የተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ሕጉን በአስቸካይ ስብሰባ ሊያጸድቅ ይችላል ተባለ

0
689
  • ለዕጩ የምርጫ ተወዳዳሪ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ የሚከለክለው አንቀጽ ክርክር አስነስቷል

የምርጫና ፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ፣ ውይይት ተካሒዶበትና በቂ ግብዓት ተካቶበት የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ከመከፈቱ በፊት በአስቸካይ ስብሰባ ሊጸድቅ እንደሚችል አዲስ ማለዳ ከምርጫ ቦርድ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። በረቂቁ ዙሪያ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር የተደረገው ውይይትም ክርክር ማስነሳቱ ታውቋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ አዋጁ በቂ ግብአቶች ታክለውበት የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ከመጀመሩ በፊት አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ ሊጸድቅ እንደሚችል አስታውቀዋል።ረቡዕ፣ ሐምሌ 17/2011 በተካሔደው የውይይት መድረክ ላይ፣ የምርጫና ፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ በዕጩነት ለሚቀርቡ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ እንዳይከፈል የሚከለክለው አንቀጽ እንዲሻሻል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጠይቀው የነበረ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ በግብር ከፋዩ ሕዝብ የሚያዘው በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋል ስላለበት፣ የመንግሥት ሠራተኛ የሆነ ዕጩ የምርጫ ተወዳዳሪ፣ ምርጫው እስከሚጠናቀቅ ደሞዝ አይከፈለውም ብሏል።

ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ፣ በአዋጁ የመንግሥት ሠራተኛ በዕጩነት ለምርጫ ውድድር ሲቀርብ በጊዜያዊነት ከሥራ ገበታው መልቀቅ አለበት የሚለው አንቀጽ፣ የተማረውን የኅብረተሰብ ክፍል ደሞዜን አጣለሁ በሚል ስሜት ከፖለቲካ ተሳትፎ ሊገድበው ይችላል ብለዋል። የተማረው ክፍል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቦታ እንዳይኖረው የሚያደርግ አካሔድ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል። ይህም ወደ ምክር ቤቱ በሚመጣው ተመራጭ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል አስተያየታቸውን አክለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ለአገር ዐቀፍ ፓርቲዎች 10 ሺሕ አባላት ለክልል ፓርቲዎች ደግሞ 4 ሺሕ የሚለው ቁጥር የተጋነነ ስለሆነ፣ መቀነስ ይኖርበታል በማለት አስተያየት ሰጥተዋል። የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ በውይይቱ ለተነሱ ጥያቄዎችና ሐሳቦች ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ ላይ፣ በግብር ከፋዩ የሚበጀተው በጀት ለምርጫ ቅስቀሳና ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል በዕጩነት የሚቀርብ የመንግሥት ሠራተኛ ምርጫው እስከሚጠናቀቅ ደሞዝ አይከፈለውም ብለዋል።

ይህም በሕዝብ ሀብት፣ ገንዘብና በተቋማት አደረጃጀት ላይ የተዛባ አስተሳሰብ እንዳይመጣ ከማገዙ ባለፈው፣ የመንግሥት ተቋማት ተዓማኒና ለተቋቋሙለት ዓላማ ብቻ እንዲሠሩ በማድረግ መንግሥትና ፖለቲካን ለመለያየት ያስችላል ነው ያሉት።አንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ጠንካራ አማራጭ በመያዝና በማስተማር ዜጎችን በስፋት ማንቀሳቀስ ይኖርበታልም ብለዋል።

ብርቱካን በአዋጁ የተቀመጠው ቢያንስ ከአምስት ክልሎች 10 ሺሕ ሰው የሚለው ከአገሪቷ የሕዝብ ቁጥር አንጻር በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው አገር ዐቀፍ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተቀመጠውን ቁጥር በማሟላት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን የበለጠ ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here