የኢንተርኔቱን ባልቦላ ማን አጠፋው?

0
555

ከሰኔ 3/2011 ጀምሮ ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የኢንተርኔት አገልግሎት በመላው ኢትዮጵያ በከፊልና ሙሉ ለሙሉ የውሃ ሽታ ሆኖ መክረሙ ከፍተኛ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። ብዙዎቹ ተቋማት የአገልግሎት መስተጓጎል ያጋጠማቸው ሲሆን በተለይ በኢንትርኔት ላይ ጥገኛ የሆኑት የንግድ ተቋማት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ካሰሟቸው ሮሮዎች መታዘብ ይቻላል። እንደአዲስ ማለዳ ያሉ መገናኛ ብዙኀን ላይም ከፍተኛ ጫና አሳድሮ አልፏል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የአጭር ጽሁፍ መልዕክት ልውውጥ አገልግሎትም የመቋረጥ ሰለባ ሆኖ ከርሟል።

የኢንትርኔት አገልግሎት አቅራቢው ኢትዮ ቴሌኮም ከመቋረጡ ጋር በተያያዘ የሰጠው ይፋዊ መግለጫ ባለመኖሩ ለአገልግሎቱ መቋረጥ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ መላምቶችን እንዲሰነዝሩ ክፍተት ፈጥሯል። በርግጥ ብዙዎች መቆራረጡን ከሰኔ 3 ጀምሮ በመሰጠት ላይ ከሚገኘው ብሔራዊ ፈተና ጋር አያይዘውታል። ይሁንና የትምህርት ሚኒስትር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ የኢንትርኔት መቋረጡ እየተሰጠ ካለው ብሔራዊ ፈተና ጋር ይያያዝ አይያያዝ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ማስታወቃቸው የበለጠ ብዥታን ፈጥሮ አልፏል። ሌሎች በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም ተጠልፎ ነው እንዲሁም የሚጠቀምባቸው መሣሪዎች ብልሽት አጋጥሟቸው ነው የሚሉ መላምቶችም ተሰንዝረዋል።

ረቡዕ፣ ሰኔ 5 በተለያዩ የቴሌቪዥን መስኮቶች ብቅ ያሉት የትምህርት ሚንስትሩ ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) የ10ኛ ብሔራዊ ፈተና በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁንና ይህ ነው የሚባል ችግር አለማጋጠሙን በገለጹበት መግለጫ ኢንተርኔት እንዲቋረጥ የተደረገው ከፈተናው ጋር በተያያዘ መሆኑንም በጨረፍታ መግለፃቸው ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የተሰጠ ብቸኛ የኢንትርኔት መቋረጥ ምክንያት ማረጋገጫ ሆኗል።

እንዲያውም ዘንቦብሽ እንደሚባለው የኢንትርኔት መቆራረጡ ከውሃና መብራት ጋር ተዳምሮ ለብዙዎች ምሬት ሰበብ ሲሆን አንዳዶች ደግሞ ‘ማሽላ እያረረ ይስቃል’ የሚለውን ብሒል በመከተል የተለያዩ ቀልዶች ፈጥረዋል፤ አዝናንተዋል። መረር ያላቸው ሌሎች ደግሞ እንደ ቲውተር ባሉ ማኅበራዊ ትስስር አውታሮች ኢትዮ ቴሌኮምን ለመክሰስ እንደሚፈልጉም አስታውቀዋል፤ ከልብ ይሁን ካንገት ባለየ መልኩ።

የሆነው ሆኖ በጣም ዘግይቶም ቢሆን ኢትዮ ቴሌኮም ማክሰኞ፣ ሰኔ 11 ባሰራጨው መግለጫ ምንም እንኳን ምክንያቱን ባይገልጽም ለአገልግሎቱ መቋጥ ደንበኞቹን ይቅርታ ጠይቋል። ደንበኞች ላልተጠቀሙበት አገልግሎት እንደማያስከፍልም አስታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here