- በኢትዮጵያ አንዲት ላም በቀን በአማካይ 1 ነጥብ 5 ሊትር ወተት ብቻ ትሰጣለች
የወተት ግብይት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የጥሬ ወተትና የወተት ተዋጽዖ ግብይት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ። አዋጁ አከፋፋዮች የግብይት ማዕከላት ሳይኖራቸው ወደ ሥራ መግባት እንደማይችሉ ይደነግጋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የወተት እጥረት እንዲሁም የዋጋ መናር እንዲከሰት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ፣ የሥርጭት ችግር መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት አዋጁ ዘላቂ መፍትሔ ይዞ የሚመጣ እንደሚሆንም ይጠበቃል ብሏል።
የኢንስትቲዩቱ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበሌ ለማ እንዳሉት ይህንን ችግር ለመቅረፍ የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው የጥሬ ወተትና የወተት ተዋጽዖ የማከፋፈል ሥራን በመከልከል የግብይት ስርዓቱን ወደ ሕጋዊው መስመር ለመክተት ይረዳልም ተብሏል። አከፋፋዮችም የግብይት ማዕከል ከመክፈት ባሻገር ማሰባሰቢያ ማዕከሎቻቸው ጥራታቸውን የጠበቁ መሆናቸው ማረጋገጫ ሳይሰጥ ወደ ሥራ መግባት እንደማይችልም አክለው ገልጸዋል።
ለማ እንደገለጹት ረቂቅ አዋጁ ከአምራቹ አርብቶ አደር ጀምሮ አቅራቢው፣ አቀናባሪውና አከፋፋዩ ሥራዎቻቸው በውል የታሰረ መሆኑን ይደነግጋል። እነዚህ አካላትና ተቋማት ውል ሲፈጽሙ የዋጋ፣ የጊዜና የጥራት መስፈርቶችንም ማስቀመጣቸው ግድ ይላል።
ለወተት የተመረጡ የእንስሳት ዝርያዎችን ለማሻሻል በ2010 ፖሊሲ የጸደቀ ሲሆን፣ በፖሊሲው መሰረት የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስቲትዩት ግንባታ እየተካሔደ እንደሆነም ታውቋል።
የወተት ጥራትን ለማስጠበቅ ከምርት ጀምሮ የእንስሳት መኖ፣ የጤና ክብካቤ፣ የወተት መያዣ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ የመገልገያ እቃዎችን መጠቀም አስገዳጅ የሚሆንበት የአሰራር ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ለማ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ወተት በሚፈለገው ደረጃ እንዳይመረት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የምርት እጥረት ማጋጠሙን የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። የዓለም ጤና ድርጅት አንድ ጤነኛ ሰው በዓመት 200 ሊትር ወተት ማግኝት አለበት ሲል ያወጣውን መስፈርት አገሪቷ እንደማታሟላም ታውቋል።
እንደለማ ገለፃ በኢትዮጵያ የተሻሻለ ዝርያ ያሉት የወተት ላሞች ብዛት አንድ በመቶ ብቻ ሲሆኑ 99 በመቶ የሚሆኑት የወተት ላሞች በባሕላዊ መንገድ የምናመርታቸው ላሞች ናቸው ብለዋል።
በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ልቀው የሔዱ ሌሎች አገሮች በቀን ከአንዲት ላም ብቻ እስከ 50 ሊትር ወተት ሲሰበስቡ በኢትዮጵያ አንዲት ላም በቀን የምትሰጠው የወተት መጠን በአማካይ 1 ነጥብ 5 ሊትር ብቻ ነው የሚሉት ደበሌ፣ በዚህም ምክንያት በዓመት 4 ቢሊዮን ሊትር ወተት ብቻ ለማምረት ተገደናል ይላሉ። ከ100 ሚሊዮን የዘለለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓመት ማግኘት የሚገባው የወተት መጠን 22 ቢሊዮን ሊትር ቢሆንም ያንን ማሳካት አልቻለችም ሲሉም ያክላሉ።
ግብርና ሚኒስቴር በግንቦት 23/2011 የወተት ቀንን አስመልክቶ ባዘጋጅው ውይይት ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪ ስንታየሁ ይግረም (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ምርታማነታቸውን በከፍተኛ ቴክኖሎጂ ያስደገፉ እስራኤልን የመሰሉ አገሮች ከአንድ ላም በዓመት እስከ 11 ሺሕ ሊትር ወተት ያገኛሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011



