ኤል ቲቪ በኪሳራ ከ20 በላይ ሠራተኛ ሊቀንስ ነው

0
891

ኤል ቲቪ የቴሌቭዥን ጣብያ ኪሳራ ገጥሞኛል በሚል ከ20 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችን ከሥራ ገበታቸው ሊያሰናብት መሆኑ ታወቀ።
የኤል ቲቪ የውስጥ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት ከሆነ የቴሌቭዥን ጣብያው በ2010 በተደረገው የውጪ ኦዲተር ሪፖርት መሰረት ድርጅቱ መክሰሩ ከመረጋገጡም በላይ እስከአሁን የሠራተኛ የወር ደሞዝና የሳተላይት ክፍያ መሸፈን ባለመቻሉ ምክንያት የተወሰኑ ሠራተኞችን ለመቀነስ ተገዷል ብለዋል። ከሥራቸው እንዲሰናበቱ ከተወሰነባቸው መካከል አንድ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንዳረጋገጡት ከሆነ ድርጅቱ በደረሰበት ኪሳራ ምክንያት ድርጅቱ ውሉን ለማቋረጥ መገደዱን እንዳሳወቃቸው ጠቅሰው እስከ ነሐሴ መጨረሻ ድረስ መደበኛ ሥራችንን ከቀጠልን በኋላ መስከረም 1/2012 ውላችን ይቋረጣልም ብለዋል።

የቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ብሩ ግን በመሰረታዊነት ሠራተኞቹ የተቀነሱት በመሥሪያ ቤቱ በተደረገው ዓመታዊ ግምገማ የብቃት ማነስ ስለታየባቸው ነው። ሠራተኞቹ ከሥራ ገበታቸው እንዲሰናበቱ ዋና ምክንያት የብቃት ማነስ ዋነኛ ቢሆንም ድርጅቱ ላይ የደረሰው ኪሳራም ትክክል መሆኑን አምነዋል።

ሠራተኞቹ ጨምረው እንደገለፁት ጣብያው ሠራተኞቹን ሲያባርር የሰጠው ደብዳቤ በተደረገው የውጪ ኦዲተር ሪፖርት መሰረት ድርጅቱ መክሰሩ ስለታወቀ የሠራተኛ ቅነሳ ተደርጓል የሚል ነው። በደረሳቸው ደብዳቤ ላይም የብቃት ማነስ ጉዳይ ያለመጠቀሱን ገልጸው እነሱ እንዲባበሩ ከተወሰነ በኋላም ሌሎች ኹለት ሠራተኞች መቀጠራቸውንም አግባብነት የሌለው እንዳደረገባቸው ተናግረዋል።

ኤል ቲቪ ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመት በፊት የሙከራ ስርጭቱን በማስተላለፍ ሥራ የጀመረ ሲሆን ከአንድ ዓመት የሙከራ ጊዜ በኋላ በ2008 የተለያዩ መደበኛ ዝግጅቶችን ለተመልካቾች በማቅረብ የ24 ሰዓት መደበኛ ስርጭቱን እያስተላለፈ ይገኛል። በገመቺስ ቡባ (ዶ/ር) ባለቤትነት የተጀመረው የቴሌቭዥን ጣብያ መቀመጫው በሰሜን አሜሪካ ሲሆን ስርጭቱን በጀመረ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በአገር ውስጥ ተገቢውን የስርጭት ፈቃድ ሳያገኙ ስርጭት ከጀመሩ ሌሎች ሦስት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች መካከል አንዱ እንደነበር ይታወሳል። ነገር ግን የቴሌቭዥን ጣብያው በአሁኑ ሰዓት የስርጭት ፍቃድ አግኝቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here