት ሊገዛ ነው

0
791

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ በክረምት የንባብ ባሕልን ለማዳበር በተያዘው መርሃ ግብር መሰረት “በመጽሐፍ እንታረም” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ፣ ሸዋሮቢት፣ ድሬ ዳዋ፣ ባሌ ሮቤና ወላይታ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ ታራሚዎች ልገሳ ለማድረግ ግዢ ሊፈፅም ነው።

በማረሚያ ቤቶች በቤተ መጽሐፍት ዙሪያ ሥልጠና በመሥጠት፣ መጻሕፍትን ግዢ በማድረግና በመጽሐፍ አደረጃጀት ላይ የምክር አገልግሎት በመስጠት ክበባትን በማቋቋም እነዚህን መጽሐፍት እንዲያነቧቸውና እንዲጠቀሙባቸው መታሰቡም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሽመልስ ታዩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዋናነት ዓላማው በማረሚያ ቤቶች ትኩረት ለመደረጉ ምክንያቱ ከዚህ ቀደም መጻሕፍትን አንብበው የወጡ ታራሚዎች ያገኙትን ዕውቀት እንደምሳሌ በመጠቀም ታራሚዎች እንዴት ማንበብ እንዳለባቸውና እውቀታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ማሳወቅ ነው ሲሉ ሽመልስ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በመጪው ሰኔ የሚጀመረው ይህ “ክረም-ተ መጽሐፍ” መርሃ ግብር ሕፃናት፣ አዛውንቶችና ወጣቶች የማንበብ ባሕላቸውን እንዲያሳድጉ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን በዋናነት በክልል ከተሞች የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ላይ ለሚገኙ እስረኞች በክልሉ ቋንቋ የተጻፉ መጽሐፎች እና የታሪክ መፅሐፍት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ታውቋል።

ከዘመቻ በዘለለ ቀጣይነት ያለው እንዲሆን የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ የየከተሞቹ መስተዳድሮች፣ በየአካባቢው የሚገኙ ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎችና በዙሪያቸው የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ በማድረግ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ “የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ወመዘክር” በሚል ሥያሜ በ1936 በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን አገልግሎት መስጠት የጀመረውም ንጉሡ ባበረከቱት ከ200 በላይ የመጻሕፍት ስጦታ አማካይነት ነው። በ1958 በተደረገው የቤተ መጻሕፍት መዋቅር ለውጥ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት የሚል ስያሜ ይዞ ጥንታዊ ቅርሶች አስተዳደር ሥራ እንዲሠራ ተደርጎ በ1967 በመጀመሪያ ደረጃ ተዋቅሮ ሥራው እንዲቀጥል ሆኗል።

በ1972 ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት መምሪያ ተብሎ ሥራውን እንዲከናውን የተደረገ ሲሆን በ1986 በተደረገ የመዋቅር ለውጥ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት ድርጅት የሚል ሥያሜ ይዞ እንዲሠራ መደረጉን ታሪክ ያወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here