አገራዊ ደኅንነት እና ተቋማዊው ማሻሻያ

0
1454

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው የለውጥ አመራር ሥልጣነ መንበሩን ከተቆጣጠረ መጋቢት 24/2010 ጀምሮ በአገር ደረጃ መነቃቃትና ተስፋ የመፍጠሩን ያክል የሰላምና ደኅንነት ሥጋቶች ብሎም ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተፈጥረዋል፤ አሁንም ሥጋቱም አለመረጋጋቱም አንዳንድ ጊዜ እየጋመ ሌላ ጊዜ ደግሞ እየቀዘቀዘ ቀጥሏል። ግጭቶችና አለመረጋጋት ክቡሩን የሰው ሕይወት በማሳጣት ዋጋ አስከፍሏል፤ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ከቀያቸው አፈናቅሏቸዋል፤ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ “ነገ ምን ይዞብኝ ይመጣ ይሆን?” በሚል ሥጋት ተሸብበዋል።

አገር ሰላም እንድትሆን፣ ከውስጥም ሆነ ከውጪ አደጋና ጥቃት እንድትጠበቅ፣ የተረጋጋና ከአሻጥር የፀዳ የምጣኔ ሀብት መስተጋብር እንዲኖርና በማድረግ የአገር ሰላምና ደኅንነትን በማስጠበቅ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት ምትክ አልባ ሚና ይጫወታሉ።

ኢትዮጵያም ከአመት በፊት ባካሔደችው የፖለቲካ ለውጥ ሰበብ የአንዳንድ ተቋማት ማሻሻያዎች ተግባራዊ ማድረጓ ይታወቃል፤ በግንባር ቀደምትነትም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት እንዲሁም መከላከያው ይጠቀሳሉ። በተለይ ከመረጃና ደኅንነት ጋር በተያያዘ የተደረገው ማሻሻያ መደረጉ መልካም ሆኖ የብዙ ሙያተኞች ከሥራ ገበታቸው መሰናበት ተቋሙ በክፍተት እንዲዋጥ በማድረግ የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅ ረገድ ዋጋ እያስከፈለ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ ከመረጃና ደኅንነት ተቋማትን ከተጨባጭ የአገር ሁኔታ አንጻር ያሉበት ደካማ ጎኖች ማጣቀሻዎችን አገላብጦ፣ የቀድሞ የደኅንነት አባላትንና በጉዳዩ ዙሪያ ጥናትና ምርምር ያካሔዱ ባለሙያዎችና አነናግሮ የሐተታ ዘ ማለዳ ገዳይ አድርጎታል።

የአገር ደህንነትን በተመለከተ በርካታ ጥናታዊ ፅሑፎችና እልፍ ጊዜ በሰላምና ደህንነት ዙሪያ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ግለሰቦች እንዲሁም በመከላከያ እና ደህንነት እንዲሁም ፖሊስ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች በገፅ ለገፅ ውይይት አድርገዋል። ይህ በመላው አለም አንገብጋቢ የሆነው የአገር ደህንነት ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ የዜጎች የዕለት ተዕለት ጥያቄ እንዲሁም ስጋት መሆን ከጀመረ ዋል አደር ብሏል ። ለዚህ ደግሞ ከመጀመሪያው በግለሰብ ደረጃ ያልተረጋገጡ ደህንነቶች የኋላ ኋላ አድገውና ሰፍተው ወደ ማኅበረሰብ እና አገር ደህንነት ስጋቶች መተለቃቸው አይቀሬ እንደሆኑ በተለያዩ አገራት ሰላምና ደህንነት ዙሪያ የተፃፉ ጥናቶች ያመላክታሉ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለይም ደግሞ በግለሰብ ደህንነት ዙሪያ በርካታ ጉድለቶች እና ክፍተቶች ሲሰተዋሉ እና በአለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲስተጋቡ እንደነበሩ የአደባባይ ምስጢሮች ናቸው። ይህንም ምክንያት ተደርጎ በርካታ ጥናታዊ ፅሑፎች በግለሰቦች ደህንነት ዙሪያ ተፅፈው ለንባብ በቅተዋል። የግለሰብ ደህንነት በፖለቲካ ሳይንስ አግባብ በተቀመጠው ጥሬ ትርጉሙ ’’የሰውን ልጅ ከተወሳሰበው ማኅበራዊ ግንኙነቱ ጋር ቅድሚያ መስጠት’’ ማለት እንደሆነ ያስቀምጣል።

ይህን በተመለከተ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም በመምህርነትና በከፍተኛ ተመራማሪነት የሚገኙት ምሁር በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያቸውን ያስቀምጣሉ። ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ሲስተዋል የቆየው አገር ደህንነትን ከማስጠበቅ አኳያ ክፍተቶች በመጀመሪያ የግለሰቦችን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ድክመት መታየቱ እንደሆነ በመጥቀስ ይጀምራሉ። አያይዘውም በተለይ ደግሞ የአገር ደህንነትን በኢትዮጵያ ደረጃ ስንመለከት በተቋማት ደረጃ የሚጠበቅ ብቻ አለመሆኑ የጉዳዩን ትልቅነት ሲገልፅ አገር በብሔር ከመካለል ጋር ተያይዞ በአንድ ልብ እና አላማ የአገርን ደህንነት ከውስጣዊ አለመረጋጋቶች ለማዳን ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንደሚኖረው ያብራራሉ። አዲስ ማለዳ የሰላምና ደህንነት ምሁሩን አሁን ላይ ባለው አዲስ የለውጥ አመራር ጋር በተያያዘ የሚታዩትን አገራዊ አለመረጋጋቶች እና ከዚህም ጋር ተያይዞ ዜጎች ከመፈናቀላቸው፣ ከመሞታቸው እና በቅርቡም በመንግስት ደረጃ የተቃጣውን የመፈንቅለ መንግስት ዙሪያ ጥያቄ አቅርባለች። በመጀመሪያ ደረጃ የአገር ደህንነት ማለት ሰፊ ፅንሰ ሃሳብ የሚይዝ ጉዳይ ሆኖ ሲያበቃ በምጣኔ ሃብት፣ በፀጥታ እና ደህንነት ፣ በወጣቶች ስራ ፈጠራ እና በሌሎች መሰል ሴክተሮች ሊረጋገጥና ተመጋጋቢ ጉዳዮችን ይዞ የሚሄድ እንደሆነ ይናገራሉ።

በፀጥታ ጉዳይ ከተባለ ከለውጡ በኋላ በለውጡ አመራሮች የተወሰደው ብሔራዊ መረጃና ደሕንነት ቢሮ ላይ የሪፎርም ስራ ከፍተኛ ከፍተት ለማስከተሉ ምንም አይነት ጥርጣሬ እንደሌላቸው ያትታሉ። በዚህ መስሪያ ቤት የግድ ነባር ከፍተኛ አመራሮች እንዲቀመጡ ባይደረግ እንኳን ከታች በሙያቸው ሲሰሩ የነበሩና እስከ ታች ድረስ የደህንነት መዋቅሩን የሚያውቁ ባለሙያዎች በነበሩበት ቦታ በመሆን የሪፎርሙ አካል ሆነው መቀጠል የሚችሉበት አጋጣሚዎች ቢኖሩ ለውጡ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የሚታዩት አገራዊ ችግሮች ባልተፈጠሩ ነበር። ቀጥለውም አንድ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ የመጀመሪያው ስራ መሆን የሚገባው የደህንነት መስሪያ ቤቱን ማጠናከር ሲሆን በመከላከያ ውስጥም በተጓዳኝ የመከላከያ ደህንነትን ማጠናከር ይኖርበታል ሲሉ ይገልፃሉ። ለዚህ ደግሞ እንደምሳሌ የሚያነሱት በ2011 መጀመሪያዎቹ ወራት አካባቢ ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደ ምኒልክ ቤተ መንግስት ጎራ ያሉትን የመከላከያ ኃይል አባላትን ነው። ‹‹የሚያነሱት ጥያቄ ይኖራቸዋል፤ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ተራ ግለሰቦች ሳይሆኑ የታጠቁ ግለሰቦች ናቸው ስለዚህ በወታደር ደንብ ጥያቄያቸውን ማስተጋባት ይኖርባቸው ነበር። ነገር ግን ከኹሉም አስደንጋጩ ነገር ከተነሱበት ቦታ ቤተ መንግስት እስኪደርሱ ድረስ በብሔራዊ ደህንነት በኩል ወይም በመከላከያ ውስጥ ባለው የደህንነት መረብ ቅንጅታዊ ስራዎች ተሰርተው መንገድ ላይ መገታት ይቻል ነበር ። ነገር ግን ከፍተቱ እጅግ ሰፊ ነበርና በቀጥታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉበት ቦታ ገብተዋል››። ይላሉ።

ይህን የሚጋሩት ደግሞ በጋምቢያ ባንጁል የሰላምና ደህንነት ዙሪያ በአንድ የአማካሪ ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ አጥኚነት እያገለገሉ የሚገኙት ኤልሻዳይ መስፍን ሃሳባቸውን እንዲህ ይገልፃሉ። ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ አገር ደህንነት ሕዝብ ከመንግስት የሚጠብቀው ዋነኛው ጉዳይ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን መንግስት ከሕዝቡ ባልተለየ ሥጋት ውስጥ ያለ ይመስላል ወይም ደግሞ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያሉት ደህንነት መዋቅራዊ ሰዎች ተገቢውን መረጃ እያደረሱት አይደለም ማለት ነው።›› ይላሉ። ቀጥለውም ከመጀመሪያው ጀምሮ መንግስት በውጭ አገራት ሆነው ሲታገሉ የነበሩትን ኃይሎች በመጀመሪያዎቹ የሽግግር ሰዓታት ወደ አገር እንዲገቡ መፍቀዱ ትልቁን ከፍተት ፈጥሯል የሚሉት ኤልሻዳይ በደህንነቱ ላይ ሪፎርም ይኖራል ከተባለ መጀመሪያ መደረግ ያለበት ነገር እስከ ታችኛው የወረዳ እና ቀበሌ ደረጃ ድረስ የተባለውን ሪፎርም ተከትሎ መዘርጋት ይገባ ነበር ። እንደምክንያት የሚያስቀምጡት ደግሞ ነገሮች መልካቸውን የቀየሩት መናበብ በማይታይበት የደሕንነት መዋቅር ውስጥ በብሔር ተደራጅተው ሲታገሉ የነበሩ ኃይሎች ወደ ማኅበረሰባቸው በገቡ ማግስት መንግስታዊ መዋቅሮች በአንድ አዳር መፍረሳቸውን አውስተዋል።

ይህ ብቻ ሳይበቃም ያላቸውን የሕዝብ ድጋፍ በመጠቀም በመንግስት ላይ ያልተገባ ጫና በመፍጠር ወደ አልታሰበ አካሔድ እንዲያመራ መንግስትን የሚያስቱ በመኖራቸው አገራዊ ደሕንነቱ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አይነተኛ ምክንያት ናቸው ሲሉም አክለዋል።

ኤልሻዳይ ቀጥለውም በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግስታቸውን የ11 ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሳውን የክልል ጥያቄዎችን በተመለከተ ያነሱትንም እንደ አብነት ጠቅሰዋል። ‹‹እንደተባለው ክልል የመሆን መብታቸው የተጠበቀላቸው የውሳኔውን ተራዘመብን በሚል ለሐምሌ 11/2011 ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማሰማት ቀጠሮ ይዘዋል›› መንግስት ግን በአደባባይ በቁጣ ምላሽ ከመስጠት አስቀድሞ የደሕንነት መዋቅሩን በአካባቢዎች ዘርግቶ ሊመጣ እና ሊደረግ የታሰበውን ሕገ ወጥ ተግባር ከቻለ ሙሉ በሙሉ ካልቻለ ደግሞ በከፊል የሚቆጣጠርበትን መንገድ ቢያመቻች ነገሮችን ማብረድ እንደሚቻል ጠቁመው ፤ ነገር ግን አሁንም በደሕንነቱ ውስጥ ያለው ክፍተት ይህንም ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ላይ ነው ብለው እንደማያምኑ አስረግጠዋል።

የአገር ደህንነት በእርግጥ በቀጥታ የሕዝብንና የአገርን ሰላም በማስጠበቅ ብቻ የሚገለፅ እንዳልሆነ ምሁራን ይገልፃሉ። ለምሳሌ የአገር ደሕንነት ከፖለቲካው እና ከደህንነት ባሻገር በኢኮኖሚም የሚገለፅበት አግባብ ትልቅ ነው። ሰላምና ደህንነት ምሁሩ በዚህም ላይ የሚሉት አለ። በሕጋዊ መንገድ ከሚነግዱት የንግዱ ማኅበረሰብ በተቃራኒው ቆመው ሰው ሰራሽ የዋጋ ግሽበቶችንና የኑሮ ውድነቶችን በሚፈጥሩ ነጋዴዎች ምክንያት የአገር ደህንነት አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ያስረዳሉ።

አያይዘውም በመጀመሪያ ደረጃ የኑሮ ውድነት የማይነካው የኅብረተሰብ ክፍል የለም ምናልባት ከፖለቲካው ርቆ የሚኖር እንኳን ቢሆን በኑሮ ውድነቱ ተማሮ ግን አደባባይ በመውጣት ጩኸቱን የማያሰማ እንደማይኖር በልበ ሙሉነት ተናግረው፤ በጎረቤት አገር የሱዳን ጉዳይ እና የአረብ አገራትን አብዮት መነሻዎች እንደአብነት ነክተዋል።

በዚህም ረገድ መንግስት የተጠናከረ የደህንነት መዋቅር ከሌለው ሕገ ወጥ ግብይቶችንና የዕቃ ክምችቶችን በመቆጣጠር ሰላማዊ እንቅስቃሴን በማስፈን ማስተዳደር ይከብደዋል የሚል ፍራቻ አለባቸው።

በአገር ውስጥ የዜጎችን ደህንነት ባለማረጋገጥ የአገርን ሕልውና ማረጋገጥ ከባድ እንደሆነ የሰላምና ደህንነት ልሒቃን በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። አገር በውስጥ ጉዳይ መረጋጋት እና ደህንነት ከሌለ ከውጭ ቀጥተኛ ወረራ እና ጥቃቶች መከላከል የማይታሰብ ነው። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ምሁራኖች የባለፉትን 27 ዓመታት እና አሁን ያለውን የለውጡ ኃይል ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ያለውን በንፅፅር ያስቀምጣሉ። በባለፉት ዓመታት መረጋጋቱ የተፈጠረበት መንገድ የሚደገፍ እና ትክክለኛ መንገድ ባይሆንም ነገር ግን በአንፃራዊነት መረጋጋቶች በኹሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የታዩበት ጊዜ ነበር ይላሉ። አያይዘውም ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ያለውን ደህንነት አገራዊ ደህንነት ከማረጋገጥ ባሻገርም በጎረቤት አገራት ላይ ቀጠናዊ የፖለቲካ የበላይነትን እስከመፍጠር የደረሰችበት ዘመን ነበር ብለዋል። ይህንም ተከትሎ ኢትዮጵያ በሱማሊያው የአሸባሪ ቡድን ላይ የወሰደችው ወታደራዊ እርምጃ ውጤት ማስመዝገቡን አውስተው በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ የተከሰተውን የደህንነት መዋቅር ክፍተት በመጠቀም አገራዊ አለመረጋገቶችን አልሸባብ ይፈጥር እንደነበር ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በዋናነት ከኤርትራ እና ከሱማሊያው አሸባሪ ቡድን በኩል ጥቃቶች ይሰነዘሩባት የነበረ ሲሆን ከአመት በፊት ወደ ስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ከኤርትራ ጋር ያለውን ውጥረት በዕርቅ መደምደማቸው የሚታወስ ነው።

በኢትዮጵያ በባለፉት ዓመታት የደህንነት እና የመከላከያ ተቋማት ከአመት አመት አቅማቸውን እያጠናከሩ በመምጣት ፈርጣማ እስከመሆን የደረሱበት ጊዜ እንደነበር በብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ለበርካታ ኣመታት ያገለገሉ እና አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ግለሰቦች ይናገራሉ።

ይታየው ይመር (ስማቸው የተቀየረ) በብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ከተራ የደህንነት አባልነት እስከ ከፍተኛ የስልጣን እርከን ድረስ በመሆን አገልግለዋል። ይታየው በተለያዩ የኢትዮጵያ ከፍሎች በመዘዋወር አገራዊ ደህንነት መዋቅሮችን በመዘርጋት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ከሚባሉ ግለሰቦች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱ ግለሰብ ናቸው። የለውጡ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ ከወራት በኋላ መንገዱን ጨርቅ ያድርግሎት የሚል ደብዳቤ ለውጡን ተከትሎ የቀድሞውን የደህንነት ኃላፊ ከተኩት ጀነራል አደም መሐመድ እንደደረሳቸው ተናግረዋል። ይታየው ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩም ‹‹ለዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል አገሬን አገልግያለሁ›› ሲሉ ይጀምራሉ ። ቀጥለውም አሁን ላይ ስላለው የደህንነት መዋቅር ሲናገሩ፤ ዋና ዋና ቦታዎች እና ልምድ ያለው ባለሙያ የሚያስፈልጋቸው ቦታዎች በአዳዲስና በደህንነት ዙሪያ ልምድ በሌላቸው ሰዎች በመሞላቱ ችግሮች ጎልተው በመውጣት በየዕለቱ የሚታዩ ናቸው ሲሉ ይናገራሉ።

አያይዘውም ለውጥ በደህንነት መስሪያ ቤቱ በኩል ተግባራዊ መሆን የለበትም አልልም የሚሉት ይታየው፤ ግን ለውጥ በምን ደረጃ ነው መተግበር ያለበት የሚለው ነገር ግን በደምብ ሊጤን ሚገባው ትልቅ ጉዳይ እንደነበር ተናግረዋል።

‹‹በእርግጥ ደህንነት መስሪያ ቤቱ ትልቅ ስህተቶችን በግላጭ ሲሰራ የነበረ መስሪያ ቤት ነው›› የሚሉት ይታየው ፤ ነገር ግን ምንም ጥፋት ያልተገኘባቸው እና በሙያቸው ሲያገለግሉ የነበሩ ግለሰቦች ለውጥ በሚል ሰበብ ከስራቸው መሰናበት እንደሌለባቸው ያስረዳሉ። ‹‹ሲጀመር የደህንነት ስራ እጅግ ውስብስብ ነው ። በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ አይነት በርካታ የተጠላለፈ ጉዳይ ባለበት አገር›› የሚሉት ይታየው የደህንነቱ ክፍተትን ከመጀመሪያው የለውጡ ጊዜያት ጀምሮ በግልፅ ይታዩ በነበሩ ችግሮች በደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ የተሰራውን ያልተጠና ለውጥ መገምገም ይቻላል ሲሉ ያትታሉ። አሁን ላይ ይታየው በጡረታ ሰበብ ከተሰናበቱበት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት በደጃፉ ከማለፍ የዘለለ ምንም አይነት ሥራ እየሰሩ አይደለም።

አዲስ ማለዳ በአገልግሎት ረጅም ዓመታትን ካገለገሉ ሰዎች መንግስት ምን ልምዶችን መቅሰም ነበረበት ስትል ጥያቄዋን በማቅረብ ወጋችንን ቀጥላለች። ‹‹ሲጀምር እኮ በየትኛውም አገር መንግስት ነባሩን የደህንነት መዋቅር በአንድ ጊዜ ለመለወጥ የሚጥርበትን አጋጣሚ በዕድሜየ አጋጥሞኝ አያውቅም ›› የመንግስት ለውጥ ተደርጎ ወታደራዊው መንግስት በተገረሰሰበት ወቅት በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ የነበሩትን ሙያተኞች ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚባል ደረጃ ባሉበት እንዲቀጥሉ በማድረግ ከነባሮች ትልቅ ልምድ መውሰዱን ተናግረዋል።

‹‹በነገራችን ላይ እስከ ቅርብ ጊዜ በጡረታ እስከተገለሉ ድረስ ከደርግ ዘመን ጀምረው ያገለገሉ የደህንነት አባላት ነበሩ›› ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከምስረታው ጀምሮ ሲያገለግሉ የነበሩትና በውጭ አገር ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት አበበ አላምረው(ስማቸው የተቀየረ) ለአመታት ባገለገሉበት መስሪያ ቤት በርካታ የአገርን ደህንነት መርህ በማድረግ ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራት መኖራቸውን ይገልፃሉ። ይሁን እንጂ አበበ እንደ ይታየው ኹሉ የነበረውን ክፍተት እና ይሰራ የነበረውን ስህተት ባይደብቁም አገራዊ ደህንነትን ከማስጠበቅ አንፃር ግን የተሔደበትን ፈታኝ እና ጠንካራ መንገድ እንዲህ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አውግተዋል። ‹‹በርካታ ጥፋቶች በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ተሰርተዋል ነገር ግን የአገር ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ነው የተደረጉት በሚል በበጎ ጎን የተወሰዱበት አጋጣሚ ነበር›› ይላሉ አያይዘውም ከቅርበ ጊዜ ወዲህ በተለይም ወር እና ኹለት ወር ወዲህ በአገር ላይ የተቃጣ የኢንፎርሚሽን መረብ ጥቃቶች መሰንዘራቸውን የሚጠቅሱት አበበ ይህ ደግሞ በመስሪያ ቤቱ የተካሔደው ለውጥ ሙያን ወይም ልምድን እንዲሁም ብቃትን ተከትሎ የተሰራ ባለመሆኑ ነው ሲሉ ይናገራሉ። እንደ እንግዳችን አስተያየት ከዚህ ቀደም ወደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት የሚገቡት ሰራተኞች ከተለያዩ የግል እና የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተማሩበት ትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው በላቀ ነጥብ የተመረቁ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል ። ‹‹ሰው የማይረዳው ነገር የፖለቲካ አቋሙ ታይቶ የሚቀጠር ይመስላቸዋል›› ይላሉ ስለ መስሪያ ቤቱ አሰራር እና የቅጥር ሁኔታ ሲያብራሩ። ነገር ግን አገርን ከጥቃት ተከላክሎ አገራዊ ደህንነትን ያስጠብቃሉ ተብሎ የሚታመንባቸውን ሰዎች በመመልመል በቦታው እንደሚያስቀምጡ ያስረዳሉ። ለውጡን ተከትሎ ግን እየተሰራ ያለው ነገር እንኳን የወደፊቱን አስበን ለመጠንቀቅ ቀርቶ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን የአሁኑን ደረጃ ተገዳድሮ ደህንነትን ማስጠበቅ ከባድ እንደሚያደርገው ይናገራሉ።

ይህን ሐሳብ የሚያጠናክርልን ደግሞ ሰኢድ ነጋሽ ለኹለተኛ ዲግሪ መመረቂያቸው በ2008 ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ተግዳሮቶች በአገር ደህንነት ላይ በሚል ርዕስ በአለም አቀፍ ደረጃ በኤስቶኒያ፣ በኢራን ፣ ቻይና እና አሜሪካ ከዚህ ቀደም የተቃጡ ጥቃቶችን እንደማሳያ በመጥቀስ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የታዩትን በባንኮች፣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ እና በኃይል ማመንጫዎች ያጋጠሙትን ጥቃቅን ግን ትልቅ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉዳዮችን አንስተዋል። ሰኢድ በጥናታቸው እንደመፍትሔ የሚያስቀምጡት ደግሞ የሰለጠነ የሰው ኃይልን በመጠቀም እና ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ግኝት በማካተት መሰረተ ልማቶችን ዘርግቶ አገርን ከጥቃት ማዳን ይገባል ሲሉ በጥናታቸው አስቀምጠዋል።

አገራዊ ደህንነትን በተመለከተ አዲስ የመጣውን የለውጥ አመራር ተከትሎ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታዩ ክፍተቶችን እና የመዋቅር መላላትን በበርካቶች ዘንድ ቅሬታን በመንግስት ላይ እንዲኖራቸው ማድረጋቸው በይፋ ሲነገር እና ሲሰማ ይታያል ። ነገር ግን ይህም ሆኖ ከላይ እንደማሳያ ያስቀመጥናቸው ሃሳበቸውን ከሰጡት ሙሁራን እና በደህንነት ሙያ ውስጥ ያገለገሉ እንዲሁም አሁን እያገለገሉ የሚገኙ ግለሰቦች በተቃራኒው ደግሞ የተለየ ሃሳባቸውን ይዘው ብቅ ያሉም አልታጡም። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት እኚህ ምሁር በፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት እና በሕግ የላቀ እውቀት ያላቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁር ናቸው። ‹‹ለውጥ ሲኖር እንደዚህ አይነት ክፍተቶች መታየታቸው የሚጠበቅ ነው ››ሲሉ ይጀምራሉ።

አዲሱ የለውጡ ኃይል በደህንነት ተቋማት ላይ ሪፎርሞችን ባያካሂድ ኖሮ ችግሮች ከዚህ የባሰ ይሆኑ እንደነበር ነው የሚገልፁት። እንደምክንያት የሚያነሱት ደግሞ ባለፉት አመታት ደህንነቱ የሕዝብን ደህንነት ከማስጠበቅ ይልቅ የፓርቲን ጥቅም ያስቀድም የነበረ መሆኑ እና በጥቅም የመተሳሰር እንጂ ለሙያቸው ተገዢ ያልሆኑ ግለሰቦች የነበሩበት መሆኑን ያነሳሉ። ቀጥለውም የአገር ውስጥ ደህንነትን ለማስጠበቅ ‹‹የደህንነት መስሪያቤቱ ላይ የተካሔዱት ሪፎርሞች አስቀድመው መደረጋቸው በቅርቡ በክልል እና በፌደራል ደረጃ የተሰነዘረው ጥቃት ረጅም ርቀቶችን ሳይሄድ መቆጣጠር ተችሏል›› የሚሉት ምሁሩ፤ ሪፎርሞች ባይካሔዱ ኖሮ ገና ገና ከጅምሩ ለውጥ የሚባለው ነገር በእንጭጩ ይቀጭ እንደነበር ነው የሚያስቀምጡት።

እንደማሳያም በሰኔ 16/2010 በጊዜው ወደ ስልጣን ከመጡ የወራት ዕድሜን ያስቆጠሩትን አዲሱን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን (ዶ/ር) ለመደገፍ በወጣው ሕዝብ ላይ የቦንብ ጥቃት መድረሱ በደህንነቱ መስሪያ ቤት የነበረው ለውጡን ‹‹እምቢ›› የማለት አንደምታ እንዳለው ነው የሚገልፁት። ‹‹በግሌ በደህንነት ተቋማት ላይ የተወሰደው ሪፎርም ለአገራዊ ደህንነት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ባይ ነኝ›› ብለው አሁንም በደምብ ሪፎርም መደረጉ እንደሚያጠራጥራቸው እና እንደገና መንግስት በአንክሮ ማጤን እና መስራት እንደሚኖርበት በመናገር ሃሳባቸውን ይደመድማሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here