የመኪና መለዋወጫ ዋጋ መናር የትራስፖርት እጥረት ፈጥሯል

0
838

ላለፉት ዐሥራ አምስት ዓመታት በሚኒባስ ታክሲ ሹፌርነት የሚተዳደሩት አየነው ንጋቱ ሰባት ልጆቻውን ጨምሮ ቤተሰቡን ለሚያስተዳድሩባት የመኪና መለዋወጨ ፍለጋ ከቄራ፣ ቡልጋሪያ ከዛም ጨርቆስ በመዟዟር ይባዝናሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየናረ የመጣው የመለዋወጫ ዋጋ ለሥራቸቸው ተግዳሮት እንደሆነባቸው የሚናገሩት አየነው ከአንድ ወር በፊት 80 ብር ይሸጥ የነበረው ጉንቲና 120 ብር ሆኖ እንደጠበቃቸው ተናግረዋል።

በተደጋጋሚ የሚቀየረው የፍሬን ሸራ ከኹለት ወራት በፊት ከነበረበት አማካኝ ዋጋ 600 ብር በእጥፍ አድጎ 1200 ብር እጥፍ ሲሸጥ አንድ ሚኒባስ ታክሲ ከአንድ ወር ተኩል እስከ ኹለት ወር ድረስ ሊገለገልበት ይችላል።

አየነው እንደሚሉት የቀን ገቢ እና ለመለዋወጫ የሚወጣው ወጪ ከሚያገኙት ገቢ አንጻር ተመጣጣኝ ያለመሆኑን ተቋቁመው ያለፉትን ኹለት ዓመታት የዘለቁ ሲሆን አሁን ግን ለመቋቋም የሚያስቸግር ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ይናገራሉ። የመለዋወጫ ችግር ለቀናት ሥራ ፈትተው ከመቆማቸው ባሻገር በውድ ዋጋ የሚገዙት ዕቃም በአጭር ጊዜ የሚበላሽ ተመሳሳይ ዕቃ ሆኖ መቸገራቸውን ይናገራሉ።

ከፍተኛ ጭማሪ ካሳዩት ግብዓቶች መካከልም የሞተር ዘይት ዋነኛው ሲሆን በአማካኝ ለ10 ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚያገለግለው 5 ሊትር ዘይት ከነበረበት 800 ብር ወደ 1200 ብር የናረ ሲሆን ለ5 ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚያገለግለው ዘይት ደግሞ ከነበረበት 4 መቶ ብር እጥፍ ጭማሪ በማሳየት ወደ 8 መቶ ብር አድርጓል።

የታሸገ ወይም የማይሞላ የመኪና ባትሪ ከነበረበት 3 ሺሕ 200 ብር ወደ 4 ሺሕ ብር ያደገ ሲሆን የሚሞላ ባትሪ ደግሞ ከ2 ሺሕ ብር ወደ 3 ሺሕ ብር ከፍ ማለቱን አዲስ ማለዳ ያደረገችው ቅኝት ያሳያል። አማካኝ ለታክሲ ሥራ በየስድስት ወሩ የሚቀየረው ካንዴላ ደግሞ ከእጥፍ በላይ በማደግ ከነበረበት 150 ብር ወደ 400 ብር ንሯል።

ይህ የዋጋ ንረት በቅርቡ እየታየ ካለው የመኪና ዋጋ ማሻቀብ ጋር ተደምሮ በከተማው ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ቁጥር መመናመን እና ከተለመደው በላይ የሰልፍ መብዛት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ውስጥ ያደረገችው ዳሰሳ ያስረዳል። የመኪና ዋጋ ከመጨመሩም ባሻገር የመኪና መሸጫዎች በውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የሚያስገቧቸው መኪኖች እጅጉን በመቀነሳቸው ወደ አገልግሎት የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ቁጥር መቀነሱንም አሽከርካሪዎች ይናገራሉ።

አየነው በበኩላቸው “ሥራ ለማቆም ባስብም ከጀርባዬ ቤተሰብ ስላለኝ እሠራለው” በማለት ምሬታቸውን ያሰማሉ። በተለምዶ ቡልጋሪያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የጋራዥ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው መላኩ የደንበኞቹን ባለ ኹለትና ባለ አራት እግር ተሽከርካሪዎች በመለዋወጫ ዕጥረት ምክንያት እስከ አንድ ወር በጋራዥ እንደሚቆሙ ይናገራል።

በእጥረቱ ምክንያትም፣ ከሌላ መኪና ላይ ተመሳሳይ ዕቃዎች እየተፈቱ ወይም አዲስ እየተገዙ ለሌላው እንዲገጠሙ ይደረጋል የሚሉት ባለሞያው ይህ ድርጊት ለአደጋ እንደሚያጋልጥ እያወቁ የሚወስዱት ኀላፊነት መሆኑንንም ይናገራሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በተምዶ ሱማሌ ተራ በመባል በሚታቀው እና ያገለገሉ መለዋወጫዎች በሚሸጡበት ገበያ ገዝቶ በመጠቀም ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እፎይታ ማግኘት የሚፈልጉ ሹፌሮች መኖራቸውን እና ይህም የመኪኖቹን ዕድሜ እንደሚያጥር ይናገራሉ።

በውጪ ምንዛሬ ምክንያት ለዐሥር ዓመታት በገበያው ሲቆዩ ካዩት እጥረት ሁሉ የከፋ የሆነባቸው መኩሪያ ላለፈው ኹለት ዓመት ሲታይ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የባሰው ያለፈው ኹለት ወር ውስጥ የታየው ነው ይላሉ። በመሸጫ ሱቃቸው የሚገኙት የኒሳን ዩዲ፣ የታታ ባሶች፣ የደረቅ ጭነት ተሸከርካሪዎች በሌሎች መለዋወጫዎች ላይ ከታየው የዋጋ ንረት የተሻለ መሆኑን ገልፀው የጥቁር ገበያው መጠናከር ግን ሌላው ችግር መሆኑን ይናገራሉ። በየብስ እና በአየር የሚገቡ የኮንትሮባንድ መለዋወጫዎች በረከሰ ዋጋ ገበያውን ይሰብሩታል ይላሉ።

የመለዋወጫ ዕቃዎቻቸውን ከዱባይ የሚያስመጡት መኩሪያ፣ ዕቃ ከውጭ ለማስመጣት የውጭ ምንዛሬ ቶሎ ማግኘት አለመቻላቸውንና ቢገኝም የሚፈለገውን ያህል የገንዘብ መጠን ባለመገኘቱ በገበያው ላይ ዕጥረት ሊከሰት እንደቻለ ያወሳሉ።
ለእነዚህም ችግሮች መንግሥት መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል ያሉት መኩሪያ፣ የውጭ ምንዛሬ መፈቀድ እና ጥቁር ገበያ ላይ የተሰማሩትን ነጋዴዎች መቆጣጠር አለበት ሲሉ ይናገራሉ።

የግል ተቋም በሆነው ትራንዚትና ሎጀስቲክስ ዕቃ አስተላላፊ ድርጅት ውስጥ በክፍያ ተመን አውጪ (‘አሰሰር’) የምትሠራው ሐረግ ተፈሪ (ስሟ የተቀየረ) አጠቃላይ የገቢ ዕቃ መጠን ከመቀነሱ ባሻገር ከዚህ ቀደም ደንበኞቻቸው የነበሩት የመኪና መለዋወጫ ዕቃ አስመጪዎች ሙሉ ለሙሉ መጥፋታቸውን ታስረዳለች።

በአጠቃላይ የገቢ ዕቃዎች ላይ ባለው የኦዲት ግድፈት አስመጪዎች ዕቃውን ባስመጡበት ወቅት ካሳወቁት ዕቃ ዓይነት የተለየ ዕቃ አሳውቀው መገኘታቸው በኦዲት ሲረጋገጥ በሚወሰደው የእግድ እርምጃ የገቡ ዕቃዎች ሳይከፋፈሉ ይቆያሉ ትለለች። ለዚህም የኦዲት አሰራሩ ከሥር ከሥር ወይም ቀድሞውንም አስመጪው በሚያሳውቀው መሰረት ሳይሆን ባለሥልጣኑ በሚያወጣው መሰረት መደረግ አለበት ይላሉ።

መንግሥት በቅርቡ ባሻሻለው መመሪያዎች እና በማሻሻል ላይ ባለው ሌሎች ሕጎች መሰረት ያገለገሉ መኪኖችን ወደ አገር የማስገባት መጠን ለመቀነስ ሥራ መጀመሩም ይታወቃል።

በተሽከርካሪ እጥረት ምክንያት በአዲስ አበባ ውስጥ እየታየ ስላለው የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን የመለዋወጫ ዕጥረቱ እና ውድነት ዋነኛ ተዋናይ እንደሆነ የብሌን ታክሲ ባለንብረቶች ማኅበር ሰብሳቢ ኑረዲን ዲታሞ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
“የታክሲ ዘርፍ ማንንም ባለሀብት የሚጋብዝ አይደለም በዘርፉ እየታዩ ያሉ ችግሮች በርካታ በመሆናቸውና ከችግሮቹ አንዱና ዋነኛ የመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረትና ዋጋቸውም በመቶ በእጥፍ መጨመር እያሳየ ነው” ሲሉ ተግዳሮት እንደሆነባቸውና እንደሚያሰጋቸው ይናገራሉ።

ለእጥረቱ መነሻ አገሪቷ ካላት ውጭ ምንዛሬ እጥረት ሲሆን በዋናነት ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሬውን ስለማያገኙ ከጥቁር ገበያ በመግዛት መለዋወጫዎቹን ያመጣሉ በኋላም ዕቃዎቹ ላይ አላግባብ ጭማሪ እና ንረት እንዲከሰትና ገበያው ላይ ተፅዕኖ እንዲፈጥር ምክንያት ነው ይላሉ።

“ጥቂት ሳንቲም ተሰብስቦ በውድ ዋጋ የመለዋወጫ ዕቃ ተገዝቶ መሥራት ይቻላል ወይ?” ሲሉ ጥያቄን በጥያቄ ይመልሳሉ። ለማሳያነት ከጥቂት ከዓመታት በፊት ከ10 ሺሕ ብር ያልበለጠ ዋጋ የነበረው የሞተር ማደሻ ዋጋ አሁን ላይ ከ40 ሺሕ በላይ እንደሆነ ተናግረው ማንኛውም ተሸከርካሪ ይህን ያህል ገንዘብ ሰርቶና ቆጥቦ ለማሳደስ አዳጋች ነው ይላሉ።
መንግሥትም የነፃ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ለትራንስፖርት ዘርፍ ላይ አለመሥራቱም ነው በማለት የታሪፍ ተመኑ ላይ ያላቸውን ቅሬታም ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here