“የእስላማዊ ባንክ ፖለቲካ!?” በሚል ርዕስ የአዲስ ማለዳ አምደኛ ይነገር ጌታቸው በግንቦት 24/2011 ዕትም ያስነበቡትን ጽሁፍ በመቃወም ኢብራሒም አብዱ ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያ ክፍል ምላሻቸውን ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህ ጽሁፍ ላይ ኢብራሒም አካታች ፋይናንስ ፍለጋ እንደፖለቲካ፣ ሥጋት ነጋዴዎች እና የሙስሊም ፖለቲካ እና ኢስላማዊ ፖለቲካ በሚሉ ንዑስ አርዕስት ምላሻቸውን አሰናድተዋል።
(የመጨረሻ ክፍል)
አካታች ፋይናንስ ፍለጋ እንደፖለቲካ
የአንድን ሙግት ቅቡልነት ከሚወሰኑ ቀመሮች አንዱ በመነሻ ሐሳብና መደምደሚያ መካከል ያለው ትስስር ነው። የይነገር ፅሁፍ ሐሳዊ መነሻ (False premises) ላይ የተመሰረተ ከመሆኑ ባሻገር ያለ ምንም አመክኗዊ ትስስር ወደ ሌላ መደምደሚያ ይዘላል። የተባበሩት አረብ ኢሚሬትን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በሐሳዊ መነሻ ሃይማኖታዊ ካባ ካለበሰው በኋላ አንዳች ሳይንደረደር ይህን መነሻ ታሪካዊ ከሆነ የሙስሊሞች አካታች የፋይናንስ ተቋም ጥያቄ ጋር ዘሎ ለማሰተሳሰር ሞክሯል። መነሻውም መደምደሚያውም ስሁት መሆኑንና ፀሀፊው በአጀንዳው ዙሪያ እውቀት እንደሌላቸው ለመገንዘብ ጥቂት የመረጃ ዳሰሳ ማድረግ በቂ ነው።
አካታች የፋይናንስ ስርዓት (Financial Inclusion) የተባበሩት መንግሥታት የልማት ተልዕኮ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠቀስ መርህ ነው። በተባባሩት መንግሥታት ፊታውራሪነት የሚቀነቀነውና በ2030 ለማሳካት ዕቅድ የተያዘለት እና አገራችንም የተቀበለችው የዘላቂ ልማት ግቦች አካታች የፋይናንስ ስርዓትን መገንባት የዕቅዶቹ አጋዥ ምሶሶ አድርጓል። የዓለም ባንክ አካታች የፋይናን ስርዓትን በፆታ፣ በብሔር፣ በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚያዊ ደረጃ እና በሌሎች ተግዳሮቶች ምክንያት ከፋይናንስ ስርዓቱ ተጠቃሚ ያልሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ሲል ይገልፀዋል። በኢትዮጵያ በሃይማኖታዊ ምክንያት ከፋይናን ስርዓቱ ተጠቃሚ ያልሆኑ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆናቸውን የዓለም ባንክን ጨምሮ በርካታ የዳሰሳ ጥናቶችን ዋቢ ማድረግ ይቻላል።
ሜርሲ ኮርፕስ በተሰኘው ዓለም ዐቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት ድጋፍ ዘይነብ ሰፍያኒ ባዘጋጀችው Policy Analysis on Ethiopia Interest Free Banking (IFB) Directive በተሰኘ መጣጥፍ ላይ ቁጥራቸው ከአገሪቱ ሕዝብ ከ35 እሰከ 40 በመቶ የሚሆኑ ሙስሊሞችን ሊያገለግል የሚችል አካታች የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት እንደሌለ ትጠቅሳለች። ጋሻው ደሳለኝና ገቤ የማታው ባጠናቀሩት Financial Inclusion in Ethiopia የተሰኘ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዳሰሰን የተመረኮዘ የመስክ ጥናታቸው ላይ እንዳሰፈሩት በሃይማኖት ምክንያት ከፋይናንስ ተጠቃሚነት የተገለሉ ዜጎች ብዙ መሆናቸውን አንስተው መንግሥት ይህን ተግዳሮት መቅረፍ እንደሚገባው ምክረ ሐሳብ አቀርበዋል። ብዙዎቹ የመስክ ዳሰሳዎች እንደሚያሳዩት ከሙስሊሙ ባሻገር በተለይም በገጠሪቱ የአገሩቷ ክፍል ነዋሪ የሆነው ክርስቲያኑ የማኅበረሰብ ክፍልም ወለድ/አራጣን በመጠየፍ ከፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ሳይሆን ቀርቷል። የማይክሮ ፋይናንስና የአነሰተኛ ብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ትኩረት አድርገው ሲሠሩበት የነበረውና የአገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርናን ለማሻሻል የማዳበሪያና ምርጥ ዘር በብድር አገልግሎት ለአርሶ አደሮች የማቅረብ አገልግሎት አካታች ባለመሆኑ በርካታቹ ተጠቃሚ መሆን አለመቻላቸው በተለያዩ ሪፖርቶች ተጠቅሰዋል። በእነዚህና በሌሎች አግላይ ምክንያቶች የአገሪቱ የፋይናንስ አገልግሎት ሽፋን እጅግ ዝቀተኛ ነው። የዓለም ባንክ የ2017 ዓመታዊ መረጃ እንደሚጠቁመው ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት አማካኝ የወጣቶች የባንክ ሒሳብ ባለቤትነት 43 በመቶ ሲሆን የአገራችን የባንክ ሒሳብ ባለቤትነት ሽፋን 35 በመቶ ብቻ ነው። ኬንያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ በርካታ አገሮች አካታች የፋይናንስ ስርዓት በመዘርጋት ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግና የዜጎቻቸውን የፋይናንስ ተጠቃሚነት ከፍ ማድረግ ችለዋል።
አካታች የፋይናንስ ስርዓት የአንድን አገር ኢኮኖሚ ለማሳደግና የዜጎች ሕይወት ለመለወጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል። ይህን ታሳቢ በማድረግም በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት መካከል ሦስቱ ወለድ አልባ አገልግሎት መሰጠት ጀምረዋል። በአሜሪካው የዕርዳታ ድርጅት የ45 ሚሊዮን ዶላር የፈንድ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው Pastoralist Areas Resilience Improvement through Market Expansion (PRIME) የተሰኘ አገር ዐቀፍ ፕሮጀከት ቀዳሚ ትኩረት ያደረገው ኢስላማዊ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ማጠናከር ነው። በርግጥ በዲሞክራሲና በኢኮኖሚ ያደጉ አገሮች የዜጎቻቸውን ፍላጎትና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳን በማሰላት በስፋት ኢስላማዊ ፋይንስ ተብሎ የሚታወቀውን የአሳታፊ ወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት በራቸውን ከፍተው፣ ምቹ የሕግ ማዕቀፍ አበጅተው እያሰተናገዱ ይገኛሉ።
የምስረታ ሒደቱን ካጠናቀቀ በኋላ በብሔራዊ ባንክ መመሪያ የታገደው ዘምዘም ባንክ ለግንዛቤ ማስጨባጫ ባሰናዳው ፅሁፍ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ባልደረባና የማይክሮ ኢኮኖሚክስና ፋይናንስ ሊቅ የሆኑት ገብረ ሕይወት አገባ (ዶ/ር) “የአሳታፊ ባንክ ፍላጎት የሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን የሌሎች እምነት ተከታዮችም ጭምር ነው። አማራጭ የባንክ አገልግሎት የማግኘት ፍላጎቱ የሚመነጨው ወለድን ከመጥላት ብቻ ሳይሆን በሥራ ላይ ያሉት ባንኮች ብድር ለመስጠት እንደ መኖሪያ ቤት፣ መኪና፣ የንግድ ድርጅትና የመሳሰሉ መያዣዎችን ማቅረብ ንግድ ስለሚሉ ጭምር ነው። በዚህም የተነሳ ሕንጻ ወይም ሌላ ቋሚ ንብረት የሌላቸው ወጣቶች ከባንክ ብድር ማግኘትና ወደ ሥራ መግባት የሚችሉበት ዕድል ባለመኖሩ አሳታፊ ባንኮች በመያዣ ብቻ ሳይሆን የብድር ጥያቄ በቀረበበት ፕሮጀክት ወይም የንግድ ሐሳብ አዋጭነት ላይ ተመስርተው የሚሰጡት አገልግሎት ብዙ ደንበኞችን የሚስብና እነሱንም ተመራጭ የሚያደርጋቸው ነው” ማለታቸውን አስፍሯል።
በአገራችን የአካታች የፋይናንስ ስርዓት አንዱ ምሶሶ የሆነው ወለድ አልባ/አሳታፊ ባንክ አገልግሎት የማግኘት የዜግነትና ሰብኣዊ መብታቸውን ለማስከበር ሙስሊሞች ትግል ማድረግ ከጀመሩ ሰንባብተዋል። የኢትዮጵያ ባንኪንግ ቢዝነስ አዋጅም በ2008 (እ.አ.አ.) በአዋጅ ቁጥር 592/2008 ለአካታች ፋይናንስ (ኢስላማዊ ፋይናንስና ባንክ) ምቹ ምኅዳር የመፍጠር መሰረት አስቀምጧል። ብሔራዊ ባንክም በ2011 (እ.አ.አ.) ይህንን መሰረት ሕይወት የሚዘራ አሳታፊ ባንክ መመስረት የሚያስችል መደላደል በአዋጅ ቁጥር SSB/51/2011 አፅድቋ። ይህን ተከትሎም ሙስሊም ነጋዴዎችና ባለድርሻ አካላት ሕጋዊ ተቋም በማቋቋም የዘምዘም ባንክ አክሲዮንን ሸጠው ለመመሰረት አሰፈላጊ የሆነውን ካፒታል በአጭር ጊዜ ማሰባሰብ ቻሉ። የዘምዘም ባንክ አክሲዮን ገዢዎችን ዝርዝር እንደሚያሳየው 60 በመቶ የሚሆኑት የአክሲዮን ባለቤቶች ሴቶችና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች መሆናቸው በተለይም ለዝቅተኛ ኢኮኖሚ ላይ ለሚገኘው የማኅበረሰብ ክፍል የአሳታፊ ባንክ አስፈልጉትን ጉልህነት አመለካች ነበር። ይህ ሒደት ግን የተለያዩ አካላት ባደረጉት ጉትጎታ በፖለቲካዊ ውሳኔ ያለአንዳች የሕግ አግባብ እንዲቆም ተደርጎ በዜጎች ሰብኣዊና ዲሞክራሲያ መብት ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ተደፍቶበታል።
ይነገር በፅሁፋቸው ለባንክ ምስረታ የሚሆነው ገንዘብ ከተባባሩት ኢሚሬት ሊመጣ ይችላል የሚለውን ሥጋት ማምረቻ ቀመራቸው ይህን ታሪክ ልብ ያላለ አልያም አውቆ የዘለለ ነበር። በመሰረቱ አገራችን የውጭ ዜጎችን የባንክ አክሲዮን ባለቤትነት አትፈቅድም። ከዚህም ባሻገር በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት በባንክና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ አንድ ባለአክሲዮን ሊኖረው የሚገባው የአክሲዮን ድርሻ ከጠቅላላው ካፒታል አምስት በመቶ በላይ መብለጥ አይችልም። ባንክ ለመመሰረት የሚያሰፈልገው የ500 ሚሊዮን ብር የመነሻ ካፒታልም አካታች የፋይናንስ ተቋም ለሚፈለገው የማኅበረሰብ ክፍል እንደማይከብደው ቀደም ብሎ አሰባሰቦ ማሳየት ችሏል። ፀሀፊው እነዚህን እውነታዎች ወደ ጎን አድርገው ነው የአካታች ፋይናንስ ተቋማት የምሰረታ ሒደቶችን ከውጭ ኀይሎች ጋር ለማስተሳሰርና ሥጋት ለማምረት የሞከሩት። በርግጥ ይህ ሒደት በሌሎች አካላት እንደሚቀጥልና መንግሥት ሐሳቡን እንዲቀይር እጅ የመጠምዘዝ ሥራ እንደሚሠራ የሚጠበቅ ነው።
አንድ ባንክ በዋናነት በብሔራዊ ባንክ የቁጥጥርና የክትትል ጥላ ሥር ነው። የአክስዮን ሽያጭ ፍላጎት ላለው አካል ሁሉ ክፍት ሆኖ በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በአደባባይ ሽያጭ የሚከናወን ነው። አላማውም እንደማንኛውም የንግድ ተቋም ደንበኞችን በማርካት የባለአክሲዮኖችን ትርፍ ማሳደግ ነው። ይህ ትርፍም በዲቪደንድ መልክ ለባለአክሲዬኖች የሚከፋፈል አልያም ለባንኮች በሚፈቀድ ሌላ ትርፋማ ኢንቨስትመንት ላይ የሚውል ነው። ይህ ሒደት የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ እሴት በመጨመር፣ ፈጠራንና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የሚኖረው ሚና ጉልህ ነው። ከአሳታፊ/አካታች ባንክ ጋር በተያያዘ ያለው አንዱ የግንዛቤ ስህተት ባንኩን እንደ አንድ የንግድ ተቋም ከመመልከት ይልቅ እንደ የሃይማኖት አልያም የተራድዖ ተቋም ከመመልከት የሚመነጭ ነው።
አሳታፊ ባንክ ግብይቱ ከወለድ ነፃ በሆነ መልኩ የገንዘብ ብድር ላይ ሳይሆን እሴት የሚፈጥር የዕቃና ንብረት ግብይት ላይ ተመስርቶ አገልግሎቱን የሚሰጥ የፋይናንስ አገናኝ (value based intermediary) ተቋም ነው። እሴትን መሰረት ያደረገ የፋይናንስ አገናኝነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ2004 ጀምሮ ሲያቀነቅነው የነበረ መርህ ነው። የአሳታፊ ባንክ ቋሚ እሴቶቹ ትርፍና ኪሳራ መጋራት፤ ገንዘብ ሰጥቶ ተጨማሪ ገንዘብ መቀበል ሳይሆን እሴት የሚፈጥሩ የዕቃና ንብረት ግብይት እንዲሁም ግብረገባዊ የሥራ መሰክ ላይ መሰማራት (socially responsible investment) ይህም እንደአልኮል፣ ሲጋራ፣ የወሲብ ንግድ፣ ቁማር፣ የአራጣ መሰረት ያላቸው የሥራ መሰኮች ላይ አለመሰማራትን ወዘተ ያካትታል። ይህን አገልግሎቱን በሦስት ተቋማዊ የመዋቅር እርከኖች ይሰጣል።
የመጀመሪያው የአገልግሎት መዋቅር የመስኮት አገልግሎት (Window banking) ሲሆን በመደበኛው ባንክ ውስጥ የብቻው መሰኮት በማዘጋጀት ደንበኞች የሚሰተናገዱበት ሒደት ነው። ኹለተኛው የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት ራሱን በቻለ ቅርንጫፍ (Subsidary) የሚሰጥ ሲሆን በዋናነት ደንበኞች ዘንድ የሚኖረን ከመደበኛው ጋር የአገልግሎት መቀላቀል ስጋትን መቀነስን ታሳቢ ያደረገና ወደ ሙሉ ከወለድአልባ ባንክነት መሸጋገሪያ ድልድይ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ወደዚህ አገልግሎት ለመሸጋገር ቅደመጥናት ላይ እንደሆኑ መረጃዎች እየተሰሙ ይገኛሉ። ሦሰተኛው የአግልግሎት መሰጫ ተቋማዊ ቅርፅ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቃል የገቡት ይኼኛው የባንክ ተቋማዊ ቅርፅ ተግባረዊ እንዲደረግ ነው።
አገልግሎቱ በኢትዮጵያ እየተሰጠና እየዳበረ ባለበት አገር ራሱን ችሎ ከወለድ አልባ የሆነ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ለመመሰረት የሚደረግ እንቅስቃሴ ከውጭ ኀይሎች ጋር ለማያያዝና ፍርሃት ለመፍጠር የተሞከረበት ሒደት ፀሀፊው ይነገር ችግራቸው ከአግልግሎቱ ሳይሆን ከሙስሊሙ ማኅበሰረብ ጋር ይሆን እንዴ የሚል ጥያቄ የሚያጭር ነው።
ሥጋት ነጋዴዎች
በአገራችን የሙስሊም አክራሪነትን በማስመለከት በርካታ መጻሕፍት ተፅፈዋል፤ ሰብከቶች ተደርገዋል፤ የሃይማኖታዊ ጋዜጣና መጽሔቶችን ዓምድ ተጣቧል። እነዚህ ሥጋት የመፍጠር ሒደቶች ተወልጄ ያደኩበት ሰፈር ጎጃም በረንዳ አካባቢ ያሉ መንጩዎች (ቀምተው ሯጮች) የሰው ንብረት ቀምተው ሲሮጡ እንዳይያዙ ሌባ ሌባ እያሉ የሚሮጡትን ይመስለኛል።
ሥጋት የመፍጠሩ ሒደት በራሱ ግብ ሳይሆን በቀጣይ እያንዳንዱ የሙስሊም እንቅስቃሴ በደኅንነት መነፅር እንዲታይ መደላደል የሚፈጥር መሸጋገሪያ ነው። በዚህም ምክንያት ሕዝባዊተ ዋስዖው (Public discourse) በደኅንነት ትርክት ይሞላል። እነዚህ ሒደቶች በደፈናው ሳይሆን በሽፋን የሚደረጉ ናቸው። በዋናነት ተገፍተው የነበሩት ሙስሊሞች በአገሪቱ የተለያዩ መድረኮች ላይ መታየት መጀመር፤ በዘውዳዊውም ሆነ በወታደራዊው ስርዓት የማይታሰቡ የነበሩት የአምልኮ ቦታ ግንባታዎችና የሃይማኖት ትምህርት መሰፋፋት፣ የባሕላዊና ሃይማኖታዊ ማንነቶች በአደባባይ መንፃባረቅ፣ የትምህርት መሰፋፋትና የቴክኖሎጂ መዘመን የወለደው ማኅበረሳባዊ ዕድገት እንዲሁም ከጂኦፖለቲካዊና ዓለም ዐቀፍ ክስተቶች ተያያዥ ተደርገው ለሥጋት መፈጠሪያ በሒደትም የደኅንነት ተዋስዖ መቀመሪያ ሽፋን ይደረጋሉ።
የሙስሊሞች የዜግነት ጥያቄዎችም በይነገር የሥጋት ንግዳቸው ግብዓት ከመሆን አልተረፉም። የሙስሊሞችን ጥያቄ የምሁራን ጥያቄ ብቻ አድርጎ ማጥበብ ብሎም ከ1966 ጀምሮ አደባባይ የዋሉትን የሕገ መንግሥታዊ መብቶቻችን ይከበሩ ጥያቄዎች ያልጠሩ ብሎ መግለፅ የሥጋት ንግዱ ቁልፍ የማሻሻጫ ስትራቴጂ እንዲሁም ለአንባቢ የራሱን የሥጋት ምስል እንዲፈጥር ሜዳውን የማደላደል ሥራ ነው። ብሔርና ብሔረሰቦች፣ ሃይማኖትና ባሕሎች በኢሕአዴግ ዘመን ያገኙት አንፃራዊ ነፃነት በተለይም አሁን አገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የምትደርገው ጥረት ይህን አንፃራዊ ነፃነት የሚያጠናክረው መሆኑ በቀዳሚዎቹ ዘመናት ብቸኛ ተጠቃሚ የሆኑ ቡድኖችን (previlaged groups) ምቾት ሊነሳቸው እንደሚችል መገመት አይከብድም። የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባሕልና ፖለቲካ ተመራማሪ የሆኑት ጆን አቢኒክ (ፕ/ር) አንፃራዊ ነፃነቶች የፈጠሯቸው የሙስሊም ኢትዮጵያውያን መነቃቃት ፖለቲካዊ ቅርፅ ያልያዘ ዜግነትን የማስረፅ ሒደት ቢሆንም በሌሎች እምነት ተከታዬች ግን በበጎ እንዳልታ ይጠቅሳሉ።
ሥጋትን ፈጥሮ መነገድና ማኅበራዊ አለመተማመንን ማሰፋፋት እጅግ ቀላሉ ሥራ ነው። ሰላምና መረጋጋት የራቃት፣ ኢኮኖሚዋ ክፉኛ የታደከመ፣ የዜጎች መፈናቀል ከዕለታዊ ዜናነት ተሻግሮ የተለመደበት፣ የብሔር ግጭትና ጥላቻ የተካረረበት፣ የደቦ ፍትሕ የሚዘወተርበት ተጨባጭ ላይ የምትገኘው አገራችን ግን ከየትኛው ጊዜ ባሸገር የሚያሻት ማኅበራዊ መተማመንን ማስፋት ነው። በዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ሁሉም ወገን የተሻለች አገር ለመገንባት ፍላጎቱን የሚገራበት እንጂ ተጠቃሚነቱን ለማጉላት ማኅበራዊ ጥርጣሬ የሚፈጥርበት እንዳልሆነ ብዙኀኑን የሚያሰማማ ነው። ፀሀፊው ግን ለሁሉም የሚመች፣ በመከባባር፣ በጋራ ተጠቃሚነትና በመተመቻማችነት ላይ የሚመሰረት አገርን ሳይሆን አግላይና ጠቅላይ የአንድ ወገን አገር ለመገንባት ጡብ ለማቀበል በሚመሰል መልኩ በሥጋት ንግዳቸው ማኅበራዊ ጥርጣሬ ማከፋፈልን መርጠዋል።
የሙስሊም ፖለቲካና ኢስላማዊ ፖለቲካ
የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲው የታሪክ ምሁር ጀሚል አይድን “The Idea of the Muslim world” በተሰኘው መፅሀፉ ሙስሊሙን ለመወንጀልና ለማጥቃት እንዲሁም የሙስሊም ፍራቻን (islamophobia) ለማሳፋፋት ጥቅም ላይ ከሚውሉ ትርክቶች አንዱ ሙስሊሙን ልክ እንደ አንድ ሕዝብ በመጨፍለቅ የሙስሊሙ ዓለም በሚል በተፈጠረ ሐሳዊ ተዋስዖ ማቆር ነው ሲል ይሞግታል። ይህ ሐሳዊ ተዋስዖ የሙስሊሞችን የፍላጎት መለያየት፣ ብዙኀ ማንነትን በመካድ ላይ የተገነባ ነው።
ይናገር የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለመዳሰስ ይህንኑ አንድ ሕዝብ የማድረግና የሌሎች ማንነቶች ገዢ ተፅዕኖ በማሳነስ ሐሳዊ ተዋስዖ በመፍጠር ላይ የመሰረተ ነው። ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች ማንነታቸውና ፍላጎታቸው የተለያየ እንደመሆኑ መጠን አንድ ፖለቲካዊ ራዕይ ሊኖራቸው አይችልም። ፌዴራላዊ ስርዓትን የሚያቀነቅን እንዲሁም የዚሁ ተቃራኒ የሆነውን አኀዳዊ ሰርዓት የሚደገፍ፤ ሊበራል እንዲሁም ኮንሰርቫቲቭ፤ የልማታዊ መንግሥት የሚመርጥ እንዲሁም የነፃ ገበያ መንግሥት የሚደግፍ፣ የዘውግ ፖለቲካን የሚያቀነቅን እንዲሁም ተቃራኒውን የዜግነት ፖለቲካ የሚደግፍ እንደ ሌላው ሕዝብ ሁሉ የሚቃረኑና የሚጋጩ ህልምና ራዕዬች ያሉት ስብጥር ሕዝብ ነው። መሰል ሕዝብ በአንድ የፖለቲካ ራዕይ ሥር ሊጠለል አይችልም። አንዱ ብሔር ሌላውን ሲያፈናቅል የሃይማኖት ተመሳሳይነት ያላገደው ለዚሁ ነው።
ኢትዮጵያዊ ሙስሊም እንደ ፖለቲካዊ ዝንባሌው በሚያመቸው የፖለቲካ አስተሳሰብ ማዕቀፍ መሳተፍ መብቱ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ግዴታውም ጭምር ነው። ይህን የዜግነት መብትና ግዴታው የሆነውን በመረጠውና በሚመቸው የፖለቲካ ራዕይ ሥር መሳተፉ ኢስላማዊ ፖለቲካ የሚባልበት አመክኗዊ መደገፊያ የለም። የሙስሊሙን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በሐሳዊ የኢስላማዊ ፖለቲካ ተዋስዖ ቅርጫት ውስጥ ማጎር ሙስሊሞች በዜግነታቸው ከሚጎናፀፉት ከማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማግለል (De-politicization) ያለመው የሥጋት ንግድ ሌላኛው የማርኬቲንግ ስትራቴጂ ነው። ይህ በሥጋት ንግድ ሙስሊሞችን የመግፋት ሒደት አሉታዊ ውጤቱ አልተሰተዋለም። በሴኩላር የፖለቲካ ምኅዳር ውሰጥ አጀንዳቸውን ይዘው እንዳይጫወቱ የተገፉ ዜጎች ለሃይማኖት አክራሪነት ቅርብ ይሆናሉ።
ሃይማኖታዊ ፖለቲካም ሆነ አክራሪነት ያለ አገር መንግሥቱ ተቋማት መዋቅራዊ ድጋፍ ቢበቅል እንኳን ቶሎ የሚከስም አረም መሆኑን ምሁራን ይገለፃሉ። ስለዚህም አገራችን የሃይማኖታዊ አክራሪነትም ሆነ የሃይማኖት ፖለቲካ ሥጋት ሊኖርባት የሚችል ከሆነ ከአገረ መንግሥቱ ጠንካራ መዋቅራ ድጋፍ ሊያገኝ ከሚችልበት አቅጣጫ ነው። የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ሊያስተሳስር የሚችለው ሴኩላር የሆነ የመንግሥት መዋቅርን መደገፋቸውና ለዚህም መታገላቸው ብቻና ብቻ ነው። በ1966ቱ ታሪካዊ ሰልፍም ይሁን ባለፉት ሰባት ዓመታት በተደጋጋሚ ያሰተጋቡት መፈክር የሃይማኖትና የመንግሥት መነጣጠል ላይ ያተኮረ መሆኑ የአደባባይ እውነት ነው። ጆን አቢኒክ እንደሚሉት እሰከ 1974 ድረስ አገራችን ያሳለፈችው በሃይማኖታዊ መንግሥት ሥር በመሆኑና ሃይማኖት የፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ምንጭ በመሆኑ ምክንያት የደረሰባቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መገለል ምክንያት የሃይማኖትን መንግሥት መለያየት በጋራ የሚጋሩት፣ የታገሉለትና የማይደራደሩበት መርህ ነው።
ኢብራሒም አብዱ በኢሜል አድራሻቸው
[email protected] ይገኛሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011



