እመጫት ተማሪዎች

0
544

ከሰኞ፣ ሰኔ 3 ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ እየተሰጠ የሚገኘው የ10ኛ፣ 12ኛ እና 8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከዚህ ቀደም ከተሰጡት ፈተናዎች ልዩ ትኩረት አግኝቷል። የዘንድሮውን ብሔራዊ ፈተና ከከዚህ ቀደሞቹ የተለየ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል በተከታታይ ቀናት በኹለት ሳምንታት ውስጥ እንዲሰጥ መደረጉ አንዱ ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኝ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው።

በመጀመሪያው ሳምንት ማለትም ከሰኔ 3 እስከ 5 ድረስ 10ኛ ክፍሎች የተፈተኑ ሲሆን ከሰኔ 6 ጀምሮ ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች እየወሰዱ እንደሆነ ይታወቃል። በተከታዩም ሳምንት 12ኛ ክፍል ተፈታኞች የቀራቸውን የትምህርት ዓይነትና የ8ኛ ክፍል ተፈታኞች ደግሞ ሁሉንም የትምህርት ዓይነት ለመፈተን የተያዘው መርሃ ግብሩ ያሳያል።

ከሰኔ 3 እስከ 5 ድረስ የተካሔደው ፈተና በመጀመሪያዎቹ ኹለት ቀናት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ስምንት የመደበኛ ተማሪና አንድ የግል ተፈታኝ በሰላም መውለዳቸውን እና እነዚህ እናቶች በመውለዳቸው ምክንያት ፈተናው እንዳያመልጣቸው ባለመፍቀዳቸው ፈተናውን እንዲወስዱ መደረጉን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። ይህንንም መረጃ ተከትሎ የአንዳንዶቹ ተማሪ እናቶች ሕክምናቸውን በሚከታተሉበት የጤና ተቋም አልጋ ላይ ሆነው ፈተናቸውን ሲወስዱ የሚያሳዩ ፎቶዎች መለቀቅን ተከትሎ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የመወያያ አጀንዳ መሆን ችለዋል።

ይህ ዜና ከተሰማ እንዲሁም ፎቶዎቹ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች መሰራጨታቸውን ተከትሎ የመጀመሪያዎቹ አስተያየት ሰጪዎች የእንኳን ደስ ያላችሁና መልካም ዕድል ምኞቻቸው የገለፁበትን፣ የሴቶቹን ጥንካሬና የእናትነት ፀጋን ያደነቁበት እንዲሁም ትምህርት ሚኒስቴርን ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች ፈተና እንዲወስዱ ማድረጉና የተማሪዎቹን ፍላጎት ማሟላቱ ሙገሳን አትረፎለታል።

ይሁንና ዘግየት ብለው በተሰጡት አስተያየቶች ጠንካራ ሒሶች ጎልተው ወጥተዋል። በመጀመሪያ ደረጃ እንዴት ልጆቹ ያለዕድሜያቸው ሊያረግዙና ሊወልዱ ቻሉ የሚለው ወቀሳ እንዲሁም በሕግ የተከለከለው ያለዕድሜ ጋብቻ ምን ያክል የተስፋፋ መሆኑን ያሳያል ሲሉም ያክላሉ። ለብዙ ሴቶች ትምህርት መቋረጥ ምክንያቱም ያለዕድሜ ጋብቻ መሆኑን እነዚህ ተማሪዎች ማሳያዎች ናቸው ያሉም ይገኙበታል። የትምህርት ሥርዓቱም ቢሆን በሥነ ወሊድ ላይ ያለው ትኩረት አነስተኛ መሆን ብሎም ጨርሶውኑም በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ያለመካተቱን ያሳብቃል ሲሉ ወቅሰዋል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ ያለዕድሜ ጋብቻን ማስቀረት ቢያቅት እንኳን በትምህርት ገበታ ላይ ያሉ ብሎም እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ መማር የቻሉ እነዚህ ልጆች የወሊድ መቆጣጢያ ግንዛቢያቸው ምንም ወይም በጣም ዝቅተኛ ነው ሲሉ እናቶቹን በሕያው ምስክርነት ጠቅሰዋል።

ለዚህም የትምህርት ሚኒስትርም ሆነ የጤና ሚኒስትር ከወቀሳው አላመለጡም። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ያለዕድሜ ጋብቻና ሥነ ወሊድ ላይ ብዙ መሥራት ያለባት የቤት ሥራ ለመኖሩ እመጫት ተማሪዎቹ በማሳያነት ቀርበዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here