የስካይ ባስ ሠራተኞች የአገልግሎት ክፍያ እንዲከፈላቸው ተፈረደላቸው

0
1985
  • ድርጅቱ ከአምስት ወራት በፊት ሥራ ማቆሙ ታወቋል

ስካይ ባስ አክሲዮን ማኅበር ከገበያ መውጣቱን አስከትሎ ከሥራ ካሰናበታቸው 28 ሠራተኞቹ ውስጥ አዲስ አበባ የሚገኙ 18 ሠራተኞቹ በመሰረቱት ክስ ሰኔ 14/2011 እንደረቱ አስታወቁ። ሠራተኞቹ የስምነት ወር ደሞዝ እንደተፈረደላቸው ጠቅሰው ይህም ያለ ማስጠንቀቅያ በተቋረጠ የሥራ ውል ቅጣትን እንዲሁም የአገልግሎት ክፍያን እንደሚያጠቃልል ታወቋል።

የካቲት 15/2011 በተመሰረተው ክስ እንደሚያስረዳው አክስዮን ማኅበሩ የካቲት 1/2011 በሁሉም ክልሎች ያሉትን ቢሮችንም በመዝጋት ስራ ማቆሙን ይጠቅሳል።ባሱ ሲንቀሳቅሳቸው የነበሩ የትራንስፖርት መኪኖችም ያለ አገልግሎት የቆሙ ሲሆን ከሠራተኞቹ ጋር በተጀመረው ክስ አማካኝነትም ከታገዱት ንብረቶች መካከል እነኚህ መኪኖች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

አክስዮን ማኅበሩ ከብርሃን ባንክ 6 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከአባይ ባንክ 1 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ድርሻ የገዛ ሲሆን ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ያሉት በመሆኑ ምንም ዓይነት ኪሳራ ሊያጋጥመው አይችልም ሲሉ ሠራተኞቹ ተከራክረዋል።

ሠራተኞቹ አክስዮን ማህበሩ ሊዘጋ የቻለበት ምክንያት በማለት በመጀመርያ የአክስዮን ቦርዱ ችግር ሲሆን ሌላው ደግሞ የማኔጅመንት ችግር ነው። እንዲህ ዓይነቱ ችግር እንደሚያጋጥም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተናገርን ቢሆንም ሰሚ ግን አላገኘንም፤ የተመረጡ የቦርድም አባለትም ሆኑ ሥራ አስከያጅ ለቦታው የሚመጥኑ አልነበረም ብለዋል። በአጠቃላይ ከፍተኛ የሆነ የአስተዳደር ችግር ጎልቶ ይታይ ስለነበር ነው ሊዘጋ የቻለው ሲሉ ሠራተኞቹ ቅሬታቸውን አብራርተዋል።

ለሠራተኞቹ ከሚከፍለው ዕዳ ውጪ የብርሃን ባንክ አክስዮን ማኅበር የብድር ዕዳ እንዲሁም ደግሞ የአንድ ዓመት የቤት ኪራይ ዕዳ መክፈል እንዳልቻለ ድርጅቱ የቅርብ ምንጮች ተናግረዋል።

አክስዮን ማኅበሩ በውስጡ 40 ሠራተኞችን የሚስተዳድር የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ ከተሞች ያሉት ቢሮዎች ዝግ ሲሆኑ የትራንስፖርተት አገልግሎች ትኬት መቁረጫ ሱቆችም መዘጋታቸውን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

በዐሥር ዋና ዋና ከተሞች ላይ መዳረሻውን አድርጎ ሲሠራ የነበረው ስካይ ባስ አዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ጎንደር፣ ጂማ፣ ሐዋሳ፣ ጅጅጋ፣ ደሴ፣ መቀሌ እና አሶሳ ላይ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በእነዚህ ከተሞች ላይ ይሠሩ የነበሩ ዐሥር ሠራተኞችም እስከአሁን ክስ ባይመሰረቱም በቅርቡ ሊመሰርቱ እንደሚችሉ የቀድሞ ሥራ ባልደረቦቻቸው ገልፀዋል። ከ3 ሺሕ 400 በላይ የሚሆኑ ባለአክሲዮኖችን ይዞ የተመሰረተው ስካይ ባስ 60 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደነበረው ታውቋል።
አዲስ ማለዳ የስካይ ባስ የቦርድ ሊቀ መንበርንና ዋና ሥራ አስኪያጅን በሥልክ ለማነጋገር ያደረችው ጥረት አልተሳካም።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here