በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት መንሸራተት ያጋጥማል ተባለ

በዘንድሮው የክረምት ወራት ከሚያጋጥመው መጠኑ ከፍ ያለ ዝናብ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 30 ድረስ ድንገተኛ መሬት መንሸራተት ያጋጥማል ተብሎ እንደሚጠበቅ የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ኤጀንሲው ጨምሮ እንደገለጸው በክረምቱ ወራት ከፍ ያለ የዝናብ መጠን የሚያገኙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ድንገተኛ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት እንደሚያጋጥማቸው ገልፆ ከእነዚህም ውስጥ መዲናችን አዲስ አበባ በመሬት መንሸራተት ልትመታ እንደምትችል እና ነዋሪው ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ አሳስቧል።

መግለጫው ጨምሮ እንደገለፀው፤ ከመዲናዋ አዲስ አበባ በተጨማሪ የዝናብ ስርጭቱ በበርካታ አካባቢዎች ላይ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን በውሃው ዘርፍ እንቅስቃሰው ላይ ሊያሳድር የሚችለው አዎንታዊ አስተዋፅዖ ሲሆን፤ በአብዛኛው የክረምት ተጠቃሚ ተፋሰሶች ላይ በመጠንም ሆነ በስርጭት የተሻለ እርጥበት ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል። ኢጀንሲው አያይዞም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ያገኛሉ የተባሉትን አካባቢዎችንም ይፋ አድርጓል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በአብዛኛው የአባይ፣ ተከዜ፣ ባሮ አኮቦ፣ የኦሞ ጊቤ የላይኛውና የመካከለኛው አዋሽ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ዋቢ ሸበሌ እና የላይኛው ገና ሌዳዋ ተፋሰሶች ላይ ከከፍተኛ እርጥበት እስከ እርጥበታማ የዝናብ መጠን ይኖራቸዋል ሲል አስታውቋል።

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በምሥራቅና ሰሜን ምሥራቅ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት እንደሚያጋጥምና ውሃን ጠብቆ ማቆየት አስፈላጊ እንደሆነ ብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በክረምቱ ወራት ከሚጥለው ዝናብ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥም ይችላል ስለተባለው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋ፤ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ስለ ጉዳዩ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት መረጃ፤ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች ተመሳሳይ የድንገተኛ ጎርፍና መሬት መንሸራተት ችግሮች ያጋጥማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ኮሚሽኑም መረጃው ስላለው የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝና ወንዝና ውሃ ዳር የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እየሠራሁ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል። አያይዞም ከነሐሴ 1 ጀምሮ እስከ መስከረም ሊዘልቅ የሚችል ከባድ ዝናብ ይኖራል ተብሎ እንደሚታሰብ ገልፆ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፏል።

ኮሚሽኑ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ላይ ሊከሰት ይችላል ያለውን የውሃ እጥረት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከወዲሁ አስፈላጊውን ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል። በአብዛኛው ዝናብ እጥረት የሚከሰትባቸው አካባቢዎች የአርብቶ አደር መኖሪያዎች ስለሆኑ ለእንስሳቶቻቸው የሚሆን የመጠጥ ውሃ እንዳይቸገሩ ወደ እርጥበታማ አጎራባች አካባቢዎች እንዲንቀሳቀሱ ከክረምቱ መግቢያ ጀምሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሲሰጣቸው እንደነበር ለመወቅ ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here