“አፍሪካዊያን ሴቶች ኮድ ማድረግ ይችላሉ” የሚለው እንቅስቃሴ ሰኞ ይጀምራል

0
768

የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት ‘ዩኤን ውሜን’ ከኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት አፍሪካዊያን ሴቶች ኮድ ማድረግ ይችላሉ በሚል እንቅስቃሴ 450 ኢትዮጵያዊያን ሴት ተማሪዎችን የሚያሰለጥንበት መርሃ ግብር በመጪው ሰኞ፣ ሐምሌ 22 ይጀምራል። ከሦስት ክልሎች አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ እና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥት 150 የኹለተኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎችን በመምረጥ ወደ ሥልጠናው የሚያስገባቸው ይኸው እንቅስቃሴ በተጠቀሰው ቀን በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ጊቢ ውስጥ እንደሚካሔድ አዲስ ማለዳ ከተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። በተመሳሳይ ቀንም በአዳማ እና በሐዋሳ ሥልጠናው እንደሚጀመር ለማወቅ ተችሏል።

ሥልጠናው ‘ዩኤን ውሜን’ ከዓለም ዐቀፉ የቴሌኮም ኅብረትና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በጋራ በመሆን የጀመረው ሲሆን ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ የሆነው በኢትዮጵያ የዴንማርክ ኢምባሲም ድጋፍ እንዳደረገ ተገልጿል። ሥልጠናው ሴቶች በቴክኖሎጂ በኩል ያላቸውን ውስን ዕውቀት ለማጠንከር የታሰበ ሲሆን የሦስት ሳምንታት የሥልጠና ጊዜያት እንደሚኖረውም ተጠብቋል። ሥልጠናው ከመሰረታዊ ኮምፒውተር እውቀት አንስቶ ኮምፒውተር ሳይንስ እውቀትና የግራፊክስ ሥልጠናም እንደሚያካትት ዩኤን ውሜን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በነሐሴ 2010 በአዲስ አበባ የተጀመረው ሥልጠናው በመጀመሪያ ዙር ከ32 የተለያዩ አፍሪካ አገራት የተወጣጡ 88 ሴት ሠልጣኞችን ያሳተፈ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ቀጥሎም ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሔደው ኹለተኛው ዙር ሥልጠና 43 ሴቶች ከሰባት ደቡባዊ አፍሪካ አገራት የተሳተፉበት ነበር።

ዩኤን ውሜን የሥልጠናውን ግብ ባስቀመጠበት ወቅት ሴቶች በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የላቀ ደረጃ እንዲኖራቸው እና የበቁ የኮምፒውተር ባለሙያዎች፣ እና የግራፊክስ ዲዛይነሮች እንዲሆኑ ዕቅድ አስቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪም የሥልጠናው ተሳታፊ ሴቶች የአፍሪካን ዲጂታል ምጣኔ ሀብቱ ላይ እንዲሳተፉ እና እንዲመሩ ታስቧል። በተመሳሳይም ሴቶች ሥልጠናውን ወስደው ወደ ቴክኖሎጂ ከመቅረባቸውም ባሻገር የሥራውን ዓለም ሲቀላቀሉም ከሌሎች ተወዳዳሪዎች በላቀ ተመራጭነታቸው እንዲሰፋም ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ታውቋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሥልጠናው ወጣት ሴቶች ወደ ቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ወደ ቴክኖሎጂ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲያመሩም መንገድ ያሳያል ተብሏል ።

እንደ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የባሕልና የሳይንስ ድርጅት ዩኔስኮ መረጃ መሰረት ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት በሳይንስና ቴክኖሎጂ እና በሒሳብ ዕውቀት ካላቸው ዜጎች ውስጥ 30 በመቶ ብቻ ሴቶች እንደሆኑ ይጠቅሳል። ይህንም ተመርኩዞ ሴቶችን በማሰልጠን በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያለውን የፆታ ተዋፅዖ ክፍተት መሙላት እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 38 ሐምሌ 20 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here