ሞምባሳ፤ የኬንያዋ የባሕር ፈርጥ

0
995

ለሥራ በተለያዩ አገሮች የሚጓዙት ቤተልሔም ነጋሽ፥ ገላጭ በሆነው ጽሁፋቸው የቱሪስቶች መናኸሪያ የሆነችውን የኬንያዋን የባሕር ዳርቻ ከተማ ሞምባሳን ያስቃኙናል፤ በጎ በጎውን ብቻ ሳይሆን ሥጋት ናቸው ያሏቸውንም ጉዳዮች ከትበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ሞምባሳ ቀጥታ በረራ ያደርጋል። ኢቲ 322 ከዚህ ተነስቶ ወደ ሞምባሳ የሚሔደው ሲሆን ኢቲ 323 ወደ አዲስ አበባ የሚመላለሰው ነው። የሔድኩት እሁድ ቀን ቢሆንም ከመንገድ ላይ ትራፊኩ ጀምሮ የኤርፖርቱ ውስጥ ባልተለመደ መልኩ ተጨናንቆ ነበር። ሻንጣ ከሚረከቡበትና የመሳፈሪያ ቅጽ ከሚሰጡበት ጀምሮ እስከ ኢሚግሬሽኑ ያለወትሮ ረጅም ሰልፍ ሆኖ በመከራ ዘለቅን። የኢሚግሬሽን ኦፊሰሩ ከሳምንታት በፊት ወደ ጆሃንስበርግ ስሔድ እንደተጠየቅኩት ደከም ባለ የድምጽ ቅላፄ እስቲ የቤተሰብሽን ሥልክ አላለኝም። በወቅቱ ያንን ጥያቄ መጠየቄ የፈጠረብኝን ድንጋጤ አስታውሳለሁ። ለካ እንደወጡ መቅረትም አለ! አልፎ አልፎ አስታዋሽ ቢያስፈልግም ድንገት ሲጠየቁ ብዙ ያሳስባል።

ከአዲስ አበባ ሞምባሳ ያለው የ2፡20 ደቂቃ አካባቢ በረራ ብዙም ሳይቆይ ነበር የተጠናቀው። በነገራችሁ ላይ በኋላ ከሌሎች አገራት የመጡ የሔድኩበት ሥልጠና ተሳታፊዎች ሲነግሩኝ ሞምባሳ ለመምጣት ከየአገሮቻቸው ከተሞች ሌሎች ቦታዎች ሔዶ ከዚያ በናይሮቢ በኩል ማለፍን ይጠይቃል። ከባማኮ ሞምባሳ ለመምጣት በፓሪስ በኩል ማለፍ አልታያችሁም። በቀጥታ እዚህ ነው የመጣነው ስንል አላመኑም። እንዴት ይላሉ ግማሾቹ። አየር መንገዳችን! ነው መልሳችን።

ጆሴፍ
ሥሜን ከነአባቴ የያዘ ‘ፕላካርድ’ ይዞ እየጠበቀኝ ቀጥ ብዬ ወደ እሱ ሔድኩና እኔ ነኝ ካልኩት በኋላ አንቺ ነሽ? ብሎ አረጋግጦ ፣ የምገፋውን ጋሪ ተቀብሎ ወደ መኪና ማቆሚያው እየመራ ወስዶ መኪናው ጋር ሲያደርሰኝ
“ራሷ የኔ መኪና” አልኩ ወሬ ለመጀመር – ‘አይስ ብሬከር’ ይላል ፈረንጅ
የመጀመሪው ጥያቄ ሁሌም ሊያጋጥም የሚችለው የሥም ጉዳይ ነበር
“ሥምሽ ይገርማል፣ የየት አገር ሰው ሥም ነው ይሔ – ወንድ ነው ሴት? እያልኩ እያሰብኩ ነበር” አለኝ።
“እንዴ ኢትዮጵያዊ መሆኔን አላወቀወክም?” አልኩ በማዳነቅ
“ኢትዮጵያዊ ነሽ – በፍፁም አላወኩም” አለ
አገሬ ሥሜም የአባቴም ሥም የተለመደ ነው አልኩት
ጆሴፍ ከኬንያዋ የወደብ፣ የሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ሞቃታማ ከተማ አውሮፕላን ማረፊያ ለሳምንት በተከራየሁት የቢች ዳር ‘አፓርትመንት’ የተዘጋጀልኝ ሾፌር ነበር።

ከኤርፖርቱ ሳንወጣ የተከራየሁት ስቱዲዩ አፓርትመንት ባለቤት ደወለና ሊያናግረኝ እንደሚፈልግ ነግሮት ሥልኩን አቀበለኝ
“እንዴት ነሽ? ደህና ገባሽ ወይ፣ እንኳን ደህና መጣሽ” አለ የሳምንት አከራዬ
አመስግኜ ደህና መግባቴን ገልጬ እሱም ገብቼ ተረጋግቼ ቀስ ብዬ ክፍያ መፈፀም እንደምችል ነግሮኝ ተለያየን።

የደንበኛ መስተንግዷቸው ሁሌም ይደንቀኛል። ምነው የኛዎቹ ይህቺን ቢኮርጁ ብዬ ሳስብ ባለፈው ወር ጎንደር ለሥራ ስንሔድ የሆነውን አስታወሰኝ።
ታዬ በላይ የተባለ ሆቴል በሥራ ባልደረባዬ በኩል ተደውሎ ክፍል ሲያዝልን፥ ከአውሮፕላን ማረፊያው ትራንስፖርት እንደሚዘጋጅልን ጭምር ተነግሮን ነበር። ገና ከአዲስ አበባ ሳንነሳ ቀኑን ስንሠራ ውለን አመሻሸ ላይ ለመሔድ ያሰብነው ቀርቶ በረራችን ከ12፡40 ወደ 10፡25 መቀየሩ ሲነገረን እኛም ይህንኑ ለሆቴሉ አሳውቀን ነበር። ወደ አውሮፕላናችን ስንገባ ቀጥታ ጎንደር ሳይሆን በአክሱም በኩል እንደምንሔድ ሲነገረንም እንዲሁ የሰዓት ለውጡን ተናግረን ሳለ ኤርፖርት ስንደርስ የተባለው ትራንስፖርት አልነበረም። ብንደውልም ስንደውልበት የነበረው ሥልክ አልተነሳም። በታክሲ ደርሰን ለምን ስንልም ማንም ከቁብ አልቆጠረን። በዚያ ላይ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ የኤርፖርት ትራንስፖርት ጥያቄ ሳቀርብ እንዲሁ ችላ ተብዬ አንድ ፈረንጅ መጥቶ ገላገለኝ። መሔዴን ብቻ ስለፈለኩ እኔን አባ ከና ሳይሉ ለእሱ ማሽቃበጣቸውን ብዙም ጉዳዬ አላልኩት።

ወደ ሞምባሳ ስንመለስ በመንገድ ያንንም ይሔንንም ስናወራ ወሬያችንን ያቋርጠን የነበረው የሚኒ ባስ ታክሲዎች እብደት ነበር። አዲስ አበባ ምን እብድ ታክሲ ነጂ አለ ጎበዝ! የባሰ አለ አገርክን አትልቀቅ ይሔኔ ነው።

በዛች አንድ መኪና የማታስኬድ ጠባብ መንገድ ጥግ ጥጉን ደርበው ይመጡና ድንገት አፍጫውን ጥልቅ ለማድረግ ሲሞክሩ አንዴማ ገጩን ብዬ ልቤ ስንጥቅ!
መንገድ ብትሉ ከኤርፖርቱ ወደ ከተማው የሚወስደው መንገድ ሁኔታ ትንሽ ያሳስባል። ሹፌሬ የፍጥነት መንገድ እየተሠራ ነው ቢልም በየቦታው ያለው ግማሹ በጎርፍ ተወስዶ የተቦዳደሰ መንገድ ሌላው በጅምር የቀረ ነው።

ሚኒባሶቹ ተረጋግቼ እንዳልቀመጥ ሲያደርጉት የኔውም አገር ታክሲዎች እንዲህ ናቸው አልኩት ጆሴፍን። ተገረመ!
የሚኒባስ እብደት ጉዳይ አፍሪቃዊ ነው ብለን ደመደምን።

ሌላ አፍሪቃዊ ነገር ያየሁት ለሾፌሬ ባላወራውም – አንዱ ወጣት ድልድይ ሥር ቆሞ ሽንቱን ሲያንፎለፉለው ማየቴ!
የሞምባሳን የውቅያኖስ ዳርቻ በጽሁፍ መግለጽ መሞከር ድካም ነው። መጨረሻው የማይታየው ሰማያዊው የሕንድ ውቅያኖስ፣ በተለይ ወደ ማታ ላይ፣ ቀኑን ሙሉ ደርቆ በእግር መንሸራሸሪያ ሰፊ አሸዋ የነበረው መሬት መሔጃ እስኪታጣ ውሃው ሲናወጥ፣ አረፋ ደፍቆ የሚመጣው ሞገድ
ባለኅብረ ቀለሟ፣ ደማቋ ሞምባሳ የአገሪቱ የኢኮኖሚና የባሕል ማዕከል ናት ይሏታል። ከተመሰረተች ክፍለ ዘመናት በማስቆጠርም ከኬንያ ግዛቶች ቀዳሚዋ እንደሆነች መረጃዎች ይጠቅሳሉ። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ900 ዓመተ ዓለም እንደተመሰረተች ሲነገር ቅኝ ገዥዎች የመጡት ግን ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ነው። በቅድሚያ ፖርቱጋል (1593- 1698 እ.ኤ.አ) ቀጥሎ የኦማን ኢማማቶች (1698–1728) ከዚያም በድጋሚ የፖርቹጊዝ ኢምፓየር (1728–1729) የኦማን ኢማማቶች (1729–1824) ተፈራርቀውበታል። የብሪታኒያ ኢምፓየር (1824–1826) ገዝቷል የመስካትና ኦማን ሱልጣኔቶች (1826–1887) በመካከል ገብተው ብሪታኒያ በድጋሚ “ብሪቲሽ ምሥራቅ አፍሪካ” ግዛት (የአሁኗ ኬንያ አካል ሆና) ነፃ እስከ ወጣችበት 1887–1963 ቆይታለች። ሞምባሳ ከናይሮቢ ቀጥላ የኬንያ ኹለተኛዋ ትልቅ ከተማ ስትሆን የከተማው ነዋሪ 1.5 ሚሊዮን ይገመታል። በኬንያ ግዛት አጠራር መሠረት የሞምባሳ አውራጃ (ካውንቲ) መቀመጫ ስትሆን ከናይሮቢ ሌላ የመንግሥት መቀመጫ (ቤተ መንግሥት – ስቴት ሃውስ) ያለባት ከተማም ናት።

የከተማዋ ዋነኛ የመገበያያ ማዕከላትና ከላይ የጠቀስኩትን ቤተ መንግሥት ጨምሮ ጥሩ የሚባሉ የመኖሪያ ሥፍራዎችን፣ የመንግሥት ቢሮዎችንና ሆቴሎችን የሚይዘው የሞምባሳ ክፍል (ደሴት) ኪዚነጎ በመባል የሚጠራ ሲሆን ዙሪያውን የከበቧትና የባሕር ዳርቻዎቿን ይዞ ሰሜናዊ፣ ደቡባዊ የባሕር ዳርቻዎች ዋናው የሞምባሳ መሬት (Mombassa Mainland) በሚል ተከፋፍላለች።

ሞምባሳ ለመድረስ በሞይ ዓለም ዐቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ በኩል በአየር መግባት ዋነኛው ሲሆን በአውቶብስ ከዋና ከተማዋ ናይሮቢ የስምንት ሰዓት ጉዞ እንደሚጠይቅ (አምስት መቶ ሃያ ኪሎ ሜትሮች አካባቢ) ተነግሮኛል። በቅርቡ እድሳት የተደረገለት የናይሮቢ ሞምባሳ የባቡር ትራንስፖርትም ሌላው አማራጭ ነው። ከአካባቢው አገሮችም በጀልባና በየብስ በጥሩ ሁኔታ የሚገናኝ ሲሆን ቅርቡ ከመቶ ምናምን ኪሎ ሜትሮች በኋላ የሚገኘው ታንዛንያ ነው። በተጨማሪ ከዩጋንዳና ከሌሎች የአካባቢው አገራት ጋር የሕዝብ ትራስፖርት ስምሪት አለ። ከኢትዮጵያ በስተቀር እነኝህ አገራት የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የሚባል ማኅበር ስላላቸው ከአንዳቸው ወደ ሌላኛቸው አገር ለማቋረጥ ዜጎቻቸው ቪዛ አይጠየቁም።

ሞምባሳ ወደብ በምሥራቅ አፍሪቃ ከሚገኙት ትልቁ ሲሆን ኬንያ በርካታ ሸቀጦችን ውጪ የምታስመጣበትና የምትልክበት ነው። ሌላው በሞምባሳ ያስደነቀኝ ጉዳይ ከቦብባሳ ደሴት ወደ ደቡባዊው ዳርቻ ለመሔድ ውቅያኖሱ ጥልቅ በመሆኑና በሌሎችም ምክንያቶች ድልድይ ከመገንባት ይልቅ ሰፊ ጀልባ (Ferry ይሉታል) ከላይ ለሰዎች መቀመጫ የተሠሩ ብዙ ወንበሮች ያሉበት ከታች ባዶውን ሜዳ ሆኖ መኪኖች የሚጫኑበትን ተጠቅሞ በየ5 ደቂቃው ሲያሻግር ይውላል። ለመንገደኞች ነፃ ሲሆን ቀላል መኪኖች 1 ሺሕ 600 የኬንያ ሽልንግ (16 ዶላር) የጭነት መኪኖች 2 ሺሕ 400 (24 ዶላር) እንደሚከፍሉ ተነግሮናል። ከሥልጠናው ጋር ተያያዞ ለመስክ ጉብኝት ወደ ደቡብ ስንጓዝ ሚኒባሳችን በጀልባ ተጭና እኛ ከላይ ወንበር ላይ ሆነን ስናይ በየጉዞው የሚመላለሰውን ሕዝብ ብዛት ዓይተን ስንጠይቅ ኬንያዊ ባልደረባችን እንደነገረን በየቀኑ እስከ 400 ሺሕ ሰው (ተማሪዎችን ጨምሮ) ከደቡብ ወደ ደሴቲቷ እየመጣ ሥራ ሠርቶ ተምሮ ይመላለሳል። ደቡብ ዳርቻ ቤት ኪራይም ኑሮም ረከስ ስለሚል የቱሪስት ብዛት ከሚያደምቃት ሞምባሳ የተሻለ በመሆኑ ለብዙኀኑ ለኑሮ እንደሚመረጥ ተነግሮናል።

የሴኩሪቲ ወይም ደኅንነት ጉዳይ በቆይታችን ከዐሥራ አምስት የአፍሪቃ አገራት የመጣን የሥልጠናው ተሳታፊዎች ምንም ያክል ባያጋጥመንም፣ ማስጠንቀቂያና ይህን አድርጉ አታድርጉ መባል የተለመደ ነው። ወደዚህ ጉዞ ከማድረጌ በፊት የተሰጠኝ የሴኩሪቲ ሥልጠና በሌሎች ከተሞች እንደልቤ የምጠቀመውን ኡበርን ሳይቀር አይመከርም ስለተባለ ውድ የሆነውን የሆቴል ታክሲ መጠቀም የግድ ነበር። እየቆየን ግን ከሌሎች አገራት ከመጡ የሥራ ባልደረቦቼ ጋር ስንሆን ኡበር መጠቀም ብቻ ሳይሆን ከታክሲዎቹ ጋር ሲነፃፀር ዋጋው ርካሽ መሆኑንም ደርሰንበት፣ አዘውትረነው ነበር።

በኋላ ላይ ከተማ መሔድ ካልፈለግን ለሥልጠና ከቆየንበት ሆቴል እስከማረፊያችን በባሕር ዳርቻው በኩል በእግራችን የውቅያኖሱን የሚገርም ውበት እያደነቅን መጓዝ የዕለት ተግባራችን ነበር። ከባሕር ዳርቻው ውበት ቀጥሎ በሞምባሳ ያስደሰተኝ የአንድ የከተማ ፓርክ ቆይታችን ነበር። ሃለር ፓርክ ሲሰኝ በአካባቢውና በኬንያ ታዋቂ የሆነው ባብቡሪ ሲሚንቶ ፋብሪካ ለሲሚንቶ የሚሆን ድንጋይ ሲያወጣ የሠራውን ሰፊ ቦታ የሚሸፍን ጉድጓድ መልሶ ለማልማት ባደረገው ጥረት ፓርኩን መሥራቱን ሰምተናል። የዚህንም ውበት፣ ፀጥታ፣ የረጃጅም ዛፎቹን ግርማ፣ የአረንጓዴውን መስክ ድምቀትና ፀጥታ ለመግለጽ መሞከር ድካም ነው። በፓርኩ ቀጭኔ፣ ጉማሬ፣ አዞ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው እባቦች፣ ወፎች ይገኛሉ። የሔዱበት ሰዓት ከቀና ጉማሬና ቀጭኔ ሲመገቡ ያያሉ። በተለይ ቀጭኔዎቹን ከጧቱ አምስት ሰዓት ደርሰን ከባልደለቦቼ ጋር ፓርኩ የሸጠልንን የተቀመመ ምግብ ከእጃችን ለማብላት፣ ውበትና ግርማቸውን ለማድነቅ ዕድል አግኝተን የነበረ ሲሆን ጥቂት ቱሪስቶችና በርካታ ተማሪዎች በሳይንስ ስለተማሩት ስለአዞና ሌሎችን እንሰሳት በአካል እያዩ ገለፃ እየተደረገላቸው ለማየት ችለናል።

ስለውቢቷ ሞምባሳ እውነታም ያየሁትንም ይህቺን ካልኩ እንደማጠቃለያ የከተማዋ ሥጋት የሚባሉትን ትንሽ ምቾት የማይሰጡ ነገሮች ላንሳ።
እንደምታውቁት ሌላ አገር ስትሔዱ አገሬው በተለይ ሌሎች የአፍሪካ አገራት እንደ ኢትዮጵያውያን (ዛሬ ጊዜ እንኳን ኤርትራ ነሽ ኢትዮጵያ ተብሎ መጠየቀ አልፎ አልፎም ቢሆን ተለምዷል) ለየት ያለ መልክ ባለበት ከእናንተ ጋር የሚያዛምደው ወይም የሚያግባባው ፍለጋ አንዳንድ ነገር መጠቃቀሱን አይተውም። እንደመግባቢያም ነው። ሰላምታውን አፀፋ መልሳችሁ መንገዳችሁን ለመቀጠል ስትፈልጉ ግን አንዳንድ ጊዜ “የያዝኩትን ሸቀጥ ግዙኝ ወይም የት ነው ያረፍሽው? መቼ መጣሽ? መቼ ትሔጃለሽ? እዛኛው ደሴት ለመሔድ ጀልባ አለ፥ ለምን አልወስድሽም? ብዙ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሰልችቶ አልፈልግም ሲባልም ትንሽ የማስጨነቅ ነገር አስተውያለሁ። እኛጋ ምናልባት የቋንቋዋም ጉዳይ ስላለች (ከሌላ አገር በሚመጡ ባልደረቦቼ ልምድ እንደታዘብኩት) ከአንዳንድ የታክሲና የሆቴሎች ትራንስፖርት ሾፌር ውጪ ተራው መንገድ የሚገኘው ዜጋ ብዙ የሚሰለች አይደለም።

ሌላው ሞምባሳ የተለያዩ ዓይነት በሽታዎች እንዳሉ (ወባ ፣ የደንጊ ትኩሳት፣ ታይፎይድ ዲዘንትሪ) ተነግሮን ውሃ ከቧንቧ እንዳንጠጣ ስንመከር ከፀሐይ መጥለቅ በኋላ ባሕር ዳርቻው ላይ እንዳንቆይ፣ የሴክስ ቱሪዝም በቤተሰብ በሚደረግ ድጋፍና ማበረታቻ ጭምር ዕድሜያቸው ያልደረሱት ሳይቀር እንደሚሰማሩበት፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ወንዶች ባልደረቦቻችን ችግር ውስጥ እንዳይገቡም ተነግሮን ነበር። የሄሮይንና ኮኬይን ሕገወጥ ሽያጭ እንደተስፋፋ እዚህም ውስጥ መሳተፍ አደጋ እንደሆነም ጭምር።

ለእኔ በግሌ ሞምባሳና አካባቢዋ ላይ ያጠላ ጥላ ብዬ ያሰብኩት ግን የሃይማኖት ጽንፈኝነትና አክራሪነት ጉዳይ ነው። በከተማዋ ይንቀሳቀስ የነበረ ሞምባሳ ሪፐብሊካን ካውንስል ብሎ የሚጠራ መሰል ቡድን እንደነበር እንቅስቃሴው ተዳክሞ ቆይቶ ካለፈው ሚያዝያ ጀምሮ ማንሠራራት መጀመሩም ከሴኩሪቲ ኦፊሠራችን ተነግሮናል። ከሶማሊያ ጋር የቅርብ ጎረቤት መሆኗ ብቻ ሳይሆን ከሌላው የኬንያ አካል ገንጠል ብላ ያለች፣ በንጽጽር በአብላጫው የእስልምና እምነት ተከታዩች ያሉባት መሆኗ ከኬንያ ለመገንጠል እስከመፈለግ የደረሰ ለየት ያለ የፖለቲካ አዝማሚያ ያላት ከመሆኑ ጋር ተደምሮ አልሸባብ ወታደር ይመለምልባት የነበረች መሆኗም አንድ የከተማዋ እውነት ነው። ከሴኩሪቲ አንፃር በተለይ ከደሴቲቷ ባሉት ዳርቻዎች መውጣት የአደጋ ሥጋት ያለው በዚሁ ምክንያት ነው።

የምደመድመው ከሥልጠናው ጋር በተያያዘ የትምህርት ቤት ጉብኝት ወቅት ያጋጠመኝን በመግለጽ ነው። ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን ከተማሪቹ ጋር ለመወያየት ስንቀመጥ አስተማሪያቸው ሥማችንን፣ ሥራችንንና የመጣንበትን አገር እንድናስተዋውቅ ሲጠይቀን እነሱ በምላሹ ስለመጣንበት አገር የሚያውቁትን እንዲናገሩ ሲጋብዝ ሞዛምቢክ ሲባል “ደቡባዊ አፍሪካ ያለች፣ በፖርቹጊዝ ቅኝ የተገዛች” ብለው መለሱ። ዩጋንዳ ሲባል “ምሥራቅ አፍሪካ በእንግሊዝ ቅኝ የተገዛች” ተባለ። ተራዬ ደርሶ አገሬ ስትጠራ “ምሥራቅ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያን ማንም በቅኝ አልገዛትም” አሉ በአንድነት፤ ልክ ነው፣ እሷ ናት አገሬ አልኩ በምላሹ።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here