በቤንሻንጉል በግጭት ምክንያት የምርት መቀነስ አጋጠመ

0
701

በ2011 የምርት አመት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመኸር የእርሻ ዘመን ከበቆሎና ማሽላ ምርት 30 ሚሊዮን ኩንታል ይሰበሰባል ተብሎ ቢጠበቅም፣ በክልሉ በተከሰቱ ግጭቶችና ባለው አለመረጋጋት ምክንያት የ8 ሚሊዮን ኩንታል ቅናሽ መታየቱ ታወቀ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ሙሳ አህመድ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ የቅባት እህሎችን ጨምሮ የበቆሎና ማሽላ ሰብሎችን በ109 ሺ ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ ለመዝራት እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ሰብል በሚዘራበት ወቅት ከ20 ወረዳዎች ውስጥ ምርቱ በሚመረትባቸው 7 ወረዳዎች ላይ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ 30 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ብቻ በመስኖ ለመዝራት መቻሉን ተናግረዋል።

በሰብል ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቅናሽ መታየቱን ተከትሎም በ2012 በክልሉ የኑሮ ውድነት እንዳይከሰት ስጋት መፈጠሩን ሙሳ ተናግረዋል። ይህንንም ለመፍታት የመስኖ ምርት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነም አክለው ገልጸዋል።

ከፍተኛ ምርት በሚሰበሰብባቸው መተከል ዞን እና በካማሽ ዞን 7 ወረዳዎች በ2010 እና በ2011 በጀት ዓመት ሰብል በሚዘራበት ወቅት አለመግባበቶች በመፈጠራቸው፣ በታቀደው መሠረት ሊሠራ አልቻለም።

የግብርና ቢሮው ባለሞያዎችም ለአርሶ አደሩ የሚያደርጉትን ሙያዊ እገዛ ማከናወን ባለመቻላቸው በምርት መቀነሱ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲያሳድር ማድረጉንም ሃላፊው ጠቅሰዋል። ባለሙያዎች ወደ አርሶ አደሩ በሚሄዱበት ወቅትም በድንገት የሚከሰቱ ግጭቶች አደጋ በመጣላቸው ስጋት ውስጥ ገብተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

በያሶ እና በሎጂጋንፎይ ወረዳዎች የለማው የበቆሎ ምርትም ምንም ጉዳት ሳይደርስበት 35 ሺህ ኩንታል ዘር መሰብሰቡንም ሙሳ ገልጸዋል። ግጭቱ ከአርሶ አደሩ ባሻገር አምራች ድርጅቶችን፣ ባለሃብቶችንና የጉልበት ሠራተኞችንም ጭምር ከአካባቢው አንዲወጡ በማድረግ የብዙዎችን ኑሮ ያመሰቃቀለ ነበር ሲሉም ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና፣ የቤኒሻኑጉል ጉሙዝ የግብርናና እንስሳት ሃብት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ፍቃዱ ወዬሳ እንዳሉት፤ በአካባቢ በነበረው አለመረጋጋት በካማሺ ዞን፣ በቡልዲጊሉ ወረዳና በሌሎችም ሰሊጥን በአግባቡ መሰብሰብ አልተቻለም። አርሶ አደሩና ባለሃብቱ ከአካባቢው ነዋሪና ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በመተባበር ምርቱን ለመሰብሰበ ጥረት ቢደረግም በታሰበው መጠን ሰብሉን መሰብሰብ አለመቻሉን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባለፈው የምርት ዘመን ከሰሊጥ ምርት 309 ሺህ 550 ሜትሪከ ቶን ምርት ወደ ወጭ በመላክ 394 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በዘንድሮው ዓመት ከ780 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በሰሊጥ የተሸፈነ ሲሆን ምርቶቹ በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ይገኛሉ።

በአሁኑ ሰዓት ሰላም እርቋቸው በነበሩት 7 ወረዳዎች የተረጋጋ ነገር መኖሩንም ከክልሉ የግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here