አራት የኢዜማ አባላቶች በደቡብና በአማራ ክልሎች ታሰሩ

0
421
  • በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውም ታውቋል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በደቡብ ክልል አማሮ ወረዳ 1፣ በዳውሮ ዞን 2 እና በአማራ ክልል ቋራ ወረዳ 1 አባላቶቹ መታሰራቸውን አስታወቀ። እስረኞቹ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ቢገባቸውም አለመቅረባቸውን አዲስ ማለዳ ከፓርቲው ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ፓርቲው ሕግን ለማስከበር በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ሕግ ፊት መቅረባቸው ተገቢ መሆኑን ተቀብሎ፣ ተጠርጣሪዎች ከመታሰራቸው በፊት ለእስር የሚያበቃ በቂ ምክንያት መኖሩ መረጋገጥ እንዳለበት ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16 በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

ኢዜማ የአባላቶቹን ጉዳይ በክልሉ አመራሮች በኩል እየተከታተለ መሆኑን እና አባላቶቹ የታሰሩበትን ምክንያት እያጣራ መሆኑን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ናትናኤል ፈለቀ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የአገሪቱ ችግሮች መነሻ በተወሰነ ደረጃ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት መሆኑን ያስታወቀው ኢዜማ፣ ችግሮቹ በዘላቂነት የሚፈቱት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ ችግሮች ሲሻሻሉ እንደሆነ እንደሚያምን ነው የገለፀው።

ፓርቲው የሰጠው መግለጫ በደቡብ ክልል እየተነሳ ባለው የክልልነት ጥያቄ እና አለመረጋጋት ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ ማንኛውም ዜጋ ሕጉን መሰረት አድርጎ መያዝና ለሕግ መቅረብ እንዳለበት ትኩረት የሰጠም ነበር።

ከቀናት በፊት ከሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በዞኑ በሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ “እጅግ አሳዛኝ” ጉዳት መድረሱን የገለፀው ፓርቲው፣ በዚህም የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ በርካታ ንብረት መውደሙን እና ቤተ እምነቶች መቃጠላቸውን አስታውቋል። ይሁን እንጂ በአዋሳ እንዲህ ዓይነት ቀውስ ሊኖር እንደሚችል ፓርቲው መረጃ እንደነበረውና ይህንንም ለሚመለከተው የመንግሥት አካል አሳውቆ እንደነበር አክሎ ገልጿል።

ድርጊቱን ያወገዘው የፓርቲው መግለጫ፣ ክስተቱ እንደ አገር አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሳችንን የሚጠቁም ነው ብሏል። መንግሥት በሲዳማ ዞን የተፈጠረውን ችግር ለማርገብ አፋጣኝ ፖለቲካዊና ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ አለበት ያለው ኢዜማ፣ በጥፋቱ ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ አካላትን በማጣራት ለሕግ ማቅረብና ለሕዝብ ማሳወቅ እንደሚገባው እና ለተጎጂዎችም ተገቢው ካሳ እንዲከፈል ጠይቋል። በቀጣይ በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መንግሥት የፀጥታ መዋቅሩን በማጠናከር ዜጎችን ከጥቃት የመከላከል ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርቧል።

መንግሥት አሁን በሲዳማ ዞንም ይሁን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለተፈጠሩ ችግሮች አፋጣኝ ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ፣ በዚህ ጥፋት እጃቸው ያለበትን አካላት ሁሉ የሕግ አግባቡን በመከተልና በተገቢው አካላት በማጣራት ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቋል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here