ከአምባሳደሮቹ አንደበት ስላለፈው እና መጪው ጊዜ ተስፋ እና ሥጋት

በቅርቡ የዩናይትድ ስቴትስ የሰላም ተቋም ባዘጋጀው የውይይት መድረክ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አመራር ውስጥ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ አገሪቱ ዓለም ዐቀፍ ተቀባይነት ማግኘቷን በተመለከተ እንዲሁም የገጠሟትን በርካታ ፈተናዎች በማስመልከት ተሳታፊ የነበሩ አራት የቀድሞ የአሜሪካ አምሳሳደሮች በኢትዮጵያ ለመድረኩ ካካፈሉት ሐሳቦች አስማማው ኀይለጊዮርጊስ ለአዲስ ማለዳ ተደራሲያን ይሆናል ያለውን በሚከተለው መልኩ ከትቦ አቅርቦታል።

ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦችን በመያዝ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በጣም ወሳኝ እና ብዙ የሕዝብ ብዛት ካላቸው አገራት መካከል የምትመደብ መሆኑን ያወሳው የዩናይትድ ስቴትስ የሰላም ተቋም – በኢትዮጵያ በቅርቡ በፖለቲካ አመራር ውስጥ የተደረጉ ለውጦች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሰፊ ተቀባይነትን ስለማስገኘቱ በማተት ነገር ግን ከዚህ አዎንታዊ እርምጃ በተቃራኒው አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በርካታ ፈተናዎች እየተጋፈጠች ስለመሆኑ አስምሮበታል።

የኹለቱ አገራትን ታሪካዊ የኹለትዮሽ ጠንካራ ግንኙነት መሰረት በማድረግ አሜሪካ ለኢትዮጵያ በዚህ የሽግግር ወቅት የምትሰጠው ድጋፍ ለአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ከግምት በማስገባት የሠላም ተቋሙ “የኢትዮጵያን የሽግግር ለውጥ ለማገዝ ከዚህ ቀደሙ ከአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ መማር ወሳኝ ነው” በሚል ዓውድ ሰፊ ውይይት አዘጋጅቶ ነበር። ይህንን ውይይት ለየት የሚያደርገው ከድኅረ የደርግ ወታደራዊ መንግሥት በኋላ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር በመሆን ያገለገሉ አራት የቀድሞ አምባሳደሮች ልምዳቸውን ያካፈሉበት አጋጣሚ መፈጠሩ ነው። በተለይ ርዕሰ ጉዳዩ በዋንኛነት ‹‹ካለፈው መማር›› የሚልን ዓላማ በማንገቡ አራቱም አምባሳደሮች ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በነበራቸው ተልዕኮ የገጠማቸውን አስቸጋሪ ሆነ አስገራሚ ሁኔታ ያወሱበት መሆኑ እንዳለ ሆኖ በተለይ ኢትዮጵያ ሳሉ ወይም መገናኛ ብዙኀን ፍጆታ ያልዋሉ አንዳንድ ጉዳዮችንም ማውሳታቸው አልቀረም።

ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሥዩም መስፍን ለቀድሞ አንድ የአሜሪካ አምባሳደር ከምርጫው ጋር በተያያዘ ኢምባሲው ምንም አሉታዊ መግለጫ እንዳይሰጥ ማስጠንቀቁ ይገኝበታል።

አራቱ አምባሳደሮች
የዚህ ውይይት ዋነኛ ተሳታፊዎች አራት አምባሳደሮች ሲሆኑ እነሱም አምባሳደር ማርክ ባስ – ኢሕአዴግ እንደገባ አካባቢ ማለትም ከ1992-1994 (እ.ኤ.አ) በኢትዮጵያ በአምባሳደርነት ያገለገሉ። በኢትዮጵያ ጉዳይ ሆነ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ዙሪያ ዘውትር የተለያዩ አስተያየቶችን በመስጠት የሚታወቁት የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን ሌላኛው የዚህ ውይይት ተሳታፊ ነበሩ። ከአሜሪካ የቀድሞ ሴት አምባሳደሮች መካከል አንዷ የሆኑት አምባሳደር ኦሬሊያ ብራዚል ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ ሲሆኑ በተለይ እኝህ አምባሳደር በምርጫ 97 ወቅት አዲስ አበባ የነበሩ እንደመሆናቸው ብዙዎች ከዚሁ የድኅረ ምርጫ ውዝግብ ጋር በተያያዘ ያስታውሱዋቸዋል። አራተኛው መድረክ ተሳታፊ በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ ነበሩ። ከሞላ ጎደል ሁሉም አምባሳደሮች ከሹመታቸው በፊት ሆነ በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያን ደጋግመው ለመጎብኘት የቻሉ ስለመሆኑ በዕለቱ የገለጹ ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያ በአምባሳደርነት በማገልገል ላይ ሳሉ የገጠማቸውን ተግዳሮት፣ ከኢትዮጵያ ባሥልጣናት ጋር ስለነበራቸው አስቸጋሪ ግንኙነትም በስፋት አትተዋል።

የሥዩም መስፍን ማስጠንቀቂያ
ሁሉም አምባሳደሮች በኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት ከኢሕአዴግ አመራሮች ጋር ስለነበራቸው ቆይታ ልምዳቸውን አካፍለዋል። አምባሳደሮቹ ልክ እንደሹመት ጊዜያቸው የአገሪቱ ሁኔታ የተለያየ ግንኙነት እንደነበራቸው መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ አምባሳደር ማርክ ባስ ኢሕአዴግ ገና ሥልጣን እንደያዘ አምባሳደር ሆነው በመሾማቸው የያኔውን የሽግግሩን መንግሥት መሪ መለስ ለማግኘት ቡዙም እንዳልተቸገሩ አውስተዋል። ይሁን እንጂ ሌሎቹ አምባሳደሮች እንደሁኔታው አስቸጋሪ ጊዜን ስለማሳለፋቸው አውስተዋል። የዲፕሎማሲው ዓለም የራሱ የሆኑ ደንቦች፣ ፕሮቶኮል እና ሥነ ምግባር ያሉት ከመሆኑ በተጨማሪ እያንዳንዱ እርምጃ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ሁኔታዎችን ከግምት ባስገባ ስሌት ጭምር የታጠረ እንደመሆኑ ስለአንድ ጉዳይ ከአንድ ዲፕሎማት ሃቁን በቀጥታ እሰማለሁ ማለቱ ዘበት ነው። ይሁን እንጂ በተለይ አምባሳደሮች የሹመት ጊዜያቸውን ካገባደዱ በኋላ አሊያም በራሳቸው አገር ውስጥ በሚኖር ውይይት ውስጥ ለወትሮው በሚስጢር የሚይዙትን ጉዳዮች ይፋ ለማድረግ አይቸገሩም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የገጠማቸውን አስገራሚ ነገር አውስተዋል።

“ኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኜ በሔድኩበት ወቅት የኢሕአዴግ አመራር በምን ያህል ጥልቅ የፍርሃት ውስጥ እንደነበሩ አላወኩም ነበር። ለካ ከድኅረ ምርጫ 97 በኋላ የኢሕአዴግ አመራር በፍርሃት ውስጥ የሚኖር ሆኗል። ስለሆነም እኛ ነፃ እና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲደረግ በጠየቅን ቁጥር እንሱ ለፓርቲያቸው አመራሮች የሚገልፁት እነዚህ ‘የውጭ አገር ሰዎች’ በምርጫ ሥም ብጥብጥ አስነስተው ከሥልጣን ሊያስነሱን ነው የሚፈልጉት የሚል ነበር። ለዚህም ነው ምርጫ 2002 ሲደርስ የምርጫ ታዛቢን ካለማሳተፍ ባለፈ ልክ ምርጫው ኹለት ሳምንት ሲቀረው ባወጡት ድንጋጌ ሁሉም የዲፕሎማቲክ ማኅበረስብ ሆነ የረድኤት ድርጅት አመራሮች ከመንግሥት ፍቃድ ካላገኙ በቀር ከአዲስ አበባ እንዳይወጡ ከለከሉ።”

አምባሳደሩ እንዳወሱት ከሆነ በጊዜው የምርጫውን ሒደት ለመታዘብ ሳይሆን እንዲሁ ከአዲስ አበባ ወጣ ለማለት ቀደም ብለው ፕሮግራም የያዙ ዲፕሎማቶች መኖራቸውን ተከትሎ “መለስ በቁጣ ተሞልቶ ደውሎልኝ ማንኛውም ዲፖሎማት ከአዲስ አበባ ውጪ ከተገኘ መንግሥት ለማሰር እንደሚገድድ” እንደገልፁላቸው፣ በተጨማሪ፣ የያኔው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሥዩም መስፍን የምርጫው ዕለት ደውለው “ማንኛውም ዓይነት አሉታዊ መግለጫ (‘ኔጌቲቭ ስቴትመንት’) ስለ ምርጫው ከኢምባሲው ከወጣ በኹለቱ አገራት የኹለትዮሽ ግንኑነት ላይ በጣም አደገኛ የሆነ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል እንዳስጠነቀቋቸው አውስተዋል።”

ይሁን እንጂ ይላሉ አምባሳደሩ ከማስጠንቀቂያው በተቃራኒው በእርግጥ ምርጫው ነፃ እና ፍትሐዊ ስላለመሆኑ መግለጫ ማውጣታቸውን ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ ይህንኑ ተከትሎ የያኔው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሥዩም ሆነ የያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የወሰዱት እርምጃ ስለመኖሩ ያብራሩት ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ በጊዜው እሳቸው እንዳስተዋሉት ከሆነ መለስ ሁልጊዜም ቢሆን በጣም ተጠርጣሪ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከምርጫ 97 ጊዜ አንጻር የተሻለ መሰናዶ ይኖር ይሆን?
ቀጣዩ ምርጫ ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ ብቻ የቀረው መሆኑን በማስታወስ ከፕሮግራሙ አስተባባሪ “በአሁኑ ወቅት ከምርጫ 97 ጊዜ አንጻር የተሻለ መሰናዶ ይኖር ይሆን?” የሚል ጥያቄ ለአምባሳደር ኦሬሊያ ብራዚል ተነስቶ ነበር። አምባሳደሯ ለጥያቄው ቀጥታ ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት ወደ ኋላ መለስ በማለት በምርጫ 97 የተከሰተውን አስታውሰዋል። በወቅቱ መንግሥት በምርጫው የተከሰተው በጭራሽ ያልጠበቀው እንደነበር ተናግረው በጊዜው እሳቸው ይመሩት የነበረው የለጋሾች ቡድን የበለጠ ችግሩ እንዳይሰፋፋ እና መንግሥታዊ ስርዓቱ የለየለት ቀውስ ውስጥ እንዳይገባ የድርሻቸውን መወጣት ስለመቻላቸው በተለይ በጊዜው ዋነኛ ትኩረታቸው የሰው ሞት አንዳይከሰት በመሆኑ በዚህ ረገድ የለጋሾቹ አምባሳደሮች ቡድን ቢሳካለትም በቀጣይነት የነበረውን የጅምላ እስር፣ ስደት እና ወከባ ለማስቆም ግን እንዳልቻለ በማስታወስ በአጠቃላይ ከምርጫው በኋላ ከተከሰተው ቀውስ ውጪ ቅደመ ምርጫ የነበረው ሒደት ለነፃ ምርጫ በጣም አመቺ እንደነበር በማስታወስ ይህ ዓይነቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ በመጪው ምርጫ እንዲፈጠር ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ከነበረው ኢሕአዴግ በአንጻራዊነት የተለየ ሁኔታ ላይ ባለው እና ለመለወጥ ፍላጎት ባሳየው የኢሕአዴግ የለውጥ አመራር በቀጣይነት የሚካሔደው ምርጫ ምን ዓይነት ትርጉም ይኖረው ይሆን የሚል ጥያቄ ከፕሮግራሙ አስተባባሪ የተሰነዘረላቸው አምባሳደር ቡዝ “ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 ከደረሰበት ሽንፈት የተማረው ነገር ቢኖር ከዚህ በኋላ ‘don’t be surprised’ (በምርጫ ውጤት እንዳትደነቅ) በሚል ዓይነት አካሔድ ፓርቲውን ማግዘፉ (ማሳደጉ) ላይ ነው ያተኮረው” ካሉ በኋላ በአንድ ወቅት ከመለስ ጋር በነበራቸው ስብሰባ የተናገረውን ቅሬታ አስታውሰዋል። መለስ “እኔ የወረስኩት ኢምፔሪያል ቢሮክራሲ (Imperial bureaucracy ) በመሆኑ ምንም ለለውጥ ዝግጁ አይደለም” በማለት እርሱ ለለውጥ ዝግጁ ቢሆንም ቢሮክራሲው ግን ምላሽ የማይሰጥ ስለሆነ የፈለገውን ለውጥ እንዳላመጣ አድርጎኛል” ስለማለቱ በቅድሚያ አውስተው – “ይህም የመነጨው ከመሰረታዊው ችግር አገሪቱን ለመምራት ፓርቲው ላይ ብቻ የመተማመን ነው። በማለት የችግሩን ሥር ካሰመሩበት በኋላ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እስካሁን ባላቸው አቋም ከፓርቲው ይልቅ አገሪቱን በሚገባ ለመምራት መንግሥታዊ መዋቅሩ ላይ ማተኮራቸው ነው። ይህ ተገቢ እርምጃ ቢሆንም ምን ያህል ጠንካራ የሆነ መንግሥታዊ ተቋም ይኖር ይሆን? የሚለው ጥያቄ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል አውስተዋል። የሆነው ሆኖ ቀጣዩ ምርጫ በተለይ በርካታ የተማሩ የመጀመሪያ ጊዜ መራጮች ስለሚሳተፉበት፣ የማኅበራዊ ሚዲያም ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ መልኩ ለቅስቀሳ በጥቅም ላይ ሊውል መቻሉን በማስታወስ ሁሉም አምባሳደሮች እነርሱ ከነበሩበት ጊዜ ይልቅ የአሁኗ ኢትዮጵያ በእጅጉ የተለየች መሆኗን በማውሳት በዛው መጠን የምርጫው ሒደትም ከመቼውም ጊዜ የተለየ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ሰንዝረዋል።

የብሔር ፌዴራሊዝም እና የዜሮ ድምር ፖለቲካ
አምባሳደር ዴቪድ ሺን በአገሪቱ እየተካሔደ ካለው አስገራሚ ለውጥ በተቃራኒው በተለያዩ አካባቢዎች የብሔር ግጭት መበራከቱን ተከትሎ ለተነሳው ጥያቄ በየክልሉ በብሔሮች መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም ከወዲሁ ተገቢው እርምጃ ካልተወሰደ በቀር በቀጣይነት ሊከሰት የሚችለው አደጋ ሰፊ ሊሆን እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልፀዋል።

በብሔር ግጭት መበራከት ዙሪያ የተሰጠውን ሐሳብ ተከትሎም ከአወያዩ “አሁን ለውጥ ላይ ኢትዮጵያ እያለች በዚህ ደረጃ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱትን የብሔር ግጭት ከግምት በማስገባት በእርግጥ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የብሔር ፌዴራሊዝም ዘላቂ በሆነ መልኩ ውጤታማ ሊሆን ይቻለዋልን?” የሚል ጥያቄ ተነስቶ አምባሳደር ቡዝ ሲመልሱ “በእርግጥ ይህ ኢትዮጵያውያን ሊመልሱት የሚገባ መሰረታዊ ጥያቄ ነው” በማለት ጥያቄው ወሳኝ መሆኑን ካሰመሩበት በኋላ ይህንን ጥያቄ ከወዲሁ በሚገባ ካልፈቱት በቀር የሰው ደኅንነት ለአደጋ እየተጋለጠ፣ ኢኮኖሚውን በሚገባው መንገድ እንዳያድግ ከመቀዛቀዝ ባለፈ ስኬታማ ምርጫ ማድረጉም ያስቸግራል ሲል የችግሩን መዘዝ ሰፊ ስለመሆኑ አውሰተዋል።

ይህንኑ የብሔር ፌዴራሊዝም በተመለከተ በቀጥታ መለስን በግንባር ጠይቄው ነበር ያሉት አምባሳደር ዴቪድ ሺን ሁኔታውን እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል። ‹‹ ከአምባሳደርነቴ በኋላ መለስን ባገኘሁት ወቅት የብሔር ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ ትክክለኛው ፖሊሲ ነው ብለህ አምነህበታል ብዬ ስጠይቀው የሰጠኝ ምላሽ የተለመደውን የእሱ መለያ ዓይነት ነበር። ይኸውልህ አምባሳደር ከዚህ ቀደም አንባገነን አገዛዝን ሞከርን አልተሳካም፣ ኢምፔሪያሊስት አገዛዝን ሞከርን፤ አልተሳካም፣ ወታደራዊ ሶሻሊስትን በደርግ ሞከርን አልተሳካም ስለዚህ አሁን ደግሞ ይህንን እንሞክረው …” እንዳላቸው ይፋ አድርገዋል።

አስማማው ኃይለጊዮርጊስ ጋዜጠኛ እና የኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ ፌሎ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው
[email protected] ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here