“ሴት ያሳደገቻቸው!”

0
991

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ልጆቻቸውን እናትም አባትም ሆነው ብቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶች በጣት የሚቆጠሩ አይደሉም። ያላቸውን ነገር ሁሉ ሰጥተው ልጆቻቸውን ለብቻቸው የሚንከባከቡ እናቶችን በቅርበት አይቻለሁ። የራሳቸውን ሕልምና ምኞት ጥለው በልጆቻቸው ነገን ለማየት በእያንዳንዷ ቀን የሚገጥማቸውን ፈተና በፈገግታ እያለፉ በጥንካሬና በተስፋ ልጆቻውን የሚሳድጉና ያሳደጉ እናቶችንም አውቃለሁ።

ልጅን ለብቻ ማሳደግ ለወላጅ እናቶች የሚሰጠውን ስሜት ባላውቅም ቀላል እንደማይሆን ለመገመት አያስቸግርም። በእርግጥም ቀላል አይሆንም፤ኑሮውና ከገንዘብ ጋር የተገናኙ ችግሮች እንዳሉ ሆነው የማኅበረሰቡ አቀባበልም በራሱ ፈተና ነው። ይሁንና ችግሩን ሁሉ ተወጥተው፤ ስለድካማቸው በልጆቻቸው ፍሬያማነት ክፍያን ያገኙ ብሎም ደስ የተሰኙ እናቶች ጥቂት አይደሉም።

በአገራችን ደግሞ እንደምታውቁት “ሴት ያሳደገው!” የሚባል ‘ስድብ’ መሳይ ነገር አለ። አስቸጋሪ፣ ያዘዙትን የማይሰማና እኩይ ተግባር ላይ የተገኘን ወጣት “ሴት ያሳደገው!” ይሉታል። እናት አትጋረፍም ወይም አትቆጣም ስለዚህ ልጇን ስርዓት ማስያዝ አትችልም ለማለት ይመስላል። የሚገርመው ታድያ በተለያየ ምክንያት ልጆች በእናት ብቻ እንዲያድጉ የሚገደዱባት አገር ላይ ነን። ይህ ነገሬ ምናልባት በጥናት የተደገፈ ማረጋገጫ የሚፈልግ ይሆናል እንጂ በዙሪያችን የምናየው እውነትም ሆነ የምናውቀው ታሪክ የሚያስረዳን ይህንኑ ነው። ተመልከቱ፥

በተለያየ ምክንያት በአገራችን በተነሱ የእርስ በርስ ጦርነቶች ወንዶች ሲዘምቱና ሲሰዉ ወይም መስዋዕት ሲሆኑ፤ ባለትዳር የሆኑት ልጆቻቸውን ለትዳር አጋራቸው ወይም ለሚስታቸው ትተው ነው። ታድያሳ የአገራችንን የግጭትና የጦርነት ታሪኮች እንዘርዝር? ከዛ ውጪ ከተለያዩ ሴቶች ልጆች የሚወልዱ መኖራቸውን ልብ ይሏል። ትዳር የሚያፈርሰው፣ “አባት አይደለሁም” ብሎ የሚክደው፣ “የት አውቅሻለሁ?” ብሎ ዞር በይልኝ የሚለውና የመሳሰለው ሳይቆጠር ማለት ነው።

እንዲህ ባለው እልፍ ምክንያት ልጅ በእናት ብቻ እንዲያድግ በሚገደድባት አገር ላይ ነው እንግዲህ “ሴት ያሳደገው!” ከስድብ ተራ የሚመደበው። ይህ ይቆየንና በእርግጥም ለእናት ብቻ ሳይሆን ለአባትም ቢሆን ልጅን ያለረዳት ለብቻ ማሳደግ ቀላል አይሆንም። ልጅ አዋቂ እስኪሆን ድረስ ማስቸገሩ አይቀርማ! መገራትና መስመር እንዲይዝ ማድረግ፤ በዚህም ላይ መሠረታዊ የሚባሉትን ጨምሮ ቁሳዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ያስፈልጋላ!

ይህን ደግሞ ብዙ እናቶች በብቃት ተወጥተውታል። እንደውም አሁን አሁን እንደምንሰማው ከሆነ ለብቻቸው ልጃቸውን የሚያሳድጉ እናቶች ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ። ከዚህም አልፈው “ልጆቼን ለብቻዬ የእናትም የአባትም ፍቅር እየሰጠሁ ማሳደግ እፈልጋለሁ” የሚሉ ሴቶች አሉ። በእርግጥ በአስገዳጅ ሁኔታ ካልሆነ በቀር ወላጆች ልጆቻውን በጋራ ቢያሳድጉ ይመከራል። ቢሆንም እናቶችም ልጆቻቸውን ለብቻቸው ሲያሳድጉ ያጎደሉት አንዳች እንደሌላ ብዙ ምስክሮች አለን!

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here